በአዲስ አበባ የኤች አይ ቪ ኤድስ ወረርሽኝ ስርጭት በታቀደው መጠን መቀነስ አልቻለም

0
583

የመዲነዋ የወረርሽኝ መጠን 3.2 በመቶ ነው

በአዲስ አበባ ያለው የኤች አይ ቪ ኤድስ ወረርሽኝ የሥርጭት መጠኑ በሚፈለገው ልክ መቀነስ አለመቻሉ ተገለጸ። በከተማዋ ባለፈው ዐሥር ዓመት ወስጥ በቫይረሱ የመያዝ መጠን በሚፈለገው ልክ መቀነስ እንዳልቻለ የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል።
በከተማዋ ያለው የኤች አይ ቪ ኤዲስ ወረርሽኝ የሥርጭት መጠን 3 ነጥብ 2 በመቶ ሲሆን፣ ከክልሎች አንጻር ሲታይ መጠኑ በጣም ከፍተኛ መሆኑ ተነግሯል።

የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ የዘርፈ ብዙ ምላሽ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ፈለቀች አንዳርጌ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ በመዲናዋ ባለፉት ዐሥር አመታት የቫይረሱ የሥርጭት መጠን ጨምሯል ባይባልም፣ መቀነስ በሚገባው ልክ ግን አልቀነሰም ነው ያሉት።
ለዚህም እንደምክንያት የተነሱት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እና ሌሎች በአገሪቱ የተከሠቱ ሰው ሠራሽ ችግሮች ናቸው። ችግሮቹ የማኅበረሠቡን ትኩረት በመሳብ ለኤች አይ ቪ ትኩረት እንዳይሠጥ ማድረጋቸውን የገለጹት ዳይሬክተሯ፣ የተለያዩ የመንግሥት፣ የግልና የማኅበረሠብ ተቋማት፣ እንዲሁም ግብረ ሠናይ ድርጅቶች የቫይረሱን ወረርሽኝ ለመቀነስ ካስቀመጡት ግብ አንጻር ውስንነት እንዳለባቸው አስቀምጠዋል።

የመገናኛ ብዙኃንም ችግሩን በማንሳት ሕብረተሠቡ እንዳይዘናጋ ከማድረግ አኳያ ክፍተት አለባቸው ያሉት ዳይሬክተሯ፣ በሚመለከታቸው ተቋማት እንዲሁም በማኅበረሠቡ ዘንድ ያለው ቸልተኝነት በዚህ ከቀጠለ የቫይረሱ ሥርጭት መጠን ሊያገረሽ እንደሚችል ነው የጠቆሙት።
ቀደም ባሉት ዓመታት ሥርጭቱን ለመቀነስ ሠፊ የሕዝብ ግንኙነት እና የንቅናቄ ሥራዎች ይሠሩ የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ላይ ግን ያን ከማድረግ አንጻር ብዙ ክፍተት መኖሩን አመላክተዋል።

በአሁኑ ወቅት 107 ሺሕ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ የሚገኝ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ ከ62 በመቶ በላይ የሚሆኑት ሴቶች መሆናቸው ተገልጿል። ከአጠቃላይ የቫይረሱ ተጠቂዎችም 14 በመቶ የሚሆኑት ከወላጆቻቸው የተላለፈባቸው ናቸው ነው የተባለው።

በዚህም፣ የረዥም ርቀት አሽከረካሪዎች፣ የሕግ ታራሚዎች እና ተንቀሳቅሰው የሚሠሩ ሠዎች ቫይረሱ ካለባችው ሰዎች ውስጥ የላቀውን ቁጥር የሚይዙ ሲሆን፣ በተለየ መልኩ ደግሞ ሴተኛ አዳሪዎች በከፍተኛ ኹኔታ ችግር ውስጥ እንደሆኑ የገለጹት ዳይሬክተሯ ናቸው።
በቫይረሱ አዲስ የመያዝ መጠኑ በሴቶች ላይ በጣም ከፍተኛ ሲሆን፣ አፍላ ወጣቶች በተለይም ዕድሜያቸው ከ24 ዓመት በታች የሆኑት ከፍተኛ ተጠቂ መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል።

ወረርሽኙ በሴቶች ላይ ከፍተኛ የሆነው ካላቸው ዝቅተኛ ገቢ የተነሳ የወሲብ ሥራን እንደገቢ ማግኛ በመቁጠራቸው ሲሆን፣ ወንዶች የሚያደርሱባቸው ጫናና ወሲባዊ ጥቃትም ሌላኛው መንስኤ መሆኑ ተመላክቷል።

ሴቶች ከዚህ በላይ የቫይረሱ ተጠቂ እንዳይሆኑም የገቢ ማግኛ ሥልጠናዎች እንደሚሠጣቸውና ከተቻለም የሥራ ማስጀመሪያ ገንዘብ እንደሚያገኙ የጠቀሱት ዳይሬክተሯ፣ ከዚህ ባለፈም ጤናማ የወሲብ ሥራ እንዲሠሩ ለማድረግ ኮንዶምን በአግባቡ እንዲጠቀሙ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ ይሠራል ሲሉ ተናግረዋል።

ሆኖም ከኮንዶም ሥርጭት ጋር በተያያዘ በኹሉም ቦታዎች ለማቅረብ ችግሮች መኖራቸውን ሳይጠቅሱ አላለፉም። የዲኬቲ ኢትዮጵያ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍም በበኩሉ፣ የኮንዶም ዕጥረት ባይኖርም፣ ጥቅም ላይ የሚውልን ኮንዶም ማረጋገጫ የሚሠጠው ተቋም መጓትት እንዳለበትና በከተማዋ ካለው ከፍተኛ የቫይረሱ የሥርጭት መጠን አንጻር ይህ መስተካከል እንዳለበት ለአዲስ ማለዳ ገልጿል።

በአዲስ አበባ ከተማ የቫይረሱ የሥርጭት መጠን ከጋምቤላ ብሔራዊ ክልል ቀጥሎ በኹለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ነው የተባለው። በአገር አቀፍ ደረጃ 0.9 በመሆን የቫይረሱ ሥርጭት ወረርሽኝ ደረጃ ባይደርስም፣ ወረርሽኝ ለመባል ግን ጥቂት እንደቀረው ተመላክቷል።
ባለፈው ዓመት የነበረው የቫይረሱ ሥርጭት መጠን 3 ነጥብ 4 እንደነበርና በአስር ዓመት ውስጥ ያለው የሥርጭት መጥን ለውጥም ተመሳሳይ እንደሆነ ተገልጿል።


ቅጽ 4 ቁጥር 174 የካቲት 26 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here