መጠጥ ማብዛት በአንጎላችን ላይ የሚያስከትለው ተፅዕኖ

0
1585

መጠጥ መጥመቅ መቼ እንደተጀመረ ሳይንስ የሚገምተው ዘመን ከባለሙያ ባለሙያ ቢለያይም፣ ከኃይማኖታዊ የታሪክ መዛግብት መረዳት እንደሚቻለው ግን፣ የአዳም 10ኛ ትውልድ በነበረው ኖሕ ዘመን ተጠጥቶ ይሰከር እንደነበር ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ መረዳት ይቻላል።

ከ6ሺሕ ዓመት ገደማ በፊት እንደአሁኑ የተለያየ መጠጥ ይጠመቅ እንደነበር ባይታወቅም፣ የወይን ዘለላ ከማር ጋር ታሽቶ ለወር ታሽጎ ከተቀመጠ በኋላ፣ ውኹዱ ይጠጣ እንደነበር ይነገራል። ይህ ወይነጠጅ የሚባለው አስካሪ መጠጥ እንዳሁኑ ከወይን ወይም ከጠጅ ለየብቻ የሚጠመቅ ባይሆንም፣ አስካሪነቱ ተመሳሳይ መሆኑን መገመት አያስቸግርም። መጠጥ አጠማመቅን ለመጀመሪያ ጊዜ ማን አውቆ እንዳስተማረ በግልጽ ባይታወቅም፣ አንዳንድ ዛፎች በተፈጥሮ ፍሬዎቻቸው በስለው ወደ አልኮልነት ስለሚቀየሩ (ፈርመንት ስለሚያደርጉ) እነሱን የበሉ እንስሳትም ጭምር ይሰክራሉ። ይህ አስካሪነቱ በእንስሳቱ መወደዱን የሥነ-ተፈጥሮ አጥኚዎች ታዝበው ምክንያቱን ለማወቅ እየጣሩ ይገኛሉ።

መጠጥ ጥቅም ላይ የዋለበት ጊዜ ላይ ልዩነት ቢኖርም፣ እንደሚያሰክርና ያልተፈለገ ክፉ ነገርን እንደሚያሠራ ኹሉም ያውቃል። በማኅበረሠብ ደረጃ የተነቀፈና የተወገዘ ድርጊትን ሠዎች እንዲያደርጉ ይገፋፋል ድፍረትም ይሰጣል የሚባለው መጠጥ፣ በኹሉም የዓለማችን ክፍል የሚመረት ነው። በአማዞን ጫካ ተገልሎ የሚኖር ማኅበረሠብ እንኳን የተፈጥሮ አስካሪ ቅጠልና ቅርፊትን ጭምር እንደሚጠቀም ይታወቃል።

ከተለያዩ ፍሬዎች፣ ሰብሎች፣ አትክልቶችና ተክሎች የሚጠመቀው የአልኮል መጠጥ፣ እንደሕብረተሠቡ አመለካከትና ዕምነት የተለያየ ቦታ ይሠጠዋል። በአንዳንድ ማኅበረሠቦች ዘንድ ሕፃናት ሳይቀር እንዲጠጡ ይደረጋል። በሌላው ኃጢዓት በመደረጉ መያዝ ብቻ እንደከፍተኛ ወንጀል ይቆጠራል። አመለካከቱ ይለያይ እንጂ፣ የማያውቀውና ጉዳቱን የማይረዳ የለም ማለት ይቻላል። በተቃራኒው የበዓልና ድግስ ማድመቂያ፣ መጫወቻና ዘና መባያ ነው እየተባለ ጥቅሙ ሲዘረዘርም ይሠማል። “ሆድ ያባውን ብቅል ያወጣዋል” እየተባለ እንደምስጢር ማወጣጫ ከማገልገሉም በላይ፣ አዕምሮን ለመሳትም ሆነ ጭንቀትን ለመርሳት እንጠቀምበታለን የሚሉ በርካቶች ናቸው። ሕመምን ለማደንዘዣ፣ የሆድ ትላትልን ለማስወገጃ፣ ብርድን ለመቋቋሚያ፣ ለምግብ መፈጨትን ማገዣ፣ እንዲሁም ለእንቅልፍና ለቁንጫም እየተባለ ይወሠዳል።

ስለመጠጥ ጎጂነት ብዙ ማለት ቢቻልም፣ በአብዛኛው “እስካልበዛ ጥሩ ነው፣ አትስከሩ እንጂ አትጠጡ አልተባለም” እየተባለ ሲነገር ይደመጣል። መጠኑና ዓይነቱ እየተለየ ከዚህ በላይ አይሁን ተብሎ ከአስካሪነቱ አኳያ በሊትርም ይሁን በዓይነት ገደቡ ስለማይቀመጥ፣ ለአንዱ የሚያሰክረው ከሌላው ስለሚለያይም ወጥ የሆነ መስፈርት ማስቀመጥ አስቸጋሪ ነው። እንደመጠጥ ዓይነቱ ይህን ከዚህ በላይ አትጠጡ እያሉ እንደልማድ መጠኑን ከሠው ሠው ለይቶ ለመናገር አስቸጋሪ ቢሆንም፣ በደም ውስጥ ባለ የአልኮል መጠን እየተለካ ግን ጠጪው ይቀጣበታል። አሽከርካሪ በደሙ ውስጥ ከተፈቀደው በላይ የአልኮል መጠን እንዳይገኝበት ምን ያህል ብርጭቆም ሆነ ጠርሙስ መጠጣት እንዳለበት የተለየለት ነገር የለም።

መጠኑ ከሠው ሠው ይለያይ እንጂ በየቀኑ ሲደጋግሙት ይበቃ የነበረ መጠን እንደማያሠማ ይታወቃል። ይህ የሚወሠድ መጠን በብዙ ቦታዎች የብቃት መለኪያ እየተደረገ በቀላሉ የሰከረ ልምድ እንደሌለው ተደርጎ መቀለጃ ሲደረግም ይስተዋላል። የስካር መጠኑ ከሠው ሠው እንደልማዱ እንደመለያየቱ፣ ያስገኛል የሚባለው ጥቅምም ሆነ ያስከትላል የሚባለው ጉዳትም እንደሠዉ አመለካከት ይለያያል። ከማኅበረሠብ ማኅበረሠብ ጭምር ከፍተኛ የሆነ የአመለካከት ልዩነትን የሚያስተናግደው የአልኮል መጠጥ አጠቃቀም፣ በሳይንሱም የተለያየ ማስረጃ ሲቀርብለትና ሲቀርብበት ቆይቷል።

ከሠሞኑ ይፋ የተደረገ አንድ ጥናት እንደጠቆመው፣ መጠጥን ባያበዙም በየቀኑ አከታትለው የሚጠጡ ለአስተሳሰብ መዳከም እንደሚጋለጡ ነው። እስከዛሬ አነስተኛ መጠን በየቀኑ መውሰድ ጥሩ ነው የሚባለውን የባለሙያዎች ምክር ውድቅ ያደረገው ይህ ጥናት፣ ሠዎች የአንጎላቸው የማሠብ መጠን ቀስ በቀስ እየወረደባቸው እንዳይሄድ የሚጠጡበትን ጊዜና መጠን እንዲቀንሱ ያመላክታል ተብሏል። በአነስተኛ መጠን አልኮልን መጠጣት ለደም ዝውውር፣ ለምግብ መፈጨት፣ ለሆድ ዕቃዎች ጤናማነት አስተዋጽዖ አለው በሚል በተለያዩ ጊዜያት ሲነገር የነበረ የተለያየ ምክርን ውድቅ የሚያደርገው ይህ ግኝት፣ መካከለኛ ጠጪና አነስተኛ ጠጪዎችንም የሚመለከት ነው።

‹ኔቸር ኮሚኒኬሽንስ› መጽሔት ላይ ይፋ የተደረገው ይህ የጥናት ውጤት፣ 30 ሺሕ ሠዎችን እንደናሙና በመውሰድ የተካሄደ ነው። በቀን አንድ ወይም ኹለት ብቻ የሚጠጡ ሠዎች በአዕምሯቸው ላይ የሚመጣባቸው የጉዳት መጠን በኹለት ዓመት እንደማርጀት ነው ተብሏል። ከዚህ በላይ የሚጠጡት ደግሞ እንደሚጠቀሙት መጠን አንጎላቸው ላይ የሚያስከትለው ችግር ይጨምራል ሲሉ ተመራማሪዎቹ አሳውቀዋል። እንዲህ ዓይነት ጠጪዎች ላይ የሚታየው ለውጥ፣ የማስታወስ ብቃት መቀነስን ብቻ ሳይሆን የአንጎል ቅርፅ እንዲቀየርና መጠኑ እንዲኮማተር ያደርገዋል ብለዋል።

በአንጎላችን ላይ የሚያስከትለው ለውጥ አብዝተው ለሚጠጡ ብቻ ሳይሆን አንድ ብርጭቆ ወይንን ወይም አንድ ቢራ ብቻ የሚጎነጩ ላይም ቢሆን፣ መጠኑ ይለያይ እንጂ አዕምሮ ላይ በጊዜ ሒደት ለውጥ ማምጣቱ እንደማይቀር ሳይንቲስቶቹ ምልከታቸውን አስቀምጠዋል።

በምርምር ጉዳት እንደሚያመጣ አውቀናል ያሉት የአልኮል መጠን፣ በመንግሥትም ሆኑ በተለያዩ አካላት ከሚቀመጠው የጎጂነት ገደብ በጣም አነስተኛ ስለሆነ፣ በተለምዶ ይቀመጡ የነበሩ መስፈርቶችም ሆኑ አመለካከቶች እንደገና መቃኘት እንዳለባቸው ተናግረዋል። ከዚህ ቀደም ከዚህ ከአሁኑ ግኝት የሚቃረኑ የጥናት ውጤቶች ይፋ ሲደረጉ ቆይተዋል። ከእነዚህም መካከል ዕድሜያቸው የገፋ ሠዎች አልኮል በመጠኑ ቢጠቀሙ እንደሚጠቅማቸው የሚናገር ነው። ይህን መሠል ጥናቶች ውድቅ ለማድረግ የአሁኑ ዓይነት ጥናት በሠፊው በርካታ ናሙናዎችን አካቶ፣ እንደዕድሜ ልዩነቱ አለያይቶ ማካሄድ እንደሚገባ ተጠቁሟል።

አሁን ይፋ የተደረገው ጥናት የ30 ሺሕዎቹን ሠዎች መረጃ እንደዕድሜ ልዩነታቸው፣ እንደፆታቸው፣ እንደሲጋራና ሌሎች ደባል ሱስ አጠቃቀማቸው፣ እንዲሁም ያለባቸውን የጤና ዕክልም ሆነ ያለፈ ታሪካቸው መረጃ በመጠቀም ከአዕምሯቸው መጠንና ተግባር ጋር በንጽጽር የተጠናቀረበት እንደሆነ አጥኚዎቹ ተናግረዋል። የአዕምሮ መረጃቸው የተከማቸ ሠዎችን በመለየት፣ ለእያንዳንዳቸው መጠይቅ በማዘጋጀት የአልኮል አጠቃቀማቸውን በቡድን በማስቀመጥ የተካሔደ ጥናት ነው። ምንም አልኮል ከማይቀምሱት ጀምሮ አብዝተው የሚጠጡትን በመለየት የሠጡትን መረጃ ከአንጎላቸው ኹኔታ ጋር በማነጻጸር ልዩነቱን መዝግበዋል። እንደአልኮል ተጠቃሚነታቸው መጠን የአዕምሯቸው ለውጥም እንደሚጨምር ማረጋገጥ ችለናል ያሉ ሲሆን፣ አብዝተው የሚጠቀሙትን ባየን ቁጥር ከሌላው የተለየ የአዕምሮ መዳከም ይታይባቸዋል። ማስታወስን የመሳሰሉ አንጎላችን የሚከውናቸው ተግባራት ይበልጥ በሚጠጡት ላይ ከመቀነሱ በላይ፣ ‹ግሬይና ዋይት ማተር› እየተባለ የሚታወቀው የአንጎል ክፍልም እንደሚቀንስ መመልከት መቻላቸውን ተመራማሪዎቹ አሳውቀዋል። ቀናትን እየዘለሉ የሚጠጡ ላይ ያን ያህል ለውጥ የለም የተባለ ሲሆን፣ አነስተኛ መጠን ቢሆንም፣ በየቀኑ የሚወስዱት ላይ ግን ለውጡን ማየት እንደሚቻል ጠቁመዋል።

ይህ ጥናት ከቶውንም አትጠጡ ለማለት ሳይሆን አታብዙ ለማለት ነው ያሉት ተመራማሪዎቹ፣ ቀስ በቀስ እንደሸመገለ ሠው እንዳንሆን መጠናችንን ማወቅ ያስፈልገናል ይላሉ። በተለይ አብዝተው ለሚጠጡ መልዕክቱ አስፈላጊ በመሆኑ፣ ከለመዱት ቢያንስ የመጨረሻዋን መለኪያ በመቀነስ ወደማይጎዳው ደረጃ መሸጋገር ይቻላቸዋል ሲሉ መክረዋል።

ስለመጠጥ ማብዛት ብዙ የተሠሩ ምርምሮች ቢኖሩም፣ በኢትዮጵያ ውስጥ በባህላዊ መንገድ የሚያመጣውን የአስተሳሰብ ለውጥ ለማስረዳት የሞከሩ ንጉሠ ነገሥት ነበሩ። በ1708 የነገሡት አፄ ዳዊት አሁን ሠንበቴ እንደሚባለው ከገበሬ ወዳጆቻቸው ጋር ይጠጡ እንደነበር ይነገራል። ከሠው ሳይወስድ ለፍቶ በጉልበቱ ከሚያድር ጋር መወዳጀት ይሻለኛል ብለው ለረጅም ጊዜ ከተቀራረቧቸው ጋር ሲጠጡ አንዱን ቀን ጨዋታው ይግልና አንድ ሞቅ ያለው ገበሬ ተነስቶ በጥፊ ያጮላቸዋል። ይህን የተመለከቱ ጋሻ ጃግሬዎቻቸው ይዘን ካልገደልነው ሲሉ፣ ጓደኛቸው ስለነበረ ለምነውለት ቀኑን ከግርፊያና ዱላ ያድኑታል። ምድራዊ የበላይ የሌለባቸው ቢሆኑም፣ ንጉሥም ቢሆኑ ሕግን መጣስ አይችሉም ተብለው በፍትኃ ነገሥቱ መሠረት ንጉሥን የነካ እጁን ይቆረጥ ስለሚል ገበሬ ወዳጆን ማስጣል አይችሉም ተብለው ሸንጎ ይሠየማል።

በዕለቱ ግን፣ መኳንንቱ ተቀምጠው ሲጠባበቁ ገበሬው ታስሮ ከመምጣቱ በፊት ንጉሡ በሠንሰለት የታሠረ አንበሳ ከጉረኖው ውስጥ እንዲመጣ አስደርገው በመኳንንቱ ፊት እንዲቀመጥ ያስደርጋሉ። ቀጥሎ ግመሬ ዝንጀሮ እንዲሁ ታሥሮ እንዲገባ ያስደርጋሉ። ዝንጀሮው ገና አንበሳውን እንዳየው በድንጋጤ ብርክ ይዞት መንቀጥቀጥ ሲጀምር አውጡት ይላሉ። ግራ የገባቸው መኳንንት ራቅ ብሎ እንዲያዩት እያስደረጉ ለዝንጀሮው እስኪበቃው ጠጅና ጠላ እንዲጠጣ ያስደርጋሉ። ትንሽ አቆይተው ጭንቅላቱ ላይ መጠጡ እንዲወጣበት ካስደረጉ በኋላ መልሰው አንበሳው ፊት ያስቀምጡታል። ያ መጀመሪያ በፍርሃት ሊሸና የነበረው ዝንጀሮ አሁን ጠባዩን ቀይሮ ወደአንበሳው ካልተጠጋሁ ብሎ፣ አንበሳውን ለመግደል በሚመስል ሙከራ ያዙን ልቀቁኝ ሲል ለመኳኳንንቱ ያሳያሉ። መልዕክቱን በቀላሉ እንዲረዱ ካደረጉ በኋላ፣ ወዳጄን መጠጡ እንደዝንጀሮው አሳስቶት እንጂ በእኔ ላይ ክፉ አያስብም፣ እንዲያውም እናንተ ለእኔ ካሰባችሁት በላይ ዕድሜና ጤና የሚመኝልኝ እሱ ነው ብለው በነፃ እንዲሰናበት ማድረጋቸው በታሪክ ተመዝግቧል።


ቅጽ 4 ቁጥር 175 መጋቢት 3 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here