“የኢትዮጵያ ፖለቲካ ዕምብረቱ የግለሰብ ተክለ ሠብዕና የተጫነው ነው”

0
1319

ዓለማየሁ አረዳ(ዶ/ር) የፖለቲካ ተኝታኝና ጸሐፊና ሲሆኑ፣ በፖለቲካው ዘርፍ ሐሳብ ከማካፈል በተጨማሪ “ምሁሩ” እና “የሰጎን ፖለቲካ” የተሠኙ በፖለቲካ ላይ የሚያጠነጥኑ ኹለት መጻሕፈት ለንባብ አብቅተዋል፡፡ ዓለማየሁ ለኢትዮጵያ ፖለቲካ ሐሳብ በማዋጣት የድርሻቸውን እያበረከቱ የሚገኙ ምሁር ናቸው፡፡ ስለ ኢትዮጵያ ወቅታዊ ኹኔታ፣ ሥለ አገራዊ ምክክርና ስለ ኢትዮጵያ የፖለቲካ ምኅዳር ከአዲስ ማለዳው መርሻ ጥሩነህ ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡

ዓለማየሁ አረዳ(ዶ/ር)፡- ኢትዮጵያ በተለይ ባለፉት ኹለትና ሦስት ዓመታት ውስብስብ ችግሮች ውስጥ ገብታለች፣ ኢትዮጵያ አሁን ያለችብትን ኹኔታ እንደ ፖለቲካ ባለሙያ እንዴት ይገልጹታል?
አዲስ ማለዳ፡- ካለፉት ኹለት ሦስት ወራት ከነበረው ትንሽ ውጥረቱ ቀለል ያለበት እና ኢትዮጵያን ወጥረው የያዙት ነገሮች በምን ኹኔታ ነው የተቋጩት ወይም የት ጋር ነው የቆሙት የሚለው ነገር ግልጽ ያልሆነበት፣ ኢትዮጵያ ደግሞ በታሪኳ በጣም ጠያቂ የሆነ ኹሉን ነገር ከፊቴ እንደድራማ እየሠራችሁ አሳዩኝ ልወቅ የሚል ሕብረተሰብ የተፈጠረበት የፖለቲካ ድባብ ውስጥ ነው ያለነው። መንግስት ደግሞ ብዙዎቹን ነገሮች ከዚህ በፊት በጀመረው መልክ ሳይሆን ትንሽ ግልጽነቱን ቀነስ ያደረገበት ኹኔታ ውስጥ ነው ያለነው። አዲሱ የተፈጠረው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሒደት ውስጥ ማለት በየዐሥር ዓመቱ ብትከፋፍለው ሚዲያው አሁን ‹ዩኒፖላር› አይደለም።

መንግሥት የሚቆጣጠረው ሚዲያ ብቻ አይደለም ያለው፤ መንግሥት የሚቆጣጠረው ሚዲያ አለ፤ ከዛ ውጭ ደግሞ ማኅበራዊ ሚዲያዉ አለ። ሚዲያ ደግሞ ብዙ ጊዜ ዓለም ላይ እንደሚያደርገው ትክክለኛውን መረጃ በማያገኝበት ጊዜ ብርበራ ውስጥ ይገባል። በተለይ ማኅበራዊ ሚዲያው ልዩ ልዩ የሴራ ትንተናዎችን ከዚህም ከዚያም እየቆነጣጠሩ የፖለቲካውን አውድ በምንም ዓይነት የተረጋጋ እንዳይሆን፣ እንዳይተኛ የመቀስቀስ ሥራ የሚሠራበት ሁኔታ ውስጥ ስላለን የተወሠነ ሥጋት የተወሠነ መረጋጋትም ያለበት ኹኔታ ውስጥ ነው ያለነው።
የዲፕሎማሲው ሁኔታውን ስንመለከተው፣ በመጠኑ በተለይ ከዚህ ከአፍሪካ ኅብረት እና ከአውሮፓ ኅብረት የጋራ ግኑኝነት በኋላ በተለይ የአፍሪካ ኅብረት ስብሰባ ኢትዮጵያ ውስጥ ከተካሄደ በኋላ የተወሰነ መርገብ፣ ኢትዮጵያን የሚያስጨንቁ ነገሮች መላላት ይታያል።

ከዛ በተረፈ ያለው የፖለቲካ አስተሳሰብ ብዙ ጊዜ ግርታ የሚፈጥረው በአሁኑ ሕወሓት በአፋርም በአማራ ክልልም የተወሰኑ አካባቢዎችን በመውረርና በመድፍ በመምታት የሚያደርሳቸው ጉዳት ላይ የፌዴራል መንግሥቱ ምንም ተሳትፎ ያለው አይመስልም። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግን ከክልሎቹ በተለይ ከአፋር ጋር አብረን እየሠራን ነው ይሉሃል። ግን ምንድነው እየተሠራ ያለው? ሕዝቡ ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ሕወሓትን መምታት ጦርነቱን መጨረስ ይመስለዋል። እንደዚህ ዓይነት ጦርነት ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ አያልቅም። ብዙ ጊዜ እንዲያውም ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ አጠፋዋለው ብለህ ስትመታው ሌላ መዘዝ ልትመዝ ትችላለህ። ስለዚህ አጠቃላይ ያለንበት ሁኔታ እኔ ስመለከተው መጠነኛ የመረጋጋት ሁኔታ ይታያል፣ ግን ብዙ ጊዜ የሚበጠብጡ እና የሚረብሹ ነገሮችም ሥጋት ውስጥ የሚከቱ ነገሮችም አሉ።

ሕብረተሰቡ ዛሬ ንገሩኝ የሚል ሆኗል፤ መንግሥት ምስጢር እንዳለው ይታወቃል። ግን እሱም ቢሆን ፊቴ ይቅረብ የሚል ስሜት በሕዝቡ ውስጥ ይታያል። አንዱ አካባቢ ሒደህ ስትጠይቅ ባይገልጸውም ባያብራራውም ብዥታ ውስጥ ነው። በአንዳንድ ግለሰቦች ላይ ያለው ጥላቻ ጨምሯል።

የኢትዮጵያ ፖለቲካ እየረጋ (ኖርማላየዝ እያደረገ) ነው። ከዚህ በፊት ልክ እንደሚፈላ ውኃ በሁሉም አቅጣጫ እየተንተከተከ ዛሬ ወዴት ይሄዳል እያለ ያሳስበን የነበረው ሁኔታ ቀዝቀዝ እያለ እየሄደ ይመስለኛል። ምክንያቱም በሕወሓትም በኩል ስትመለከተው የጣር ሁኔታ ነው የምትመለከተው። የበለጠ ግን ፖለቲካውን እያወሳሰበው ያለው የኦሮሞ ክልል ጉዳይ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩም እንዳሉት፣ ኦነግ ሸኔ በኦሮሚያ ውስጥ እንደልቡ እንዲምነሸነሽ የቻለው በምን ምክንያት ነው? የኦሮሞ ሕዝብ ለምን አቀፈው? ለምን ዝም አለው? በእርግጥ ኦሮሞዎችም ይገደላሉ፤ ዘራቸው ተለይቶ በየቦታው የሚገደሉ ቢኖሩም፣ ግን ኦሮሞዎችም ይሞታሉ። ለምንድነው የኦሮሞ ሕዝብ የታገሰው? የኦሮሞ ሕዝብ ምንድነው የሚፈልገው? ኦነግ ሸኔን የመሰለ ኃይል በውስጡ እንዲመላለስ ይፈልጋል ወይ? ሌላው ነገር ግልጽ ያልሆነው መንግሥት ብዙ ደፍሮ የማይሄድበት የኦነግ፣ የኦፌኮ እና ሌሎች አክራሪ የሆኑ ሕጋዊ ነን ብለው

በሕጋዊነት ሽፋንም የሚንቀሳቀሱ የኦሮሞ ድርጅቶች ምንድነው ሚናቸው?
የኢትዮጵያ መንግስት በእኔ ሐሳብ እስትራቴጂው መጥፎ አይደለም። ጥሩ ነው አላልኩም! መጥፎ ግን አይደለም። ምክንያቱም ለሕወሓት የሚገባው ይሄ ነው፤ እዛው መቆየት አለበት የሚል እሳቤ ነው ያለው። እኔ በጣም በጣም ለኔ እንደውም አስፈሪው ነገር በኦነግ ሸኔ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጠየቁት አይነት የኦሮሞ ሕዝብ ለምን አቀፈው? እነዚህ ደግሞ የኦሮሞ ተቃዋሚዎች ናቸው የሚባሉት ብልጽግናን የሚቃወሙ የኦሮሞ ድርጀቶች ምንድነው አቋማቸ? በኦነግ ሸኔ ኦሮሚያ ውስጥ ለውጥ እንዲመጣ ይፈልጋሉ ወይ? የሚለው ነገር ግልፅ ውይይት አልተደረገበትም። የኦነግ ሸኔ ጉዳይ ዝም ብሎ የተድበሰበሰ ነው።

የሰሜኑ የኢትዮጵያ ጦርነት ከተጀመረ አንድ ዓመት አልፎታል፣ ይሁን እንጂ አሁንም ዕልባት አላገኘም። የፖለቲካ እና ወታደራዊ ባለሙያዎች ጦርነቱ የተራዘመ እንዳይሆን ሲወተውቱ ነበር፤ ነገር ግን የተራዘመ ጦርነት መሆኑ አልቀረም። ጦርነቱ በምን መልኩ ዕልባት ማግኘት አለበት ይላሉ?
ሕወሓት እስከዛሬ ድረስ ከኢትዮጵያ መንግስት እና ከሌሎች የክልል ኃይሎች ጋር ባደረገው ፍልሚያ ብዙ ስህተቶችን ሠርቷል። እጅግ በርካታ የኢትዮጵያ ወጣቶችም አልቀዋል። የትግራይ ልኂቃን ተቃዋሚ ነን ብለው የተሰለፉም አሉ። እነዚህ ኃይሎች ትግራይ ላይ እየደረሰ ያለውን ጉዳት ተረድተው ሕወሓትን በቃ ብዙ ርቀት ልትሄድ አትችልም፣ ብዙ ሠው መስዋዕት ተደረገ። በቃ በውሸት ከዚህ በላይ መሄድ አንችልም የሚል አቋም ቢወስዱ ኑሮ ሕወሓት የቀረበለትን ቅድመ ሁኔታ ተቀብሎ ችግሩ የሚፈታበት ሁኔታ ይመጣ ነበር።

የትግራይ ተወላጅ የትም ይሁን የት ሕወሓት ላይ ያለው አቋም ካልተቀየረ እና መቀየር ካልጀመረ፣ ሕወሓት ይዞት እየሄደ ያለው መንገድ ስህተት እንደሆነ እስካልተገነዘበ ድረስ ጦርነቱ ላይቆም ይችላል። ኹለተኛ ደግሞ ሕወሓት እራሱ ቢገነዘብ እና በዚህ የጥፋት መንገድ እስከመጨረሻው ድረስ ዘልቆ ሊሄድ እንደማይችል ሊረዳ ቢችል፣ የኢትዮጵያ መንግስት እንደ በዳይ እንደ ጨቋኝ አድርገው ሲመለከቱ የነበሩ የሚዲያ አካላት፣ አገሮችና ትልልቅ ድርጅቶች ቀስ እያሉ እግራቸውን ወደኋላ እየሳቡ ባሉበት ሁኔታን ተገንዝቦ ወደ ሰላሙ ቢሄድ ኖሮ አንዱ መፍትሔ ነበር።

ግን አሁን ስንመለከተው ሕወሓት እንዲያውም ቅድመ ሁኔታወችን ለጥጦ እስከ ኤርትራ ድረስ ወስዶ ነገሩን የበለጠ እያውሰበሰበው ነው። በአብዛኛው ሕብረተሰብ እና የፖለቲካ ልኂቃንም ሕወሓት ላይ ወረራ አድርገን መቀሌ ድረስ ሔደን አስወግደነው መምጣት ነው የሚሉ አሉ። ይሄ መንገድ በትግራይ ውስጥ ትልቅ ብሔርተኝነትን የሚቀሰቀቅስ በመሆኑ ጦርነቱን ያበርደዋል ማለት በጣም አስቸጋሪ ይመስለኛል።

ምክንያቱም እንዲወረሩ ነው የሚፈልጉት። በተለያዩ ሚዲያ ሲናገሩም እኮ ስንስማቸው፣ ሊፈጁን ነው፤ ዘር ማጥፋት ሊያካሂዱብን ነው የሚሉት የሕወሓት አባላት ብቻ ሳይሆኑ ከሕወሓት ውጭ የሆኑትም ምሁራን ጭምር ናቸው። ስለዚህ ሔደህ በአንድ ጊዜ ጥርግ አድርገህ መጨረስም አትችልም።

የኢትዮጵያ መንግስት ግልጽ አቋሙን በትክክል የዓለም አቀፉ ሕብረተሰብ እንዲያውቅ እያደረገ ጦርነቱን እና ዲፕሎማሲውን አቀናጅቶ በማስኬድ፤ ሕወሓትን የወረራ ዕቅድ የማያወጣበት ደረጃ እንዲደርስ፣ አጎራባች አካባቢዎች በመድፍ የማይመቱበት ሁኔታ በመፍጠር፣ እና ትግራይ ውስጥ ባለው ሕብረተሰብ መካከል እንዲሆን አፍኖ የመያዝ ዘዴ ሊከተል ይገባል።

ቆቦ ላይ ወይም ድንበር ላይ ለምን ትቆማለህ? ትግራይም ኢትዮጵያ ነው። የተወሰነ ኪሎ ሜትር ገባ ብለህ አትቆምም። የአፋር ሕፃናት፣ ሴቶች፣ ሽማግሌወች መጠቃት የለባቸውም። መንግሥት እነዚህ ነገሮች የመጠበቅ ኃላፊነት አለበት። የተወሰነ አካባቢውን ይዘህ፣ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን ብቻ በማሳለፍ ደጋፊዎቹም እንዲያውቁ በማድረግ፣ በተለይ ደግሞ በጣም በጣም ስልታዊ በሆነ መንገድ የሕወሓትን ኃይል በማዳከም ጥያቄው በሕወሓት እና በትግራይ ሕዝብ መካከል እንዲሆን ማድረግ አንዱ የመጀመሪያው ይመስለኛል።

አለበለዚያ ግን ለኢትዮጵያ ሥጋት ነው። ዛሬ አፋርን ደበደበ፤ ነገ ዋጃን መታ፤ ከነገ ወዲያ ጠለምትን ደበደበ እያልን የምንኖርበት ሁኔታ መቆም አለበት። የኢትዮጵያ ሠራዊት እሽ መቀሌ ደረሰ አይሂድ፣ ነገር ግን ለምንድነው ከድንበሩ ሀምሳ ኪሎ ሜትር ራድየስ ላይ ለምን እውነተኛውን ከበባ አያደርግም?
ኹለተኛ ሕዝቡ በኢትዮጵያ በኩል ፕሮፖጋንዳውን እንዲያገኝ ምንም ጥረት ሲደረግ አታይም። እዛው እነሱ በያዙት ቴሌቪዥን ስርጭት ጭንቅላቱ ተይዞ ነው ያለው። ለምንድነው ሌላ ዘዴ የማይፈለገው? ለምንድነው የዓለም አቀፉ ሕብረተሰብ የበለጠ እንዲገነዘበው ለምን አይደረግም እና የሚዲያ ዘመቻ የሳይኮሎጅ ጦርነት ለምንድነው እየተፋፋመ የማይሄደው? በእንደዚህ ዓይነት መንገድ ሕወሓትን ከራሱ እውነታ ጋር ፊት ለፊት እንዲገናኝ ማድረግ ዘላቂ መፍትሔ ሊያመጣ ይችላል።

በምንም ዓይነት ኹኔታ የአፋር ሕፃናት እንዲገደሉ መፈቀድ የለበትም። ምክንያቱም አውሮፓውያን የሕወሓትን መጥፎነት እንዲያውቁ ኢትዮጵያውያን መሞት የለባቸውም። አምጥተህ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ምክትል ዋና ጸሐፊን አፋርን አስጎበኘህ፤ የተደፈሩ ሴቶችን አስጎበኘህ፤ ነገም ይሄን ልታደርግ ነው። ይሄ ሞኝነት ይመስለኛል።

ሕወሓት በምንም ዓይነት የአፋር እና የአማራ ሴቶችን እየደፈረ፣ ሕፃናት እየገደለ፣ ሽማግሌወችን በመድፍ እየደበደበ የሚኖርበት ኹኔታ ግን መኖር የለበትም። ይህን ማድረግ ከተቻለ ሕወሓት ያለ ጦርነት መኖር ስለማይችል፣ የመጀመሪያ ጠቡ የሚሆነው እርስ በርሱ ነው። ስለዚህ በተለይ ደግሞ የትግራይ ህዝብ መረጃ እንዲደርሰው ለማድረግ የሚሰራው ስራ በጣም ደካማ ይመስለኛል።

አሁን የተያዘው ፈሊጥ ምንድነው መሰለህ፣ እኛኮ ድሮም ቢሆን መጥፎ አይደለንም ሕወሓት ነው መጥፎ የሚል ቅስቀሳ ለምዕራባውያን እያደረግን ይመስላል። በሌላ በኩል ደግሞ ተደራደሩ ሲባል የተዘበራረቀ ነገር ነው የሚነገሩህ፤ አንዱ አይደረግም ይላል ሌላው መደራደር አይቀሬ ነው ይላል። ስለምንስ የኢትዮጵያ ሕዝብ ቢያንስ ቢያነስ እንዴት ኹለቱን ያጣል፤ የትግራይን ሕዝብ እየተሰቃየ ነው።

ሦስተኛው በኢትዮጵያ ውስጥ ማለት ከትግራይ ውጭ ያሉት የትግራይ ተወላጆች ግልጽ አቋማቸው መታወቅ አለበት። የኢትዮጵያ ሠራዊት እየሞተ ኹሉን ነገር አረጋግቶ ትግራይ የምትባል ክልል እንድትኖር ነው የሚፈልገው ወይስ እንድትገነጠል? የሚፈልጉት መታወቅ አለበት።
የመንግስት እስትራቴጂ ግለጽ መሆን አለበት። የሚደራደር ከሆነ ከሕወሓት ጋራ በምን ኹኔታ? ምን ይዞ? ምን ግብ ለማምጣት ? ስለዚህ ይንገረን፡፤ ግልጽ እስትራቴጅ ይዞ ይምጣ። ብደግመው ብደግመው የማይሰለቸኝ ግን የኢትዮጵያ መንግሥት ለአፋር ሕጻናት፣ ለአፋር ሕዝብ፣ ለአማራ ሕዝብ ልዩ ኃላፊነት አለበት። በመድፍ ነጋ ጠባ የሚሞቱ ሕጻናት እና የሚሰደዱ ሠዎችን እየቆጠሩ መኖር ሰልችቶናል።

አሁን ያለው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አስተዳደር(ብልጽግና ፓርቲ) ለውጥ ከታሰበው በተቃራኒ ሆኗል የሚሉ አሉ። እርሶ ምን ይላሉ?
የጠቅላይ ሚኒስትሩ አስተዳደር ያመጣው ቀውስ (ክራይስስ) ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዛ ቀውስ ውስጥ አወጣለሁ አልወጣም በሚል ሥጋት ውስጥ በተንጠለጠለበት ሰዓት ላይ የፓርቲ ሳይሆን ግለሰብ ድምጽ፣ የግለሰብ ተክለ ሠውነት እና ተክለ ሠብዕና የጎላበት የፖለቲካ ንግግር፣ የፖለቲካ ቋንቋ ነው አየር ላይ አንሳፎን ይዞን የሄደው። ኢትዮጵያን እግዚአብሔር ይባርካት ሲባል፣ መደመር አለብን ሲባል፣ አንድ መሆን አለብን ይጠቅማል ሲባል፣ ኢትዮጵያ ጥንታዊት አገር ነች ታሪኳ መከበር አለበት ሲባል፣ ኹላችንም ከዚህ በፊት ስናሰበው ስንመኘው የነበረውን ነገር ባልተለመደ ሁኔታ በአንድ ሰው አማካይነት ሲጻፍ ሲወራ አየር ላይ ነው የተንሳፈፍነው። አሁን ከአየሩ ላይ እየወረድን ነው ያለነው። እየወረድን ስናይ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ዕምብረቱ የግለሰብ ተክለ ሠብዕና የተጫነው ነው። ድርጅታዊ አቅሙ አሮጌ ነው።

በአሮጌው አስተሳሰብ ላይ የተገነባ ድርጅት እና አዲስ አስተሳሰብ ለማንጸባረቅ የሚሞክር መሪ እነዚህ ኹለቱ መካከል ያለው ጉዳይ ነው እኛን እያንጓለለን ያለው። የሚሠራው ድሮ ኢሕአዲግ በሚሠራው መንገድ ነው። ዋነኛው የመንግሥት መሠረቱ ምንም አልተቀየረም፤ እንዳለ ነው። ከላይ ግን ፖለቲካል አስተዳደሩና፣ ላይ የሚባለው ነገር ከታች ምን ያህል በራሱ በድርጅቱ ውስጥ ተመጧል? ውኃ ቢሆን ምን ያህል ሠርጎ ገብቷል ብለህ ብትጠይቅ ብዙ ሰው ሊነግርህ የሚችለው ነገር ድርጅቱ እና ዶክተር ዐቢይ የሚሉት ነገር አንድ ባንድ እንዳልተጣጣመ በደንብ ትመለከታለህ።

ለዚህም ነው በቅርብ ጊዜ ንግግራቸው ሠውየው ከዚህ በፊት ኹሉ ነገር አልጋ ባልጋ ኹሉ ሰው ደግ ኹሉን በደግነት ማሰብ፣ ስለሰወች ክፋት አለማሰብ ነበር ሲነግሩን የነበረው፤ ዛሬ ደግሞ ቢሮክራሲው ሌባ እንደሆነ፣ አጭበርባሪ እንደሆነ፣ ነገ በሚዲያ እና ሁሉ ነገር እንደሚቆጣጠሩት፣ ሊቀጥል እንደማይችል ወደ ማስፈራራት ሔደዋል። ይሔንን ማስፈራራት ከየትኛውም ፓርቲ ኃላፊ አትሰማም፤ እንዲያውም የፈሩ አይመስልም። አንዳንድ ነገሮች ጥርት ብለው እንኳን ወይይት እንዲደረግባቸው እሚፈለግ አይመስልም።

ፖለቲካ ሁልጊዜ የፖለቲካ አመራር ድርጅት ይፈልጋል። ድርጅትን ደግሞ የሚፈጥረው የፖለቲካ አስተሳሰብ ነው። ሐሳብ ነው የፖለቲካ ዕውቀቱን ይዞ ድርጅቱ ውስጥ የሚገባው። ያ ሐሳብ ሰርጾ ካልገባ ድርጅት የለም ማለት ነው፤ ሐሳቡ አለ ግን የተደራጀ ድርጅት የለውም ማለት ነው።

ድርጅት የሰዎች መሰብሰብ ማለት አይደለም። ለምሳሌ በተያዘው አካሄድ እንኳን ብትመለከት ብልፅግና ሲመጣ ከዚህ በፊት በብሔር የነበሩ አደረጃጀቶች አንድ ላይ መሆን ይሻላል፣ በአንድ ድርጅት ተዋኅዶ የብሔር ነገር ይጠፋል ነበር የመሰለን፤ የሚታየውና መሬት ላይ ያለው ግን ሌላ ነው።

የአማራ፣ የኦሮሞ፣ የአፋር ብልጽግና ተከፋፍለው ይታያሉ። ለምንድን ነው እንደዚህ የሚሆነው ብለህ ስጠይቅ ቅርጫፎች ናቸው ይሉሀል። መግለጫ መስጠት ካለባቸው አንድላይ ነው። ተለያይተው ግን መግለጫ ሲሰጡ ይታያሉ፤ ስለዚህ በየክልሉ አሥራ አንድ ፓርቲ አለ ማለት ነው።

ይሄ አስተሳሰብ ለምን ቆየ ካልን ብዙ ጠላቶች ስለተነሱበት ነው። ሕወሓት አሁን ላለው ብልጽግና ትልቅ ውለታ ነው የዋለለት። አሜሪካ ትልቅ ውለታ ነው የዋለችለት። የኢትዮጵያ ሕዝብ ምድር ላይ ምንጣፉን ሳይሆን ጣራውን እየተመለከተ ደግፎ ነው የኖረው። በአድዋ ስሜት ነው እንጂ የተቀሰቀስነው አሁን ባለው የሲቪክ መብትና ድሞክራሲ አይደለም።

ዶክተር ዐቢይ መጥፎ መሪ አይደሉም፤ ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ድርጅቱን በአዲስ መልክ ማዋቀር ችለዋል ወይ የሚለው ጥያቄ ነው መነሳት ያለበት። በአዲስ መልክ መዋቀር ብቻ አይደለም፣ አዲስ ሰው ብቻ ማምጣት አይደለም የአሠራር እና የአስተሳሰብ ለውጥ ማምጣት አለበት። የኢትዮጵያ ሕዝብ ፊትለፊቱ ላይ ተስፋ ሳይሆን እስኪ ዕድል ዕንስጥ ብሎ ነው ዕድል የሠጠው።

አሁን በያዝነው አካሄድ የምንሄድ ከሆነ ችግሮች አይገጥሙንም ብየ አላስብም። የዐቢይ አሕመድ አስተዳደር ያለበት ኹኔታ እና ኢትዮጵያ ያለችበት ኹኔታ ላይ ስንነሳ የነበርናቸው ችግሮች አሁንም አሉ።

ኢትዮጵያ ከገጠሟት ፈተና መውጫ መንገድ ይከፍታል የተባለለት አገራዊ ምክክር ሂደት ተጀምሯል። በሳይንሱ ፕሪፓሬሽን ፌዝ፣ ፕሮሰስ ፌዝና ኢምፕለመንቴሽን ፌዝ አለው እስካሁን የነበረውን ሂደትስ ይህን ያማከለና ሊያግባባ በሚችል ሁኔታ መሰረት ጥሏል ብለው ያምናሉ?
አንደኛ ኮሚሽኑ እስከዛሬ ድረስ ኢትዮጵያን አስጨንቀው የያዟትን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ የብሄር ጥያቄ እና ሌሎች ችግሮችን ጨምሮ በደንብ ተገንዝበው ውይይቱ በሰከነ እና በደንብ በተደራጀ መልክ ልዩ ልዩ አወያይ ፈጥረው ማወያየት ይጠበቅባቸዋል።

እነዚህ ከተካሄዱ በኋላ ሁለተኛው ተግባር የሚወስዳቸውን መረጃዎች በትክክል መተግበር ይኖርበታል። እነዚህ መረጃዎች በትክክለኛ ሁኔታ ከተወሰዱ በኃላ ማፅደቅ ያስፈልጋል። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህገመንግስቱ፣ የስርአተ ትምህርቱ፣ የልዩ ልዩ መሰረታዊ እሴቶች የሚስተካከሉበትና የጋራ መስመር የሚይዙበት ስለሆነ በደንብ መደራጀት ይኖርበታል ብየ አምናለሁ።

አገራዊ ምክክሩ የታሰበውን ውጤት እንዲያመጣና ለችግሮች የመፍትሔ በር እንዲከፍት በምን ሁኔታ መካሄድ አለበት?
ስለ ምክከሩ የሌሎች አገራት ልምድ መመልከት እንችላለን። ለምሳሌ ቱኒዚያ የፖለቲካ ችግሯን ለመፍታት የሄደችበት መንገድ ስንመለከት፣ ሙሀመድ ቡአዚህ እራሱ ላይ ነዳጅ ካርከፈከፈ በኋላ እረብሻ ተነሳ፣ ፕሬዝዳንቱ አገር ጥለው ጠፉ በዚያን ሰአት ላይ አገሪቱ ነውጥ ውስጥ እንዳትገባና ከዚያ ፖለቲካ ችግር ውስጥ የታደጋት ብሄራዊ የምክክር መድረክ የረዳት ሲሆን፣ ይህንንም የታገለው የሲቪክ ማህበረሰቡ ነው።

ደቡብ አፍሪካን ስንመለከት ከአፓርታይድ ወደ ድሞክራሲ ሽግግር ማድረግ ነበረባት፣ ሽግግሩን ለማድረግ ግን ማንዴላ ከእስር እንደሚፈቱ ሲታወቅ በነጮችና በጥቁሮች መካከል ከፍተኛ ያለመስማማት ችግሮች ነበሩ። በመጨረሻም ማንዴላ ከተፈቱ በኋላ በአገሪቱ ምርጫ እንዲካሄድ ስምምነት ላይ ተደርሶ፣ በምርጫው መሰረት ጥቁሮች አሸንፈው የስልጣን ወንበሩን እንዲይዙ፣ ነጮች ደግሞ በነፃነት እንዲኖሩ የተደረገበት የሽግግር ጊዜ ነበር።

የኮሎምቢያን ስንመለከት በአገሪቱ የደፈጣ ውጊያ የነበረ ሲሆን፣ ይህን ዉጊያ ለማብረድ መንግስት ከተዋጊዎች ጋር እየተዋጋ በነበረበት ጊዜ በጦርነት አይቋጭ ሲል ያገሪቷ ፕሬዚዳንት በጎ ፍቃድ አሳይተው ከተዋጊዎች ጋር እርቅ አድርገዋል።

ሩዋንዳ የቱትሲና የሁቲ አንድ ግጭት ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ሁሉም አለ። የፖለቲካ ቀውሱ አለ፣ ሽግግር መደረግ አለበት። እንደገና ህወሓት አለ፣ ኦነግ ሸኔ አለ ከነዚህ ቡድኖች ጋር እንዋጋለን። የኢትዮጵያ ጉዳይ እንደ ቱኒዚያ፣ ኮሎምቢያ፣ ደቡብ አፍሪካ ነው።
ለምሳሌ የመንን ስንመለከት፣ እዚያ በነበሩ የሁቲ ቡድኖች እና በአገሪቱ መንግስት መካከል ሰላም ለማምጣት የተደረገው ጥረት አለመሳካቱን ተከትሎ ጦርነቱ ቀጠለ፣ የኛ ግን እንደዛ አይደለም፣ ይሄ ድርድር እና ምክክር ካልተሳካ እጅግ ከባድና ከምንገምተው በላይ የፖለቲካ ቀውስ ውስጥ ነው የምንገባው።

ምክንያቱም ሁሉም ተፎካካሪዎች አሉና እኛ ብሄራዊ ምክክሩን የምንፈልገው ወደ ድሞክራሲ ለመሸጋገር ነው። ባለፈው አመት ምርጫ ብልፅግና ስለተመረጠ የኢትዮጵያ ህዝብ ወደ ዲሞክራሲ አልተሻገረም።

ወደ ድሞክራሲ የተሸጋገረ ህዝብ እኮ የይስሙላ ንግግር እየተደረገለት የሚሄድ ህዝብ አይደለም። በደንብ የኑሮን ውድነት ላይ ግልፅ የሆነ መረጃ እያገኘና ጥቅሞቹ እየተከበሩ መሄድ አለባቸው። ዛሬ የተወሰኑ የብሄር አባለት ምስራቅ ወለጋ እና መተከል መኖር አይችሉም።
ይሄ ነው ድሞክራሲ፣ ከዚህ ውስጥ መውጣት አለብን። ይሄን የደፈጣ ውጊያ የሚለውን ስሜት መዝጋት አለብን። የስራ ሽግግር ማድረግ፣ ያልተረጋጋና ያልተናበበ ፖለቲካ ይዘን ኮሚሽኑ ገለልተኛ አይሆንም በማለት ምክክሩ ላይ አልሳተፍም የሚል ተፎካካሪ ሀይል ባለበት አገር በውይይቱ የማንስማማ ከሆነ ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ ነው የምንገባው። ኢትዮጵያ ውስጥ ሁሉም ቀውስ ስላለ በዚህ ድርድርና ምክክር የማይፈቱና መልካም ሆነ ቦታ ላይ የማንደርስ ከሆነ የባሰ ከፍተኛ ቀውስ ነው የሚፈጠረው።

አገራዊ ምክክሩ ሂደቱን ጠብቆ በትክክል ካልተመራ ምን አይነት ችግር ሊፈጥር ይችላል?
ቅድም እንዳልኩት ከድጡ ወደ ማጡ ሄደናል ያልኩት ነው። ሁላችንም በገባንበትና በተስማማንበት የፖለቲካ አስተሳሰብ ላይ ተመስርተን ካለንበት ቀውስ ውስጥ በምንወጣበት ጊዜ በምናውቀው ጎዳና ሁላችንም በምናየው ፋና የምንሄድ አይነት ሆነን ቢሆን ኑሮ አንድ ቦታ ላይ ሲበላሽ እንዴት ነው ወደመልካም ነገር እንሄዳለን ወይ ስንል፣ ወደድጡ የተመለስንበት ነው እንል ነበር። እንዳልኩት የፖለቲካ ሂደቱ ኢህአዴግ ከገባ ጀምሮ ከነበርንበት ቀውስ ውስጥ ስንወጣ ትቦውን ይዘው የወጡት ከሕወሓት ኢህአዴግ ውስጥ የወጡ ሰዎች ናቸው። እነሱ ራሳቸው እዛ ውስጥ ሊተርፉና በመሪነት ሊቆዩ የሚችሉት መልካም መልካም ነገር ሲናገሩ ነው። ለመስራትማ ጊዜ ያስፈልጋቸዋል። ስለዚህ ምንድን ነው ያደረጉት፣ የዶክተር ዐቢይ ተክለስብዕና በጣም ተፅእኖ ስላደረገ ሁላችንንም አየር ላይ አንጠልጥሎን ነበር። አራት ዐመት ፈጀብን መሬት ላይ ለመውረድ። እኔ ወደማጡ ገብተናል ብዬ አላስብም። ይህን ስል መልካም ነው ማለቴ አይደለም። አሁን ይህ ነገር እንደሚነገረው አይደለም እንዴ? የሚል ጥያቄ የምናነሳበት ደረጃ ላይ ደርሰን እንደሠው ማሰብ ጀምረናል። ለምሳሌ፣ ባለፈው የተካሄደው ምርጫ ዛሬ

ቢካሄድ ብልፅግና ያሸንፍ ነበር?
የኢትዮጵያ ፖለቲካ ምህዳር ከድጥ ወደ ማጡ መውጣት ያልቻለው ለምን ይመስለዎታል?
መሬት ላይ ስላንሳፈፈን መሬት ላይ ሊያወርደን የሚችለው ምናልባት ሌላ ሐይል አይኖርም እስኪ ለእሱ እድል እንስጠው ተብሎ ነው ማለት እንችላለን። እኔ እንደውም የሽግግሩ ወቅት ከሶስት ዓመት አምስት ዓመት ተጨመረለት ነው የምለው። በዚህ ጊዜ ነው ምክክሩ ወደሽግግሩ ይዞን የሚሄደው። በስሜታችን በተሟሟቅነው ሳይሆን በምናውቀው ነገር እየተመራን አገራችን የምናሳድግበት ሁኔታ ውስጥ እንድንገባ ይህ ምክክር በአግባቡ ከያዝነው ሊረዳን ይችላል።

ኢትዮጵያ ለገጠማት ችግር መነሻ የፖለቲካ ስርዓቱና ፖለቲከኞች መሆናቸው ብዙ ጊዜ ይጠቀሳል የኢትዮጵያን ፖለቲካ እና ፖለቲከኞች(ፓርቲዎች) መሰረታዊ ችግር ምንድን ነው?
ከቀውስ ውስጥ ስንወጣ እነዛው በኢህአዴግ ዘመን የነበሩ ድርጅቶች የብሔርና የልዩነት አጀንዳቸውን እንደያዙ ነው ቁጭ ያሉት። እነሱ ትላንትና ውስጥ ነው ያሉት። ችግር ብለው ያነሱት የነበረው ክልላችንን እኛ እንደፈለግን አልገዛንም፤ ሕወሓት ከለከለን ጣልቃ እየገባ፣ መሬታችንን ነጠቀን ነው እንጂ ያሉት በብሔር ተደራጅተው ልዩነትን እያስፋፉ የሚሄድ ፌደራሊዝም አይጠቅምም የሚል ደረጃ ላይ አልደረሱም። ሂደቱ እየተካሄደ እያለ አይደል እንዴ ክልል ካልሆንን ብለው ሲታገሉ የነበረው። እድል እንኳን ሊሰጡት አልተቻለም። እነዚህ ሰዎች በመሰረተ ሐሳቡ የሕወሓት ርዕዮተ ዓለም ጠላቶች አይደሉም። የበላይነቱ፣ አለቃነቱ፣ ማፈኑ ነው ያስጠላቸው። ለቀቅ እንዲደረጉና እያንዳንዱ የብሔረሰብ ሊቅ የራሱን ብሔር እንደልቡ ሊገዛው ነው የፈለገው። ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ እነዚህን የአካባቢ ማንነቶች በተቻለ መጠን ለዜጋዊ ብሔርተኝነት ወይም ለዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝንት እድል በሚሰጥ መልኩ አርቃ መሄድ ካልቻለች በስተቀር ምንም ለውጥ አይመጣም። ወደዛ ነው እኮ መሄድ ያለብን። እኛ ለብዙ ዘመን አገራዊ ብሔርተንነት ከነገስታቱ ዘመን ጀምሮ በደርግም ለረጅም ጊዜ አብሮን ኑሯል። ኢህአዴግ ሲመጣ የብሔር ፌደራሊዝምን መሠረተልንና ወደውስጣችን ወደልዩነታችን ማየት ጀመርን። ዛሬ ስንሄድ ስንሻገር ሶስተኛውንና ኢትዮጵያ ውስጥ በስም እንኳን ተጠርቶ የማያውቅ ናሽናሊዝምን ያዝን።


ቅጽ 4 ቁጥር 174 የካቲት 26 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here