የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የቀድሞው ቤተ-መንግሥት ሕንጻ በወቅቱ ባለመታደሱ አደጋ ተጋርጦበታል

0
661

አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ውስጥ የሚገኘው የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የቀድሞው ቤተ-መንግሥት፣ የአሁኑ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም የሚገኝበት ሕንጻ በወቅቱ ባለመታደሱ አደጋ እንደተጋረጠበት የተቋሙ ሠራተኞች ተናገሩ።

አዲስ ማለዳ በቦታው ተገኝታ እንደተመለከተችው፣ የውጨኛው የሕንጻው ክፍል መሰነጣጠቅ ያጋጠመው ሲሆን፣ ጣራው ፍሳሽ እንደሚያስገባና ጣውላውም እንዳረጀ፣ ሞዛይኩም እየለቀቀ መሆኑ ይታያል። በሕንጻው ዙሪያ ያሉት የውኃ ማስተላለፊያ መስመሮችም ያረጁና ጥገና የሚፈልጉ ሲሆን፣ የሕንጻው ደረጃዎችም በጎርፍ የተጠቁ መሆናቸውን ለማየት ተችሏል።

የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ዳይሬክተር ታከለ መርዕድ (ዶ/ር)፣ ሕንጻው እንዲታደስ በየጊዜው ጥያቄ ሲቀርብ መቆየቱን ጠቅሰው፣ አሁን ላይ ጥያቄው በዩኒቨርስቲውን ይሁንታ በማግኘቱ በመጭው በጀት ዓመት ሊታደስ እንደሚችል ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የተቋማዊ ልማት ምክትል ፕሬዝዳንት ጽሕፈት ቤት ተጠንቶ፣ ለመሉ ሕንጻው መሠረታዊ ዕድሳት 56 ሚሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ ታውቋል ነው ያሉት። የሕንጻው ቅርሳዊ ይዘት እንደተጠበቀ ሆኖ ወጥ ዕድሳት እንዲደረግለት መታቀዱንም ገልጸዋል።

ገንዘብ ሚኒስቴር ከኹለት ዓመት ወዲህ ለቅርስ ጥገና በጀት መመደብ አቁሟል የሚባል ነገር አለ ያሉት ዳይሬክተሩ፣ መንግሥት ለቅርስና ቅርስ ነክ ለሆኑ ቤቶች ካለው ዝቅተኛ አመለካከት የተነሳ ሕንጻው እስካሁን ሳይታደስ መቆየቱን አንስተዋል። መንግሥት በራሱ ተነሳሽነት ቅርሶችን መጠበቅ እና መንከባከብ ነበረበት፤ አሁን እየሆነ ያለው ግን በተቃራኒ ነው። ቅርሶችን ለማሳደስና ለማስጠገን በልመናና በትግል መሆን አልነበረበትም የሚል አስተያየታቸውንም ገልጸዋል።

አሁንም ቢሆን ተቋሙ ዩኒቨርስቲውን ከመጠበቅ የራሱን የገቢ ምንጮችን እየፈለገ ነው ያሉ ሲሆን፣ ለዚህም በእንግሊዝ አገር የሚኖሩ እና ሌሎች የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ወዳጆችን እያነጋገርን ነው ብለዋል። በባለሙያ አስጠንተን የተጠየቀውን የገንዘብ መጠን በኢ-ሜል ልከንላቸው ምላሻቸውን እየጠበቅን ነው ሲሉም አክለዋል።

በሕንጻው ውስጥ የሚገኘው የራስ መኮንን አዳራሽ በ2011 የቅርስ ይዘቱ ምንም ሳይነካ እንደታደሰ የገለጹት ዳይሬክተሩ፣ አሁንም የሕንጻው የውስጥና የውጭ ክፍል ሙሉ አዳራሹ በታደሠበት መንገድ እንደሚታደስ ነው ያመላከቱት።
የራስ መኮነን አዳራሸ በሕንጻው ውስጥ የሚገኝ ሠፊ አዳራሽ ሲሆን፣ በተደረገለት ዕድሳትም ወለሉ በማሸን ተፈቅፍቆና ጣራው ቀለም ተቀብቶ የድምፅ ማዳመጫው እንዲስተካከል መደረጉን ለማወቅ ተችሏል።
ሕንጻውን ለማደስ ሙያዊ ብቃት እና ልምድ ያላቸው የአገር ውስጥ፣ እንዲሁም በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱ የውጭ ድርጅቶች መኖራቸውንም ተቋሙ ጠቁሟል።

ከ200 ባላነሰ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ማረፉ የሚገመተው የቀድሞው ገነተ-ልዑል ቤተ-መንግሥት፣ በ1927 ግንባታው ተጠናቆ ለአገልግሎት የዋለ ሲሆን፣ አሁን ላይ 88 ዓመቱ ነው ተብሏል። ከዐሥር ዓመት በፊት በባህልና ቱሪዝም ተቋም ዕድሳት ተደርጎለት የነበረ ቢሆንም፣ዕድሳቱ መስፈርቱን የጠበቀ እንዳልነበረ ነው የተመላከተው።

የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም አንድ አካል የሆነው እና በሜድሮክ ድጋፍ የተሠራው ቤተ- መጻሕፍትም እንዲሁ፣ ተሠርቶ ካለቀ ከዓመት በላይ ሳይሆነው የወለሉ ሴራሚክ መነሳቱን አዲስ ማለዳ አረጋግጣለች። ይህንንም ለመጠገን ዩኒቨርስቲው ጨረታ ማውጣቱንና ክረምቱ ሳይገባ ሊታደስ እንደሚችል የተቋሙ ዳይሬክተር ገልጸዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 174 የካቲት 26 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here