“ሲቄ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ‹አለንጋ› የሚል ትርጉም አለው። በገዳ ትውፊታዊ አስተዳደር ውስጥ በባሏ ጥቃት የደረሰባት ሚስት፣ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ባሏ ላይ የካሣ ውሳኔ የምታሳልፍበት ስርዓት ሲቄ ይባላል።
ኢትዮጵያውያን ብዙ ባህል እና ትውፊት ያለን እንደመሆናችን መጠን የተለያዩ እጅግ የተዋቡ አገራዊ አለባበሶች አሉን ። ነገር ግን፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ የአገራችን ወጣቶች አለባበስ፣ ባህል እና ወጉን እየዘነጋ የመጣ ይመስላል።
ከባህል ወጣ ያለ አለባበስ አሁን ላይ በስፋት ይስተዋላል። በተለይ ደግሞ የወጣቶችን አለባበስ ስንመለከት ከወግ እና ባህል ያፈነገጡ አልባሳትንና የአለባበስ ሥርዓት መመልከት እየተለመደ ነው። ምንም እንኳ አገራችን ብዙ ትውፊት ያላት በውስጧም እጅግ ብዙ የተዋቡ የአለባበስ ባህሎች የሚታዩባት ቢሆኑም፣ ሥልጣኔ ባመጣው ጣጣ ወጣቱ ባህል እና ወጉን እንዲረሳ፣ የባህር ማዶ በህልን እንዲናፍቅና በሌሎች ባህል ተጽዕኖ ሥር እንዲሆን ተደርጓል። አብዛኛው ወጣትም ለባዕዳን ባህልና ልማድ ሰለባ እየሆነ እንዳለ መረዳት ይቻላል።
አካሏን የሚያጋልጥ ነገር እስካለበሰች ድረስ አንድ ሴት ዘናጭ አይደለችም እስከመባል የደረስን ይመስላል። በዕምነታችን እና በባህላችን ሠውነትን ባልተገባ መልኩ ማጋለጥ ፈጽሞ ነውር እና የማይፈቀድ ነገር ቢሆንም፣ በአሁኑ ጊዜ ግን “ምንም ማለት አይደለም፤ አታካብዱ” የሚባልበት ጊዜ ላይ እየደረስን ስለመሆኑ አውራጎዳናዎች ላይ ብቅ ብሎ ማየቱ በቂ ማስረጃ ይሰጣል። አጉል መገላለጥ እና መሰልጠን ከባህል እና ከወግ ያርቃል በራስ መተማመንን ያጠፋል ። በአገር ልብስ ማማር፣ መዘነጥና መድመቅ ሲቻል የራስን ውበት ቀብሮ የባዕድ አገር ማንነትን መላበስ ምን ይሉታል? በአገራችን ቀደም ባሉት ጊዜያት ሴት ልጅ በተለይ ደግሞ በዓል ሲሆን የምትለብሰው ልብስ የሀበሻ ቀሚስ ነበር። አሁን ላይ ግን አለባበሷን እንደባህሏ አሳምራ ለብሳ የምትወጣ ሴት ልጅ ማግኘት በተለይ በአዘቦት ከባድ እየሆነ መጥቷል።
ቀደምት ኢትዮጵያውያን ጥጡን አብቅለው፣ ፈልቅቀው፣ ነድፈው፣ ፈትለው እና ሸምነው እራሳቸውን ሲያለብሱና ሌላን ሲያስተምሩ ኖረው ለዛሬው ትውልድ ሙያቸውን ከባህሉና ትውፊቱ ጋር አስተላልፈው አልፈዋል። አሁን ላይ ግን ትውልድ ወዴት እየሄደ ነው ያስብላል። የራሱን ንቆ የፈረንጅን ያከብራል። የራሳችን ውብ አለባበስ እያለን የባዕድ አገር ልብስ እየለበስን የራሳችንን ጥለነዋል። ለምን የራሳችንን ማንነት ችላ እንላለን። ያለንበትን ባህል ወግ እምነት ማህበራዊ አስተሳሰባችንን ስናከብረው አለምን የመሳብ አቅም እናገኛለን ፤ አለም ያከብረናል ።
ዛሬ ላይ እኛ የአሁን ትውልዶች ባህል እና ወጋችንን ጠብቀን ካላቆየን ቀጣይ ለሚመጣው ትውልድ ማን ተጠያቂ ሊሆን ነው። ከአሁኑ አካሄዳችንን ካላስተካከልን እድሜልካችንን የምንኮራበትን አለባበስ ካልያዝን በቆየንበት ቁጥር ለመመለስ አስቸጋሪ ይሆንብናል። ስለዚህ ባህላችንን እንወቅ፤ የራሳችንን ምርት በመጠቀም ዓለምን በተራችን ወደ እኛ የመሳብ አቅምን እናዳብር። ለዘመናዊ ባርነት ተገዥ አንሁን።
ልዩወርቅ ዲበኩሉ
ቅጽ 4 ቁጥር 175 መጋቢት 3 2014


