ኢትዮጵያ ዘመናዊ የላይዳር ቴክኖሎጂን ለአየር ላይ ቅየሳ ሥራዎች እየተጠቀመች መሆኑ ተገለፀ

0
1243

አርብ መጋቢት 2 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) ኢትዮጵያ ዘመናዊ የላይዳር ቴክኖሎጂን ለአየር ላይ ቅየሳ ሥራዎች እየተጠቀመች መሆኑን በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።

በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶ/ር በለጠ ሞላ የተመራ ልዑክ ዘመናዊ የአየር ላይ ቅየሳ ሥራዎች የመስክ ምልከታ በአዲስ አበባ አየር ክልል ላይ አድርገዋል።

የላይዳር ቴክኖሎጂ ከአየር ላይ በመሆን በየሴኮንዶች ከፍተኛ ጉልበት ያለው የሌዘር ጨረር በመልቀቅ ምድር ላይ ያሉ ቁሶችን ከፍታ ሞዴል የሚያደርግ ቴክኖሎጂ ነው።

ኢንስቲትዩቱ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ የጂኦስፓሻል መረጃ መሰብሰቢያ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ለተልዕኮው መሳካት ያደረገው ዝግጁነት የሚበረታታ መሆኑን የተናገሩት ሚኒስትሩ የሚያመርታቸው መረጃዎች ለአገር ዕድገት ወሳኝ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

አክለውም ተቋሙ ዘርፈ ብዙ ሥምሪት ስላለው ሁሉም የሚመለከታቸው የመንግስት ተቋማት እቅዳቸውን ለማሳካት የጂኦስፓሻል መረጃን በግብዓትነት የሚጠቀሙ እንደ መሬት አስተዳደር፣ የመንገድ እና ግድብ ግንባታ፣ የመስኖና ተፋሰስ ልማት፣ የኢነርጂ መሠረተ ልማት ዝርጋታ እና የመሳሰሉ ቁልፍ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ከዚህ ተቋም አገልግሎቱን ማግኘት አለባቸው ብለዋል።

የጂኦስፓሻል ኢንፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቱሉ በሻ ዘርፉ ለአገራችን የ10 ዓመት መሪ የልማት ዕቅድ መሳካት ጉልህ ሚና ስላለው ከተለያዩ ተቋማት ጋር ቅንጅታዊ አሰራር በመፍጠር እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አገራችን ወደ ሥራ ያስገባችው የአየር ላይ ቅየሳ ላይዳር ቴክኖሎጂ በዓለም ላይ ቴክኖሎጂውን ከሚጠቀሙ አገራት ተርታ እንድትሰለፍ አድርጓታል።

ዘመናዊ በአየር ላይ የመሬት ካርታ ቅየሳ ቴክኖሎጂ ለመስራት በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ሊሰራ ለታሰበው ከእንጦጦ ወደ ኮተቤ የሚሄድ መንገድ የከፍታ መረጃ የማሰባሰብ ሥራ ሂደት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩን ጨምሮ የልዑክ ቡድኑ ከበረራና ከአየር ካርታ ቅየሳ ባለሙያዎች ጋር በበረራው መሳተፉን ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
_________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here