የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ የቀብር ሥነ-ሥርዓት የፊታችን እሁድ መጋቢት 4 ይፈጸማል

0
1109

ማክሰኞ የካቲት 29 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አራተኛው ፓትርያርክ የብጹዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ የሽኝት መርሃ-ግብር እና የቀብር ሥነ-ሥርዓት የፊታችን እሁድ መጋቢት 4 ቀን 2014 እንደሚፈጸም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቅዱስ ሲኖዶስ አሳውቋል።

ቅዱስ ሲኖዶሱ በዛሬው ዕለት ባወጣው መግለጫ አስቀድሞ በተያዘው በመርሐ ግብር መሠረት ቅዳሜ መጋቢት 3 ቀን 2014 ከጠዋቱ 3:00 ሰዓት ጀምሮ የብጹዕነታቸው አስከሬን በመስቀል አደባባይ የሕዝባዊ ሽኝት መርሃ ግብር የሚከናወን መሆኑን ገልጿል።

ሥርዓተ ቀብራቸውም በማግስቱ እሁድ መጋቢት 4 ቀን 2014 ከማለዳው ጀምሮ የፍታት ሥነ ሥርዓት ተደርጎ በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የሚፈጸም እንደሚሆን የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ ገልፀዋል።

በሽኝት መርሀግብሩና በቀብር ሥርዓቱ ላይ ከሁሉም የአገሪቱ አካባቢ የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት የሚሰባሰቡ ሲሆን አገራትን ወክለው የሚመጡ ዜጎችም እንደሚሳተፉበት ቤተክርስቲያኗ አስታውቃለች።

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ትውልዳቸው በቀድሞው የጎንደር ክፍለ አገር በደብረ ታቦር አውራጃ አረጊት ኪዳነ ምሕረት ልዩ ስሟ ማር ምድር ሲሆን፤ ከአባታቸው ከብላታ ፈንታ ተሰማ እና ከእናታቸው ለምለም ገሰሰ በ1930 አብዝታ የፈተነቻቸውን ግን ንቀው በአርምሞ ድል ያደረጓትን ምድር ተቀላቀሉ፡፡

ቅዱስነታቸው ባሳለፍነው አርብ የካቲት 25 ቀን 2014 በተወለዱ በ84 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በድካም መለየታቸው ይታወሳል፡፡

_____________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here