ኢትዮጵያ ሶርያን አትሆንም!

Views: 227

ኮቪድ-19 የተሰኘው የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ተከትሎ፣ የተለያዩ ዘረኛ አስተያየቶች በተለያየ አጋጣሚ ሲሰሙ ነበር። ይህም በተለይ በአሜሪካ በኩል ‹የቻይና ቫይረስ› እየተባለ መጠራቱ ዘረኝነትንና ጥላቻን ያስከትላል ተብሎ በመገናኛ ብዙኀን ቃሽ መቆየቱ ይታወሳል። በተጓዳኝ በኢትዮጵያ አሜሪካውያን ከቫይረሱ ጋር በተገናኘ ጥቃት ደርሶባቸዋል ተብሎ በመገናኛ ብዙኀን የተነገረው፣ ሌላ ዓላማም ያለው ነው ሲሉ ግዛቸው አበበ ይሞግታሉ። በተለይም አሜሪካ የሕዳሴ ግድቡን በተመለከተ በኢትዮጵያ ላይ ዓለማቀፍ ጫና ለመፍጠር የተጠቀመችበት ይሆናል ሲሉም የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀን ጉዳዩን አግንነው መስተጋባታቸውን ወቅሰዋል። እንዲያ ባለ ተግባር የተሳተፉ ሰዎች ካሉ ግን፣ በጣም ጥቂት ስለሚሆኑ፣ እንዲጠነቀቁ ማሳሰብ ይሻላል ብለዋል።

የሶርያ እርስ በርስ ግጭት ሊጀማምር ዳር ዳር ሲል፣ በደማስቆ የሚገኙ የአሜሪካና ፈረንሳይ አምባሳደሮች ከተቃዋሚዎችና አመጽ ለመስቀስ ዳር ዳር ከሚሉ ወገኖች ጋር ግልጽ ግንኙነት ያደርጉ ነበር። ሶርያ ውስጥ ቁጭ ብለው የአሳድን መንግሥት በግልጽ ከማውገዝ ጀምሮ፣ ተቃዋሚዎችን በገሃድ እስከ ማበረታታት የደረሱ ሥራዎችንም ይሠሩ ነበር። በሌላ አገር የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባት ሊባል የሚገባው አካሄድ ቢሆንም፣ በዚህ አቅጣጫ ነገሩን ለማየት የሞከረ የምዕራቡ ዓለም ጋዜጠኛ አልነበረም።

አምባሳደሮቹና ወኪሎቻቸው በተቃዋሚዎች ስብሰባ መካፈልን ጨምሮ በአመጹ ውስጥ በሰፊው እጃቸው ተነክሮ ስለነበር፣ እነሱ ወደ ስብሰባዎች ሲሄዱና ሲመለሱ ጣልቃ መግባታቸውን ያልወደዱ ሶርያውያን በየመንገዱ እየጠበቁ መኪኖቻቸውን በቲማቲምና በገማ እንቁላል ይደበድባሉ። ይህን ጉዳይ የአሜሪካ ድምጽ (ቪኦኤ) እና የጀርመኑ ዶቸቨለ፣ የአሳድ ደጋፊዎች የአሜሪካና የፈረንሳይ ኤምባሲ መኪኖችን አጠቁ እያሉ ዜና እንደነገሩን አይዘነጋም።

የሶርያ አመጽ ወደ እርስ በእርስ ግጭት ሲያድግ፣ የሶርያን መንግሥት የሚቃወሙና በምዕራባውያኑ የሚበረታቱ ሶርያውያን ብቻ ሳይሆኑ ከአሜሪካ፣ ከአውሮፓ፣ ከመካከለኛው ምሥራቅ ዓረብ አገራት፣ ከአፍጋኒስታን፣ ከፓኪስታን ወዘተ… ጭምር የተመለመሉ በሺሕዎች የሚቆጠሩ የሌሎች አገር ዜጎች የሆኑ ወጣቶች፣ ጎልማሶችና አዛውንቶችም ጭምር በሽብር ተግባር እየሠለጠኑ በገፍ ወደ ሶርያ እንዲገቡ ተደርገዋል። እነዚህ ግለሰቦች ከየአገሩ እየተነሱ ወደ ሶርያ ሲላኩ፣ አምባገነንነትን እንደሚዋጉ፣ በሶርያ ዴሞክራሲን እንደሚያሰፍኑ እየተነገረላቸው ወደ ሶርያ ቢገቡም፣ ተግባራቸው ግን ይህ አልነበረም።

በሰፊው ሲሠሩት የነበረው ሥራ የሽብር እንጂ ሌላ አልነበረም። በምዕራቡ ዓለም ሚዲያ ስለማይነገር፣ የሶርያ ሚዲያዎችም ስለታፈኑና ከሳተላይቶች እንዲወርዱ ስለተደረጉ (ናይል ሳትና ኣረብ ሳት ላይ ይገኙ ነበር) ሃቁ ቢሸፋፈንም፣ ሶርያ ውስጥ ቁጥር ስፍር የሌላቸው ቡድኖች የአሳድን መንግሥት በመዋጋት ሥም ይርመሰመሱ እንደነበረ ሊታወቅ ይገባል።

እነዚህ ቡድኖች የተለያዩ የውጭና የአገር ቤት ጠባብ ዓላማዎችን አንግበው፣ ሶርያውያንን የእምነት (የእስልምና) ቅርንጫፎችን፣ የጎሳ ልዩነቶችን፣ አካባቢያዊ ማንነቶችን ወዘተ…. መሰረት አድርገው መግደላቸው እና ሶርያንም ማውደማቸው አሁን በገሃድ የታወቀ ነገር ነው።

ከእነዚህ ቡድኖች አንዳንዶቹ ወደ አንድ ጎራ ተደራጅተው ኢስላሚክ ስቴት (IS) የተባለው ቡድን መሥርተው ሰዎችን በአደባባይ ማረዳቸው፣ ሰው ከነ ሕይወቱ ማቃጠላቸው፣ በሰዎች አንገት ላይ ፈንጅ አስረው ማፈንዳታቸው፣ ሰዎችን በፍርግርግ የብረት ጎጆ ውስጥ ቆልፈው ወደ ውሃ ውስጥ እያሰመጡ መግደላቸው ወዘተ…ታሪክ የማይረሳቸው አጸያፊ የሽብር ተግባሮቻቸው ናቸው።

የሶርያ ኢንደስትሪዎች፣ ታሪካዊ ቦታዎች፣ ከተሞች፣ መንደሮችና የተለዩና ድንቅ ናቸው የተባሉ የእስልምና መስጊዶች በፈንጅ የወደሙትም በእነዚህ ከአሜሪካ፣ ከአውሮፓ፣ ከዓረብና በሙስሊም አገራት በመጡ አክራሪ አሸባሪዎች ነው። እናም ሶርያ በቅጥረኞች ወድማለች። ለዚህ ውድመት ደግሞ የምዕራባውያኑ እገዛ በጣም ሰፊ ነው። ይህ የምዕራባውኑ እገዛ የተጀመረው የአሜሪካና የፈረንሳይ አምባሳደሮች ሶርያ ውስጥ ሆነው ሶርያን ከበጠበጡበት ጊዜ ጀምሮ ነው።

የሶርያ መንግሥት ለአገራቸው በጽኑ በቆሙ ሶርያውያን መራር ተጋድሎ፣ ከኢራንና ከሩሲያ እንዲሁም ከሂዝቦላህ ባገኘው ዕርዳታ ቅጥረኞችን እና አሸባሪዎችን ሲያሸንፍ፣ አሜሪካና አውሮፓ ወደ ሶርያ ሲሄዱ በዝምታ ያይዋቸውን ዜጎቻቸውንና ጥገኞቻቸውን መልሰው ላለመቀበል የፈጠሩት ንትርክ የሚዘነጋ አይደለም።

አሜሪካና አውሮፓ በተለይም በእንግሊዝ አገር ተቀምጠው ‘የሶርያ ዲሞክረሲያዊ ሃይሎች’ አና ሌሎችን የሶርያውያን የሚባሉ የሰብዓዊ መብት፣ ዲሞክራሲ፣ ነጸ ፕረስ ጠበቃ ነን ባይ ሶርያውያን ከምዕራባውያኑ ለሚያገኙት ጥቅም ሲሉ አገራቸውን አውድመዋል። ወገኖቻውን አስጨርሰዋል። ሶርያ ግን እያሸነፈች ነው። ሶርያ እያንሰራራች ነው።

ይህን ታሪክ መዘከር ያስፈለገው በአዲሰ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ በዕለተ ረቡዕ (መጋቢት 9/2012 ምሸት ላይ) የሰጠው መግለጫ ‘ኤምባሲው ወዴት እየሄደ ነው?!’ የሚል ጥያቄን በብዙዎች ዘንድ ስላጫረ ነው። ኤምባሲው የውጭ ዜጎች ጥቃት እየደረሰባቸው መሆኑን በመግለጽ የውጭ ዜጎች እንዲጠነቀቁ አሳስቧል።

የኤምባሲው መግለጫ ኮሮናን ያመጡብን የውጭ ዜጎች ናቸው በሚል የውጭ ዜጎች ምራቅ እየተተፋባቸው፣ ድንጋይ እየተወረወረባቸው፣ ማሳድድ እያጋጠማቸውና ለድብድብ የሚጋበዝ እየበዛባቸው፣ በየደረሱበት እየተሰደቡ መሆኑን፣ የታክሲ አገልግሎት እየተነፈጉ እንደሆነ ወዘተ…. የሚገልጽ ነው። ለበሽታው ብዙም መጨነቅና መደናገጥ በማይታይበት በዚህ ወቅት፣ ይህን የመሰለ መግለጫ መሰጠቱ አስገራሚና አሳሳቢ ነው።

መንግሥትም ሆነ የኤምባሲው ማኅበረሰብ በጽሞናና በጥልቀት ነገሩን ሊመረምሩት ይገባል። ማን? ለምን? መቼ? ወዘተ… ተጣርቶ፣ በሕመሙ ጋር በተያያዘ ይህን የመሰለ ድርጊት የሚፈጽሙ ካሉ ነገራቸው ከራሳቸው እንጂ ከኢትዮጵያዊ ጉዳይ የመነጨ አይደለምና አቁሙ ሊባሉ ይገባል። ነገር ግን ሌላም ጥርጣሬ አለ።

ይህ የኤምባሲው መግለጫ በአሃዱ ኤፍ ላይ ጭምር በሚስተጋቡት በቢቢሲና በቪኦኤ የአማርኛ ፕሮግራሞች ላይ በጩኸት ነው የተነገረው። የቪኦኤ አማርኛው ዜና አንባቢ ነገሩን ጋጠወጥነት ነው፣ ልቅነት ነው እያለ አጋግሎታል። ይህን ተሰደብን የሚል ዜና ብዙዎች ከሕዳሴው ግድብ ውዝግብ ጋር በተያያዘ አሜሪካውያን ያጋጠማቸውን አንዳንድ ፍጥጫ፣ ዓለም ዐቀፍ መልክ ለማሰጠትና ከሰብዓዊነት መጉደል ጋር በማያያዝ ኢትዮጵያን ለማሳጣት ሙከራ እየተደረገ ነው ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል።

አዎ! ማንኛውም ጤነኛ ኢትዮጵያዊ ከአሜሪካዊ ሰው ጋር ተገናኝቶ ግድቡን በሚመለከት አሜሪካ ልዘዛችሁ ስለማለትዋ ወሬ ከተነሳ “ጎሽ!” ብሎ የአሜሪካን አካሄድ ያደንቃል ተብሎ አይጠበቅም። ይህ ደግሞ የመጣው ይምጣ እንጅ አታዙንም ወይም ለጣሊያን እንዳልተንበረከክነው ሁሉ ለእናንተም አንሰንፍም ወይም ከአገራችን ውጡልን ወዘተ…. የሚሉ አነጋገሮችን አስከትሎ ሊሆን ይችላል።

ይህ እንደ ጥላቻ ተቆጥሮ፣ ጥላቻው ለአሜሪካውያን ብቻ ሳይሆን ለነጮች እንደሆነና ዓለም ዐቀፍ እንደሆነ ተደርጎ ይታይ ዘንድ ታስቦ፣ በኢትዮጵያውያን ልብ ኢሰብዓዊነት የሰፈነ ለማስመሰልም ከወቅቱ በሽታ ጋር እንዲያያዝ የተደረገ የተንኮል አካሄድ መስሎ እየታየ ነው። ይህ ከሆነ ደግሞ በሶርያ እንደታየው የኤምባሲው ትንኮሳ ቀጣይ፣ የውጭና የውስጥ ቅጥረኞችን የሚያሰልፍ፣ ሥልጣንና ዶላር የጠማቸውን ወገኖችንም አንዳች ጥቅም እናገኛለን በሚል ተስፋ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያውያን ላይ ለማነሳሳት ጭምር እስኪሆን የሚዘልቅ ሊሆን ይችላል።

ስለዚህ በመጀመሪያ እንደ አሃዱ ኤፍ ኤም ዓይነት የፈረንጅ ወሬ እየተቀበሉ እንደወረደ የሚያስተጋቡ መገናኛ ብዙኀን፣ ኢትዮጵያን ወይም መንግሥትን አሜሪካ ታፈርስልንና ጥቅም እናገኛለን ብለው ተስፋ የሚያደርጉ ግለሰቦችና ቡድኖች ወዘተ…. ቆም ብለው ሊያስቡበት ይገባል። በእግረ መንገድም ለአሜሪካ ድምጽ፣ ለዶቸቨለ፣ ለቢቢሲ እና ለሌሎችም የምዕራቡ ዓለም ተቋማት ወዘተ.. ተቀጥረው የሚሠሩ ወገኖች ግብግብ ከተጀመረ ዘርዓይ ደረሶች እንደሚወለዱ ታሳቢ በማድረግ ከመስመር እንዳያልፉ አደራ ማለት ተገቢ ነው።

ከወዲህ ደግሞ የተገኘን የውጭ ዜጋ አሜሪካውንንም ቢሆን በግል የሚተናኮሉ ጥቂት በጣም ጥቂት ሊኖሩ ስለሚችሉ፣ የኢትዮጵያዊነት ወግና ባህል ብቻ ሳይሆን ሕጋችንም ይህን ይከለክላልና እንጠንቀቅ።

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com