በሰሜን ወሎ ዞን ራያ ቆቦ ወረዳ፣ ቆቦ ከተማ የሚገኙ ኹለት ትምህርት ቤቶች የተፈናቃይ መጠለያ በመሆናቸው አራት ሺሕ ተማሪዎች በጦርነቱ ተቋርጦ የነበረ ትምህርታቸውን መቀጠል አለመቻላቸው ተገለጸ፡፡
ከዚህ ቀደም የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ በጦርነቱ የወደሙ ተቋማትን በመጠገን የተቋረጠውን የትምህርት ገበታ ለማስጀመር ተማሪዎቹን በመመዝገብ ላይ እንደሆነ መገለጹ የሚታወስ ሲሆን፣ በዕቅዱ መሠረት ሌሎች ትምህርት ቤቶች ወደ ቀደሞ ሥራቸው ቢመለሱም፣ ባልተቋጨው ጦርነት ምክንያት የተፈናቃይ መጠለያ የሆኑ ኹለት የቆቦ ከተማ ትምህርት ቤቶች ግን ሥራቸውን ማስቀጠል አልቻሉም ነው የተባለው፡፡
በሌሎች ዘጠኝ ትምህርት ቤቶች የሚገኙ ተማሪዎች ተቋርጦ ወደ ቆየው የትምህርት ገበታቸው ቢመለሱም፣ በቆቦ አጠቃላይ አንደኛ ደረጃ እና ሚሊኒየም ትምህርት ቤት ሲማሩ የነበሩ አራት ሺሕ ተማሪዎች ግን ከትምህርት ገበታ ውጭ መሆናቸውን የከተማው ከንቲባ አዲሱ ተሻገር(ዶ/ር) ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል፡፡
ከንቲባው ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ በከተማው የሚገኙ ዘጠኝ ትምህርት ቤቶች አገልግሎት የጀመሩ ሲሆን፣ ኹለቱ ትምህርት ቤቶች ግን ተፈናቃዮች የተጠለሉባቸው በመሆቸው ተማሪዎችን ተቀብለው የመማር ማስተማር አገልግሎት እንዳልጀመሩ ነው የተነገረው፡፡
በራያ አላማጣ፣ ዋጃ፣ ጥሙጋ እና በሌሎች አካባቢዎች ያሉ ነዋሪዎች ባልተቋጨው ጦርነት ምክንያት ወደ ቆቦ ከተማ ለማቅናት እንደተገደዱና ከ40 ሺሕ በላይ ተፈናቃዮች በከተማው እንዳሉ የገለጹት አዲሱ፣ ለተፈናቃዮች የሚሆን መጠለያ ባለመዘጋጀቱ ትምህርት ቤቶቹን ለመጠለያነት ማዋል መገደዳቸውን ነው ለአዲስ ማለዳ የገለጹት፡፡ተፈናቃዮቹ ቤት ንብረታቸውን ተዘርፈው ቀያቸውን ከመልቀቃቸው በተጨማሪ፣ አንፃራዊ ሠላም ባለበት አካባቢ ያሉ አገር ተረካቢ ተማሪዎች ከመስከረም 2014 ጀምሮ በጦርነቱ ምክንያት የተቋረጠ ትምህርታቸውን መቀጠል አለመቻላቸውን ነው ከከንቲባው ገለጻ መረዳት የተቻለው፡፡
በሌላ በኩል፣ በጦርነቱ ምክንያት የውኃ መሠረተ ልማት መውደሙ የሚታወቅ ቢሆንም፣ እስካሁን ምንም ዓይነት ጥገና ባለመደረጉ ከተማው ውስጥ የውኃ አቅርቦት ችግር እንዳለ የገለጹት አዲሱ፣ ከታኅሣሥ 11/2014 ጀምሮ ከዩኒሴፍ ባገኙት የጀነሬተር ድጋፍ በተወሰነ መልኩ ውኃ ለነዋሪው እያቀረቡ ቢቆዩም፣ የነዳጅ ዕጥረት መከሠቱን ተከትሎ ሠሞኑን አግልግሎት መስጠት አልተቻለም ብለዋል፡፡
አሁን የገጠመን ዋነኛው ችግር የነዳጅ ዕጥረት ነው ያሉት ከንቲባው፣ ውኃውን በጀነሬተር ሲስቡ በሰዓት 22 ሊትር ነዳጅ እንደሚፈጅና 16 ሰዓት መጠቀም እንዳለባቸው አብራተው፡፡ በዚህም በቀን 352፣ በወር 10ሺሕ 560 ሊትር ነዳጅ እንዲሚያስፈልጋቸው ነው የጠቆሙት፡፡
አያይዘውም፣ ምንም እንኳ ለኹሉም የማኅበረሠብ ክፍል ማዳረስ ባይቻልም፣ በተቻለ አቅም በጀነሬተር ተስቦ ሲዳረስ የነበረው የውኃ አቅርቦት በነዳጅ ዕጥረት ምክንትያት አገልገሎቱ ከተቋረጠ ኹለት ቀን አስቆጥሯል ነው ያሉት፡፡
አዲሱ አክለውም፣ ተፈናቃዮቹን ወደ ሌላ አካባቢ ሸኝተው፣ ይህ የማይሳካ ከሆነ ደግሞ ተማሪዎቹን ወደየትምህርት ቤቱ አሸጋሽገው ትምህርት ለማስጀመር እያሰቡ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
በትምህርት ገበታቸው ላይ መገኘት ያልቻሉ ተማሪዎችን በተመለከተ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የሕዝብ ግንኙነትና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ጌታቸው ቢያዝን፣ የተነሳውን ችግር ከሰሙ በኋላ ምላሽ ለመስጠት ቀጠሮ ቢሰጡም በቀጠሩት ወቅት ስልክ ለማንሳት ፈቀደኛ አልሆኑም፡፡
የክልሉ ትምህርት ቢሮ ከዚህ በፊት ሕወሓት ተቆጣጥሯቸው በነበሩ አካባቢዎች ላይ ከአራት ሺሕ በላይ የትምህርት ተቋማት በአስከፊ ኹኔታ መውደማቸውን እስከ ራያ ቆቦ ድረስ በመሄድ ማረጋገጡን ገልጾ፣ የወደሙትን የትምህርት ተቋማት ጠግኖ ትምህርት ለማስጀመር ተማሪዎችን በመመዝገብ ላይ እንደነበር ለአዲስ ማለዳ መናገሩና ጋዜጣዋም መዘገቧ አይዘነጋም፡፡
ቅጽ 4 ቁጥር 174 የካቲት 26 2014



