የተግባር ሙግት ጉራ ብቻ! ወሬ ብቻ!

Views: 226

ሙግትና ክርክር፣ ሰዎችን በሐሳብ ለመርታትና በጎ የሚሉትን ሐሳብ ለማስረጽ መሞከር ተገቢ ድርጊት ነው። በሠለጠነ ዓለምም መነጋገርና መደማመጥ አንዱ መፍትሔ ማምጫ መንገድ ሆኖ ያገለግላል። በአንጻሩ ደግሞ ንግግርና ወሬ ላይ ብቻ ችክ ማለትም ደስ አይልም። ‹አቀብሉኝ! አቀብሉኝ!› ከማለት ተነስቶ መውሰድ የሚባል አማራጭ እንዳለ ማስታወስ ያስፈልጋል።

የሴቶች የመብትና የእኩልነት ጥያቄ ላይም አንዳንዴ ከንግግርና ወሬ ያልዘለለ የሰፋና አሰልቺ ክርክር እናያለን። አግባብ አይደለም አልልም፣ እንዳልኩት መነጋገር መፍትሔ ያመጣል። ግን ደግሞ ተግባር ከሌለው ምንም ዋጋ የለውም።

የኢትዮጵያ የሕግ ባለሞያ ሴቶች ማኅበር የምሥረታው ሰሞን እንዲህ ከወሬ ያለፈ የተግባር ሥራዎችን በስኬትና በጉልህ ይሠራ ነበር። ‹ጥፋት ያጠፉ ሰዎች በአግባቡ ይቀጡ!› ብሎ ከመጮኽ አልፎ፣ ሴት የሕግ ባለሞያዎች በጥብቅና ቆመው ፍትኅ እንዲሰፍን ሲያደርጉ ታይተዋል። የተዘጋና የተዘነጋ፣ አቧራ የጠጣ የክስ መዝገብን አንስተው፣ ለንጹሐንና ለተበደሉ ሴቶች ቆመው ሲያሸንፉም ተሰምቷል። ይህ ከወሬ የዘለለ ለውጥ ነው።

‹የሎው ሙቭመንት› የሚባለው በዩኒቨርስቲ የሚንቀሳቀሰው ማኅበር፣ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለሚገኙና ችግር ጸንቶ ለትምህርታቸው ፈተና ለጋረጠባቸው ሴቶች ድጋፋቸውን ያደርጋሉ። ይህ ከወሬ ያለፈ ተግባር ነው።

የወር አበባ በሚመጣባቸው የየወራቱ ቀናት ትምህርት ቤት የማይሄዱ ሴት ተማሪዎች ጥቂት አልነበሩም። ‹መንግሥት እኩል የትምህርት እድል መስጠት አለበት!› የሚል ብዙ መፈክርና ክርክር፣ ሙግትና ትግል ተደርጓል፤ በቃል ብቻ። እንደ ፍሬወይኒ መብራኽቱ ያሉ ሴቶች ደግሞ ንጽህና መጠበቂያውን ሠርተው፣ በነጻ እንዲሰጥ ስፖንሰር አፈላልገው ተአምር የሠሩ ይገኛሉ። ይህ ተግባር ይባላል።

በፊስቱላ ሕመም የሚሰቃዩ ሴቶች ጥቂት አልነበሩም። ‹ያለእድሜ ጋብቻ ይቁም!!› የሚሉ ጩኸቶችም ጥቂት አልነበሩም። ሁሌም እንደ አዲስ በፊስቱላ ሕመም ለተያዘች ሴት ከንፈር እየተመጠጠ፣ ሌላዋ እንዳትያዝ ይጮኻል። ለውጥ ግን አልመጣም። ዶክተር ካትሪን ሐምሊን ከባለቤታቸው ጋር ሲመጡ፣ ለውጡን ይዘው መጡ። ሁሉም ጩኸቱ ላይ አተኩሮ ትኩረት የነፈጋቸው፣ መጠጊያ ያጡና በሀፍረት ውስጥ የተጣሉ ሴቶችን ዶክተሯ ቀና አደረጉ። ሥነ ተዋልዶ ላይ ሥልጠና እንዲሰጥና ማዋለጃዎች እንዲኖሩ ደከሙ፣ አደረጉትም። ይህ ከእልፍ ዘመናት ንግግር በላይ ድል የሚያደርግ ተግባር ነው።

ለሴቶች ግርዛት መፍትሔ ይምጣ ተብሎ ኡኡ ተባለ። መገናኛ ብዙኀን ጩኸቱን አስተጋቡ። ማን ልጓሙን ይያዘው ተባለ። አንድ ቀን ከከንባታ የወጣችው የማለዳ ፀሕይ ዶክተር ቦጋለች ገብሬን ይዛ መጣች። በግለሰብ ደረጃ ባደረጉት ጥረት በአካባቢያቸው የሴት ልጅ ግርዛትን ሙሉ ለሙሉ አስቆሙ። ይህ ከሁሉም የላቀ ሥራ ነው።

ወሬ ብቻ! ጉራ ብቻ! አንሁን። የለውጥ ሰው እንሁን። ለነፍሳቸው የእረፍት ስፍራን ይስጥልንና፣ ዶክተር ካትሪን እንዲሁም ቦጌን አልያም አሁንም በንቃት እየሠሩ ያሉትን ፍሬወይኒን አልያም ማኅበራቱን እንድንሆን አይጠበቅብንም። ተጣምረንና በጋራ ግን ተግባር ላይ ማተኮር አለብን። ይህም ለሴቶች እኩልነትና መብት ከወሬ የዘለለ ተግባር ሆኖ ይመዘገባል። ለሌሎች ባናደርግ እንኳ እንደሴት በየግል የምናስመዘግበው ውጤትና መልካም አረአያነት ተምሳሌት ይሆናል።

ተናጋሪና ተሟጋች ያስፈልጋል። ግን ሥራ ከሌለበት ከንቱ ሆኖ ያልፋል። ለጥቁሮች መብት ብዙ ከጮኹ ሰዎች ይልቅ፣ ‹ከተቀመጥኩበት አልነሳም› ያለችው ሮዛ ፓርክስ የማይረሳ ታሪክ ሠርታለች። አዎን! እናውራ! በመነጋገር መፍትሔ አለ። ተግባር ከሌለን ግን ምን ዋጋ አለ?
ስለሴቶች መብትና ጥቅም በተለያየ ሁኔታና በየአቅማቸው በተግባር ለሠሩ ሴቶች ግብር ይገባል!
ሊድያ ተስፋዬ

ቅጽ 2 ቁጥር 72 መጋቢት 12 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com