ዜጎች ሊሟሉላቸው ከሚገቡ መሠረታዊ መብቶች ውስጥ ትምህርት ከቀዳሚዎቹ ተርታ የሚሠለፍ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ፣ ልጆች በትምርታቸው ጠንካራ እና ስኬታማ ሆነው ከራሳቸው ባሻገር ለቤተሠብ፣ ለማኅበረሠብ፣ እንዲሁም ለአገር ጠቃሚ ትውልድ እንዲሆኑ ከተፈለገ፣ መሠረታዊ የሆነ ትምህርት በአግባቡ የሚያገኙበት ኹኔታ ከመጀመሪያ እስከ ከፍተኛ ደረጃ ትምህርት ድረስ ሊሟላላቸው ይገባል፡፡
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥት፣ የኢኮኖሚ አቅም በፈቀደ መጠን መንግሥት ለአካል ጉዳተኞች ድጋፍ የመስጠት፣ የማስተማር እና ሌሎች ኃላፊነቶች የመወጣት ግደታ እንዳለበት ይደነግጋል።
የተባበሩት መንግሥታት አባል አገራት፣ ዓለም ዓቀፍ ድንጋጌዎችን በየአገሮቻቸው ሕገ-መንግሥት አካተውና አጸድቀው፣ ማንኛውም አካል ጉዳተኛ የመማር መብት እንዳለው እና መንግሥት፣ ማኅበረሠቡ፣ ሲቪክ ማኅበራትና ወላጆች ለአካል ጉዳተኞች ምቹ ኹኔታ የመፍጠር ወይም የማመቻቸት ግዴታ አለባቸው።
ከዚህ በተጨማሪ፣ እንቅፋት የሆኑ ክፍተቶችን በመሙላት ኹሉም ባለ ድርሻ አካላት አካል ጉዳተኞች የመማር ዕድል እንዲያገኙ ማስቻል ግድ ይላቸዋል።
ባለፈው ዓመት በእንግሊዟ ዋና ከተማ ለንደን ዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ጉባኤ በተካሔደበት ወቅት፣ በጉባኤው ላይ ከተነሱ ነጥቦች አንዱ የአካል ጉዳተኞች ቁጥር አለመታወቁ ነው። ከዓመታት በፊት በወጣው የተባበሩት መንግሥታት የአካል ጉዳተኞች ሪፖርት መሠረት፣ በዓለም ላይ ካሉት 1 ቢሊዮን አካል ጉዳተኞች መካከል፣ 15 በመቶዎቹ በታዳጊ አገራት እንዳሉ እና ከእነዚህ ውስጥም 15 በመቶ የሚሆኑት በኢትዮጵያ እንደሚገኙ መረጃው ይጠቁማል።
ኢትዮጵያ ውስጥ በአካል ጉዳተኝነት ላይ መሠራት ያሉባቸው ብዙ ነገሮች እንዳሉ በሠብዓዊ መብት ተሟጋቾች የሚነገር ሲሆን፣ ከነዚህም ውስጥ ግንዛቤ መፍጠር እና ለአካል ጉዳተኞች የመማር ዕድልን ማመቻቸት በዋነኝነት ተጠቃሾች ናቸው።
አካል ጉዳተኞች መማር ካልቻሉ እና የሚማሩበትን ኹኔታ ማመቻቸት ካልተቻለ፣ ማኅበረሠቡ ምርታማ እና ውጤታማ ካለመሆን ባሻገር፣ ለጥገኝነት የሚዳረግበት ዕድል ሠፊ እንደሚሆን ለማንም አያጠያይቅም።
ትምህርት የሚያስገኘው ትሩፋት የጎላ በመሆኑ፣ የኢትዮጵያ ኹኔታ በፈቀደ መጠን አካል ጉዳተኞች በእኩልነት ትምርህት ሊያገኙ እንደሚገባ በየጊዜው የኢትዮጵያ የአካል ጉዳተኞች ማኅበር ይናገራል።
ኢትዮጵያ፣ “ትምህርት ለሁሉም” የሚል ዘመቻ እንዳላት እና ኹሉም አካል ጉዳተኞች የትምህርት ተጠቃሚ መሆን እንዳለባቸው ቢደነግግም፣ ተግባሩ መሬት ላይ ባለመውረዱ አፈጻጸሙ ከፍተኛ ክፍተት አለበት ያለው ማኅበሩ ነው።
ኢትዮጵያ፣ አካል ጉዳተኞችን የተመለከተ ዓለም አቀፍ ድንጋጌ የአገሪቱ ሕግ አካል አድርጋ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተቀብላና አስጸድቃ ሥራ ላይ ማዋሏ ይታወቃል።
ነገር ግን፣ የአካል ጉዳተኞች የትምህርት ኹኔታ እንደ ኹለተኛ ደረጃ መብት የሚታይ ሆኗል ማለት ይቻላል፡፡ በዚህም አካል ጉዳተኞች ነፃና ፍትሐዊ ትምህርት፣ እንዲሁም ዕርዳታ አያገኙም፡፡ ከዚያም ባለፈ በትምህርት ቤቱ ማኅበረሠብ፣ በመምህራን እና በወላጆች ጭምር ተገቢ ድጋፍ የማያገኙበት ኹኔታ ይታያል።
ሶፊያ መሐመድ የአዲስ አበባ ኗሪ ስትሆን፣ የ 14 ዓመት ወንድ ልጇ ባጋጠመው አደጋ ምክንያት እግሮቹ ላይ ጉዳት ደርሶበት ከቦታ ቦታ በ‹ዊልቸር› ለመንቀሳቀስ የተገደደ እንደሆነ ትናገራለች።
ልጇ ጃፈር ቃሲም ይባላል። በአዲስ አበባ በቦሌ ክፍለ ከተማ፣ ቦሌ አዲስ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የአራተኛ ክፍል ተማሪ ነው።
ጃፈርን በአምስት ዓመቱ ትምህርት ቤት እንዳስገባችው ያነሳችው ሶፊያ፣ ከመኖሪያ ቤት እስከ ትምህርት ቤት ከማድረስ ጀምሮ፣ የትምህርት ቁሳቁስ እና አልባሳትን በሟሟላት ኃላፊነቷን እየተወጣች እንደምትገኝ አስረድታለች።
ጃፈር የመማር ፍላጎት ያለው፣ ዕውቀት ገብይቶ ለቤተሰቡና ለአገሩ መስዋዕት እንደሚከፍል ኹሌም የሚያወሳ ልጅ መሆኑን ትናገራለች። ነገር ግን፣ የሚማርበት ትምህርት ቤት ክፍሎች ምቹ አለመሆን ለዓላማው እንቅፋት እንደሆነበት ጠቅሳለች።
ሶፊያ አክላም፣ ልጄ ውጤቱ ጥሩ ሁኖ ሳለና ወደ ቀጣዩ ክፍል መዘዋወር ቢኖርበትም፣ በትምህርት ቤቱ ማን አለብኝነት ወደ ቀጣዩ ክፍል መዘዋወር የሚችልባቸው ዕድሎች ባክነውበታል ትላለች፡፡ ወደ ቀጣዩ የክፍል ደረጃ ሳይሸጋገር በተለያዩ የክፍል ደረጃ ላይ ለአምስት ጊዜ እንዲቆይ ተገዷል ብላለች።
በተጨማሪም፣ በያዝነው ዓመት የመጀመሪያውን መንፈቅ የትምህርት ማጠቃለያ (ሴሚስተር) ፈተና እንዳይወስድ በትምህርት ቤቱ ተከልክሏል ያለችው ሶፊያ፣ ፈተናውን እንዳይወስድ ለምን እንደተከለከለ ለትምህርት ቤቱ ጥያቄ ብታቀርብም ምላሽ እንዳልተሠጣት በማንሳት ቅሬታዋን ለአዲስ ማለዳ ገልጻለች።
የቦሌ አዲስ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህርና የልዩ ፍላጎት ባለሙያ የሆኑት ግሩም ጉልላት በበኩላቸው፣ ጃፈር በትምህርት ቤቱ ተመዝግቦ ትምህርት መከታተል ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በመምህርነት ሙያ ላይ እንደሚገኙ በመጥቀስ፣ ተማሪ ጃፈር በሚወስዳቸው ፈተናዎች ጥሩ ውጤት እያስመዘገበ በተለያዩ የክፍል ደረጃዎች ለአምስት ዓመት ሳይዘዋወር ቀርቷል በሚለው ቅሬታ ላይ አልስማማም ብለዋል። ግሩም አክለውም፣ ቦሌ አዲስ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ለአካል ጉዳተኞች በሚመች ኹኔታ ትምህርት እየሠጠ መሆኑን አንስተዋል።
በተያዘው ዓመት፣ አንድ ሴት መምህርት ተማሪ ጃፈር በሠዓቱ በትምህርት ቤቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ አለመገኘቱን ተከትሎ፣ ሌሎች ተማሪዎችን ሰብስባ ፎቅ ላይ ትምህርት እየሠጠች በነበረችበት ወቅት፣ ጃፈር አርፍዶ ስለመምጣቱን መረጃ እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡ በዚህም በዕለቱ አንድ የትምህርት ዓይነት በሠዓቱ ሳይከታተል እንዳለፈው አስተባባሪው ጠቅሠው፣ ትምህርት ቤቱ ለመምህሯ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ መጻፉንም አስረድተዋል።
ከዚህ ባለፈ ግን፣ ጃፈር በያዝነው የትምህርት ዓመት የመጀመሪያ ሴሚስተር ፈተና እንዳለፈው እንደማያውቁ እና ሶፊያም ምንም ዓይነት ቅሬታ ለትምህርት ቤቱ አቅርባ እንደማታውቅ ገልጸዋል።
አያይዘውም፣ ተማሪ ጃፈር የ2014 የመጀመሪያ ሴሚስተር ፈተና መፈተኑ ወይም አለመፈተኑ ከተረጋገጠ በኋላ፣ ትምህርት ቤቱ ውሳኔ እንደሚያሳልፍ መምህር ግሩም ጠቁመዋል።
የአካል ጉዳተኞች መብት ፌድሬሽን አማካሪ ይልቃል አባየ፣ ኢትዮጵያ የአካታች ትምህርት መመሪያ እንደምትከተል እና የአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች ከማንኛውም ተማሪ ጋር ተካተው እንዲማሩ የሚደነግግ ፖሊሲ ቢኖራትም፣ ፖሊሲው ተግባራዊ እንዳልሆነ የሚያሳዩ የተለያዩ ጥናቶች አሉን ብለዋል።
በዚህም፣ በመንግሥት በኩል አስፈላጊው በጀት አለመመደቡ፣ የግንዛቤ ክፍተት መኖሩ፣ አስገዳጅ የሆነ የአካታች ትምህርት ሕግ አለመኖሩ፣ በቂ የመማሪያና ማስተማሪያ ቁሳቁስ አለመገኘቱ ለተግባራዊነቱ እንከን መሆናቸውን አሰረድተዋል።
ይልቃል አክለውም፣ አሁን ላይ ከመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት አንስቶ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ድረስ አካል ጉዳተኞች ትምህርት የሚያገኙበት ዕድል እንዲሠፋ ከማድረግ ባለፈ፣ መሬት ላይ ወርዶ እንዲተገበር የሚረዳ ረቂቅ ሕግ እየተዘጋጀ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የህ ሕግ ሲወጣ ደግሞ፣ የአካል ጉዳተኞችን የመማር መብት የማያከብሩ አካላትን በአስተዳደራዊና በወንጀለኛ መቅጫ ሕጎች ተጠያቂ እንደሚያደርግ የጠቀሱት አስተባባሪው፣ የተዘጋጀው የሕግ ረቂቅ ተቀባይነት የሚያገኝ ከሆነ የአካል ጉዳተኞችን መብት ለማስከበር ያለው ድርሻ ጉልህ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የሕግ ባለሙያው ጥጋቡ ደሳለኝ በበኩላቸው፣ አካል ጉዳተኞች ወደ ትምህርት ቤት እንዳይሔዱ፣ ትምርህታቸውንም እንዳይከታተሉ የሚገደቡበት ኹኔታ እየተባባሰ መጥቷል ብለዋል።
ከዚህ ባሻገር፣ ቤተሰቦች እና አሳዳጊዎች አካል ጉዳተኛ ተማሪዎችን ትምህርት ቤት ወስዶ የማያስመዘግቡበት ኹኔታ እንዳለ ጥጋቡ ጠቅሠው፣ ውጣ ውረዶችን ተቋቁመው ትምህርት መከታተል የሚጀምሩ አካል ጉዳተኞች ደግሞ ምድር ላይ ባሉ ማስተማሪያ ክፍሎች መማር እንዲችሉ ማመቻቸት ተገቢ ሆኖ ሳለ፣ በሕንጻዎች ፎቅ ላይ እንዲማሩ የሚገደዱበት ዕድል አለ ይላሉ።
የትምህርት ተቋማትም፣ አካል ጉዳተኛ ተማሪዎችን ግምት ውስጥ ያለማስገባት፣ ያለመረዳት እና ለቤተሰቦቻቸው ጉዳዩን የመተው ኹናቴ እየተስተዋለባቸው መምጣቱን ጠቅሰዋል።
በትምህርት ተቋማት የትምህርት ቁሳቁሶች በአግባቡ አይገኙም የሚሉት ጥጋቡ፣ ለአብነትም ለዐይነ ሥውራን ተማሪዎች በብሬል የተዘጋጀ ወይንም በድምፅ የተቀረጸ የትምህርት መርጃ ቁሳቁስ አለመኖር፣ የእግር ጉዳት ላለባቸው ተማሪዎች ዊልቸርና ተሽከርካሪዎች ያለማመቻቸት፣ መስማት ለተሳናቸው ተማሪዎች በተጨማሪነት የምልክት ቋንቋ የሚችሉ መምህራንን ያለመመደብ ኹኔታዎች ይታያሉ ባይ ናቸው።
ከአካል ጉዳተኞች ትምህርት ጋር በተገናኘ በሕገ መንግሥቱ የተጠቀሱ ሕጎች እየተጣሱ መሆናቸውን ከመጥቀስ ጎን ለጎን፣ አካል ጉዳተኞች ትምህርት የሚያገኙበትን ዕድል የማመቻቸት ድርሻ የኹሉም አካላት ግዴታ ነው ብለዋል።
መንግሥት የትምህርት ግብዓቶችን ማመቻቸት፣ ለመምህራንና ለትምህርት ቤት አመራሮች ሥልጠና መስጠት፣ አካል ጉዳተኞች ትምህርት ተቋማት ገብተው እንዲማሩ በየወቅቱ ዘመቻ ማድረግ፣ እና የአካል ጉዳተኛ ቤተሰቦች ወይም አሳዳጊዎች መረጃ እንዲያገኙ መሥራት እንዳለበት ጥጋቡ ተናግረዋል።
አክለውም፣ መንግሥት በግብርናውና በተለያዩ ዘርፎች ላይ ማኅበረሠቡን በተለይ አርሶ አደሩን የማብቃት ሥራ እንደሚሠራ ኹሉ፣ በአካል ጉዳትና ጉዳተኞችም ላይ ተከታታይነት ያለው ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ ሊያከናውን ይገባዋል ይላሉ።
አካል ጉዳተኞች የመማር፣ ፍትሐዊ አገልግሎት የማግኘት መብት በሕገ መንግሥቱ ከመቀመጡ ውጭ እንዳልተፈጸመ የሚያስረዱት ጥጋቡ፣ ይህንንም ለማስተካከልና ለውጥ ለማምጣት የመንግሥት ቁርጠኝነት፣ የባለ ድርሻ አካላት ተሳትፎ እና ርብርብ፣ የወላጆች ያልተገደበ ጥረት አስፈላጊ እንደሆነ ጠቁመዋል።
ቅጽ 4 ቁጥር 175 መጋቢት 3 2014



