በሞጣ ከተማ ትናንት በተከሰተ ግጭት የ4 የጸጥታ ሃይሎች ህይወት ማለፉ ተገለፀ

0
824

ሰኞ የካቲት 28 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) በአማራ ክልል ምስራቅ ጎጃም ዞን በሞጣ ከተማ አስተዳደር የታጠቁ ሃይሎች በጸጥታ ሃይሉ ላይ በከፈቱት ተኩስ 4 የጸጥታ ሃይሎች ህይወት ማለፉን የሞጣ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ።

የከተማ አስተዳደሩ ዛሬ ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው አገር በተወረረ ጊዜ ጠላትን የሚፋለም በሰላም ጊዜ ወደ መደበኛ ሥራው የሚመለስ፤ የጀግንነት ታሪክ ያለውንና በግንባርም ከፀጥታ ሃይላችን ጋር ተዋድቆ ጠላትን ድል ያደረገዉን የፋኖ ሥም እየጠሩ ታጥቀዉ የሚንቀሳቀሱ ቡድኖች ከሌላ ወረዳ ጭምር በመሰባሰብ ጥቃት መፈፀማቸውን ገልጿል።

ጥቃቱም ትናንት የካቲት 27 ቀን 2014 ረፋዱ ላይ የተፈፀመ ሲሆን፤ የመብራት ሃይል መኪና በሃይል በመቀማት እና ሁለት እጁ እነሴ ወረዳ አየን ብርሃን ቀበሌ ምድብተኛ የነበረ የፖሊስ ኦፊሰርን መሳርያ በመቀማት ከተማ ላይ ችግር ለመፍጠር እንቅስቃሴ ሲያደርጉ፤ በህግ ማስከበር ላይ የነበሩ የ4 የጸጥታ ሃይሎችን ህይወት ማጥፋታቸው ገልጿል።

በጥቃቱ ህይወታቸው ያለፈው የጸጥታ ሃይሎች መዝገበ አለማየሁ፣ ታንቴ በየነ፣ ዘላለም ፀጋ እና አሸጋው ይታየው የተባሉ ግለሰቦች ሲሆኑ፤ ከእነርሱም በተጨማሪ በሌሎች የፖሊስ አባላትና ሚሊሻዎችም ጉዳት መድረሱን የከተማ አስተዳደሩ በመግለፅ፤ በተፈጠሪው ችግር መሪር ሃዘን እንደተሰማውም አስታውቋል።
_____________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here