ከአዲስ አበባ ወደ አዋሽ መልካሳ የተላኩ የወለጋ ተፈናቃዮች በቂ ሠብዓዊ ድጋፍ አላገኘንም አሉ

ከወለጋ ተፈናቅለው በአዲስ አበባ ጃን ሜዳ አካባቢ ተጠልለው የነበሩ ከ100 በላይ ሰዎች ወደ አዋሽ መልካሳ ከተማ ተገደው ቢወሰዱም፣ በቂ ሠብዓዊ ድጋፍ እየቀረበላቸው አለመሆኑን ለአዲስ ማለዳ ተናገሩ።

በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን በየጊዜው በሚፈጠረው የፀጥታ ችግር ከተለያዩ ቦታዎች ተፈናቅለው በአዲስ አበባ ጃን ሜዳ አካባቢ ተጠልለው የነበሩ ሰዎች ለአዲስ ማለዳ እንደገለፁት፣ የካቲት 17/2014 በከተማ አስተዳድሩ ውሳኔ መሠረት በፀጥታ አካላት ታጅበው አርሲ ዞን አሰላ ከተማ መርሲ ወረዳ ገብተው የነበረ ሲሆን፣ የሚያስተናግዳቸው የመንግሥት አካል አለማግኘታቸውን ተከትሎ ወደ ምስራቅ ሸዋ ዞን አዋሽ መልካሳ (አዋሽ ጎርጎ) ከተማ እንዲመለሱ ቢገደዱም፣ በቂ የሰብዓዊ ድጋፍ እንዳልተደረገላቸው እና የመጠለያ ችግር እንደገጠማቸው ተናገረዋል።

ተፈናቃዮቹ አክለውም፣ ቅሬታቸውን ለመገናኛ ብዙኃን በሚያሳውቁበት ወቅት የእጅ ስልካቸውን በፀጥታ ኃይሎች የተቀሙ ሲሆን፣ የመጠለያ ጣቢያ እንዲዘጋጅላቸው ለመንግሥት አካላት ያቀረቡትም ጥያቄ ምላሽ እንዳላገኘ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
እነዚሁ ተፈናቃዮቹ፣ ከዚህ ቀደም የካቲት 16/2014 የመጠለያ ጣቢያ ተዘጋጅቶላችኋል ተብለው በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተገደው ወደ አማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ደብረ-ብርሃን ከተማ የተላኩ ቢሆንም፣ በደብረ-ብርሀን በርካታ ተፈናቃዮች ያሉ መሆናቸውን ተከትሎ፣ የከተማ አስተዳደሩ አላስተናግድም ብሎ እንደመለሳቸው ይታወሳል።

በተጨማሪ፣ ከኹለት ወር በፊት በምዕራብ ወለጋ ዞን ባለው የፀጥታ ችግር ሳቢያ ከተለያዩ አካባቢያቸው የተፈናቀሉ ከአንድ መቶ በላይ የሚሆኑ ሠዎች በአዲስ አበባ አስኮ ክፍለ ከተማ፣ በአቡነ አረጋዊና በአስኮ ወጣቶች ማዕከል ተጠልለው የነበረ ቢሆንም፣ በመንግሥት አካል ከመጠለያቸው እንዲወጡ መገደዳቸውን ተፈናቃዮች ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ተፈናቃዮቹ አከባቢያቸውን ለቀው ከመጡበት ጊዜ አንስቶ ለከተማ አስተዳደሩ ተደጋጋሚ የድጋፍ ጥያቄ ቢያቀርቡም ምንም ዓይነት ምላሽ ያላገኙ ሲሆን፣ በመዲናዋ ነዋሪዎችና በሠብዓዊ ድርጅቶች በኩል ግን ድጋፍና የኹለት ወር የቤት ኪራይ ተከፍሎልናል ብለዋል።
አዲስ ማለዳ ስለ ጉዳዩ ለመጠየቅ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ያደረገችው ተደጋጋሚ የስልክ ጥሪ አልተሳካም።

ከተማ አስተዳደሩ ከአንድ ሳምንት በፊት ባወጣው መግለጫ እንደገለፀው፣ በወለጋ ዞን ያለውን የፀጥታ ችግር ተከትሎ ወደ አዲስ አበባ ከተማ የገቡ ዜጎችን አስመልክቶ እየተሠራጩ ያሉ ዘገባዎች የተሳሳቱ መሆናቸው ይታወቅልኝ ማለቱ አይዘነጋም።
ከተማ አስተዳደሩ፣ እነዚህ ዜጎች ወደ ከተማይቱ ከመጡበት ጊዜ አንስቶ ጊዜያዊ ድጋፎችን ከማድረግ ጀምሮ ዘላቂ መፍትሔ እንዲያገኙ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት መደረጉን ገልጿል።

ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው እስኪመለሱ ድረስ በጊዜያዊነት ሊቆዩበት ስለሚችሉበት ቦታ ከተማ አስተዳደሩ ከዜጎች ጋር ውይይት ማድረጉን እና የዜጎች ፈቃድ ላይ ተመስርቶ ከኦሮሚያ ክልል መንግሥትና ከብሔራዊ አደጋ መከላከልና ሥራ አመራር ኮሚሽን ጋር በጋራ በመሆን በጊዜያዊነት ሊያርፉበት የሚችሉበት ቦታ እያመቻቸ መሆኑን ጠቁሟል።


ቅጽ 4 ቁጥር 174 የካቲት 26 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here