በጀግኖቿ መወድስ የምትረግድ ከተማ

0
1381

ሠርገኛውን ጥር ወር ከተሻገሩ በኋላ ለብ ካለው አየሯ በቀር የሚጣል የሌላት ድንቅ ከተማ ናት፤ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት መናገሻዋ ባህር ዳር። ለብ ያለው አየሯም ቢሆን እንዲያው ለእንደኔ ዓይነቱ ከብርዳማ ሥፍራ ለመጣ እንግዳ ትንሽ ሙቀት ቢጤ ቢሠጠኝም፣ በዕቅፏ የምታኖራቸው ውብ ሕዝቦቿ ግን ገና የሙቀቱ ጉዳይ ወቅቱ አልደረሰም ብለው ያሻቸውን ለብሰው ሲንቀሳቀሱ ይስተዋላል።

በስፋቱ ኢትዮጵያ ውስጥ ተስተካካይ የለውም የሚባለው እና ከእምቦጭ አረም ጋር አንገት ለአንገት የሚተናነቀው የጣና ጀልባ መፈንጫ፣ የዓባይ ወንዝ መመንጫ ፣ የብዝኃ ሕይወት መሸጎጫው ጣና ሐይቅ፣ ለባህር ዳር ከተማ ያለውን ግርማ ሞገስ መጥቀስ ላይ ሳይሆን ለከተማዋ የሚያቀብለው የከሰዓት በኋላ ነፋሻማ አየር ይህ ነው ተብሎ አይዘለቅም። ቀኑን ሙሉ ደረቱን ለፀሐይ ሠጥቶ የዋለው ዝምተኛው ጣና ሐይቅ አመሻሹ ላይ ዛሩ እንደተነሳበት ባለአውሊያ ሲውረገረግ ያመሻል። በዚህ መሀል ታዲያ ቀኑን ሙሉ ስትሞቅና ስትበርድ ለምትውለው ባህር ዳር ነፋሻማ በረከቱን ያድላታል፤ ያን ጊዜ ነዋሪዎቿ ከዕለት ተዕለት ሥራቸው ረገብ ብለው ጣናን ከዳር ዳር ከበው በረከቱን ይቋደሳሉ።

ይህ የባህር ዳር ነዋሪዎች እና የጣና ሐይቅ ቁርኝት ሠርክ የሚፈጸም እና በጽኑ የተጋመደ ሲሆን፣ በአስገዳጅ ጉዳይ ካልሆነ የማይስተጓጎል የዕለት ተዕለት የደኅንነት ጥይይቅ፣ አልፎ አልፎም በከተማዋ እንግዶች አድማቂነት የሚረብብ ግሩም ሕብረ ቀለማዊ ትስስር ነው። ባህር ዳር ካለፉት ኹለት እና ሦስት ዓመታት ወዲህ አስደንጋጭ ክስተቶችን ብታስተናግድም፣ የሆዷን በሆዷ ይዛ የምታድር እና እንግዶቿን ዕቅፏን ዘርግታ ከመቀበል የማታጎድል እንደሆነች ወደከተማዋ በእነዚያ ዓመታት ውስጥ የተመላለሰ ኹሉ የሚያስተውለው ጉዳይ ነው።

መሪዎቿ ተገድለው ‹‹መፈንቅለ መንግሥት›› ነበር፣ ነገር ግን ከሽፏል የተባለው እና የሰሚን ጆሮ ጭው ያደረገው ክስተት ባህር ዳር በሦስት ዓመት ውሰጥ ካስተናገደቻቸው ኹነቶች በእጅጉ የከፋው እና ልብን የሚሰብረው እንደነበር ነዋሪዎቿ ትናንት የተደረገ ያህል በሐዘን ተሰብረው ክስተቱን አሁንም ድረስ ይተርኩታል። ‹‹የሞተ ተጎዳ እንጂ›› ይላሉ ጭዋታውን ሲጀምሩ፣ ተስፋውን በአምላኩ የምድራዊ አስተዳደሩን ደግሞ በመሪዎቹ ያደረገው ሕዝብ ድንገት መሪዎቹን ሲነጠቅ የሚሰማውን ድንጋጤ ከተነጠቀው ሕዝብ በላይ ማን ሊያውቀው እና ሊሰማው ይችላል ማንም ነው መልሱ።

ይህቺ ግሩም እና አይሰበሬ ከተማ ታዲያ አሁንም የታጨች ኮረዳ መስላ ጣናን ተንተርሳ እየተሸኮረመመች እንግዶቿን መቀበሏን ከዓመት ዓመት እየጨመረች እንጂ እየቀነሰች አልሔደችም። መነሻውን ሩቅ ምሥራቅ ያደረገው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ዓለምን ሲያዳርስ ባህር ዳርንም የገፈቱ ቀማሽ አድርጓታል። ኮቪድ ጨካኝ ጅራፉን ካሳረፈባቸው የኢትዮጵያ ከተሞች ከቱሪዝም ዘርፍ ጋር በተያያዘ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ከተማ ናት። በእርግጥ ዓለም ወደ ቀደመው እንቅስቃሴው የተመለሰ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የቱሪዝም ዘርፉ ትንሽ መነቃቃት ማሳየቱ ባህር ዳርን ከቱሪስት ዕጦት ጣር መለስ አድርጓት ነበር። ነገር ግን፣ ብርቱዋ ባህር ዳር ከዓመት በላይ ባስቆጠረው የሰሜኑ ጦርነት ገፈቱን በግንባር ቀደምትነት የቀመሰው የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት መዲና ከመሆኗ ጋር ተዳምሮ እንቅስቃሴዋ ቀዝቅዟል።

ይህ ብቻ አይደለም፣ በነገራችን ላይ በመጀመሪያዎቹ የጦርነቱ ቀናት ወይም በወቅቱ ‹‹የሕግ ማስከበር›› እንቅስቃሴ ወቅት፣ ከወደ ሕወሓት የተወነጨፉ ሮኬቶች ዒላማም ነበረች። በእርግጥ የተወነጨፉት ሮኬቶች ዒላማቸውን ሳይመቱ፣ ጉዳትም ሳያደርሱ ነበር የፈነዱት። ይህ ኹሉ ታዲያ የጣና ዳር ዕንቁዋን ባህር ዳርን አልበገራትም። ከሮኬት ጥቃቶች በኋላ ከመሐል አገር ወደ ባህር ዳር እና ወደ ታሪካዊቷ የጎንደር ከተማ ይደረግ የነበረው የአየር በረራ ለበርካታ ጊዜያት መታገዱ እና ይህንንም ምክንያት ያደረጉ የደኅንነት አጠባበቅ መመሪያዎች ጎብኚዎችን ከባህር ዳር እግራቸውን እንዲሰበስቡ አድርጓቸው ነበር። በዚህ ተግዳሮት ምክንያት ከተማዋ አሁንም ድረስ የውጭ አገራት ጎብኚዎች ጠረን እንደናፈቃት ነው።

የምሽት ሕይወት
ከቀን ላይ ባተሌነት ጀንበር ስታዘቀዝቅ ባህር ዳር ረገብ ትላለች። ከግሩም ዛፎቿ ሥር ቢራ እየተጠጣ ፍቅር ይወራል፤ ፖለቲካ ይተነተናል፣ የቀን ውሎ ይዘገባል፤ ለነገ ይታቀዳል፤ ምሽቱም ይሠምራል። በነገራችን ላይ ባህር ዳርን እንደማሳወቂያነት ከሚያገለግሉት ዘንባባዎች በተጨማሪ፣ አብዛኛው የባህር ዳር ነዋሪ በመኖሪያውም ሆነ በንግድ ቤቱ ደጃፍ ላይ የተለያዩ ዛፎችን መትከል ባህል አድርጎታል።

ከሥራ በኋላ የዛፍ ሥር የቢራ ፌሽታ ባለፈ ደግሞ ትንሽ ደንገዘገዝ ሲል የባህር ዳር ውብ ገጽታ አድማቂዎች ወደ ሆኑት የባህላዊ ቤቶች ጎራ ይባላል። ከወዳጅ፣ ከእንግዳ፣ እንዲሁም ከቤተሰብ ጋር ሆኖ ከመድረክ የሚታየውን የተለያዩ የኢትዮጵያ ባህላዊ ጭፈራዎችን መመልከት የምሽቱ አንዱ አካል ነው። ታዲያላችሁ አዲስ እንግዳ ሆናችሁ ነገር ዓለሙን ረስታችሁ ከመጠጡም ከጨዋታውም እየደጋገማችሁ ቀልባቸሁን ወደ መድረኩ አዙራችሁ ዘለግ ላለ ጊዜ ቆይታችሁ ወደ ጠረጴዛችሁ ስትመለሱ እና ዙሪያችሁን ስትቃኙ ቅድም የነበራችሁበት ቤት ላይመስላችሁ ይችላል። ምክንያቱ ደግሞ ሰዓቱም ገፍቷል፤ ጊዜውም ከባህላዊው ጭፈራ ወደ ደም የሚያሞቀው ቀረርቶ እና ሽለላው ሳይበረዝ ወደሚቀርብበት ሌላኛው የባህል ምሽት ቤት ይሆናል።

በቅርቡ የተሠዉት የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አምባቸው መኮንን (ዶ/ር) ጨምሮ፣ በመንግሥት በኩል‹‹የከሸፈውን መፈንቅለ መንግሥት›› መርቷል ስለተባሉት ጀነራል አሳምነው ጽጌ፣ እንዲሁም ሌሎች ሟቾች ከፍ ባለ ድምጽ ጥልቅ ግጥምና መወድስ ይቀርብላቸዋል። እኩለ ሌሊት ቢያልፍም በቁጭት ይወሳሉ፤ ይዘከራሉ። ባህር ዳር ያገለገሏትን፣ የለፉላትን፣ የተዋደቁላትን የቁርጥ ቀን ልጆቿን ስታነግስ አምሽታ ታነጋለች። ጀግንነት ምን ማለት እንደሆነ በተግባር አሳይተውናል፤ ሳንጠግባቸው እና ሳያገለግሉን አመለጡን ይሉሃል በግጥማቸው ባህር ዳሬዎች። ‹‹በየመሀሉ የጦሩ መሐንዲስ›› ሲባል ካደመጣችሁ እንዳይደናገራችሁ፤ የጦሩ መሐንዲስ ብርጋደር ጀነራል አሳምነው ጽጌን ነው። በፉከራ፣ በሽለላ፣ በአዝማሪ ግጥም የወደቁት ጀግኖች የመወደሳቸውን ያህል ክልሉን የሚያስተዳድረው አማራ ብልጽግና ብሎም የፌዴራል መንግሥቱም በግልጽ ይወቀሳል፤ ይገሰጻል፤ ይተቻል። እዚህ ላይ ማን ምን አለ ተብሎ ጆሮ ጠቢ ከመንግሥት ወገን እንዴት አይኖርም ለምትሉ ጥያቄያችሁ ተገቢ እና ትክክል ነው። ነገር ግን፣ ከጠየቁት ሠው የሚቸርዎት ምላሽ፣ ‹‹እና ቢኖርስ ምን ሊያመጣ ነው›› የሚል ይሆናል። እርስዎም በጥያቄዎ ተሸማቀውም ወይም ተገርመው በፈገግታ ያልፉታል።

በነገራችን ላይ፣ ባህር ዳር ጀግኖቿን የምታወዳድሰው እና የምትዘክረው በምሽት ቤቶቿ ወይም በመጠጥ በተገፋፋ ስሜታዊነት ብቻ እንዳይመስላችሁ። በከተማው ዋነኛ የመጓጓዣ አውታር በሆኑት ባለ ሦስት እግር ተሸከርካሪዎች ኋላ ላይ የጀግኖች ልጆቿን ፎቶዎች ቃል ኪዳን ከሚመስል አጭር መግለጫ ጋር ባህር ዳር አንግባ ትውላለች። የሞቱት ጀግኖቿ አንጀቷን ያሳረራት ባህር ዳር ሙታንን እያነሳሳች እና በእነርሱ ቁጭት ላይ ተቸክላ የቀረች እንዳልሆነች ማሳያ ደግሞ አሁንም በሕይወት ኖረው ክልሉን እና አገርን ለማቆም ደፋ ቀና የሚሉ፣ ከአገር መከላከያም ሆነ ከፋኖ ሥመ ጥር ጀግኖችን እየጠቀሰች ትረግዳለች። ጀግናን ማወደስ ብቻ ሳይሆን ጀግኖችንም መፍጠር እችልበታለሁ የምትለው የአማራ ክልል መዲና፣

‹‹ኃምሳ ቢወለድ ሃምሳ ነው ጉዱ፤
የተባረከው የአማራ ልጅ ይበቃል አንዱ››

እያለች አንድ አይደለም በርካታ አንዱዎችን ጠርታ ታሞካሻለች። ታዲያ ጀግንነትን በጦር ሜዳ ውሎ ብቻ እንዳልሆነ የተገለጠላት ባህር ዳር፣ ክልሉ ያፈራቸውን ከክልሉ አልፈው የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች ናቸው የተባሉ ቱባ ባለሀብቶችን በሥም እየጠራችም በዓይኗ እንቅልፍ ሳይዞር ስታሞካሽ ታድራለች። ባህር ዳር የእውነት ጀግናን ማወደስ ትችልበታለች። በተስረቅራቂ ድምጾች እና በአስገምጋሚ ግሳት ከሚንተገተግ ወጣት ፎካሪ አንደበት የሚወጡት ጥልቅ ፍቺ ያላቸው ቃላት አድማጪን፣ በቤቱ ያሉ ታዳሚዎችን ቁጭ ብድግ እያደረጉ በወኔ የሚንጡ ናቸው። ‹‹ምነው እኔም ጀግንነትን ፈጽሜ ከዚህ ልጅ አንደበት መወድሰ-ዜማ በተስረቀረቀልኝ›› ሳይሉ አይቀሩም።

ከኹሉም ግን ቀልብን ይዞ ረጅም የሚያስጉዘው ወጣት ወንዶችን ተክተው ወደ ታዳሚው የሚመጡት እንስት የፉከራ እና የቀረርቶ፣ እንዲሁም የሽለላ ንግሥቶች ጉዳይ ነው። በየቤቱ በውኃ ቀጠነ ሚስቱን፣ እህቱን እና እናቱን ካልተደባደብኩ እያለ አምባጓሮ የሚያስነሳው ሞገደኛው ተባዕት ኹሉ እነዚህን እንስቶች ዐይቶ ሴት ልጅ እንኳን ጀግንነቷ ቀረርቶዋ ገደል እንደሚከት በጉልህ ይገነዘብ ነበር።

‹‹ምድር ቁና ሆነች›› የሚለው አባባል እንስት ፎካሪዎች በሕይወት ያሉትንም ሆነ የሌሉትን ጀግኖቻቸውን እየጠሩ ሲፎክሩ ነው ፍቺው የሚገባችሁ።

ታዲያ ይህቺ ድንቅ እና ውብ ከተማ አንድ አዲስ ነገርም ይስተዋልባት ጀምሯል። በውብ ጉዳናዎቿ ላይ ውለው በውብ ዛፎቿ ታዛ ሥር የሚያድሩ ቁጥራቸው እጅጉን የበረከተ ታዳጊ የጎዳና ተዳዳሪዎች ይታዩባታል። ከረጅም ጊዜ ብቻ ሳይሆን ከዓመት በፊት ወደ ከተማዋ ጎራ ብለው ከነበረ ይህ ክስተት አዲስ ቢሆንብዎት አይገርምም። ምክንያቱ ደግሞ በአስደንጋጭ ቁጥር የበዛው የእነዚህ ታዳጊዎች ቁጥር ከተማዋ እንድትደናገርዎ ማድረጉ ነው። የጦርነት አስከፊነት እና በተለይም ደግሞ በክልሉ ላይ ያሳደረው ተጽዕኖ ከእነዚህ ታዳጊዎች ኹኔታ ጋር ሊገናኝ ይችላል? ማን ያውቃል?! ትንታኔውን ለባለሙያዎች ብንተው ይሻላል።

አሁን ባህር ዳርን የምሰናበትበት እና ተመልሼ በዐይነ ሥጋ እስከማያት ድረስ ቅር እያለኝ የምለያይበት ሰዓት ደርሷል። የቀናት ቆይታዬ በፍቅር እና በሐሴት የተሞላ ቢሆንም፣ ባህር ዳር የራባት አንድ ነገር እንዳለ በማየቴ ግን ቅሬታ ቢጤ ጎሸም አድርጎኛል። የጎብኚዎች መቀዝቀዝ እና በዘርፉ ውስጥ ዋና ተዋናይ ናቸው የሚባሉት ባለድርሻ አካላት ሥራ ፈተው ማየቴ ደስታዬ ሙሉ እንዳይሆን አድርጎታል።

ባህር ዳር ሆይ የኢትዮጵያ ሠላም ተመልሶ ክልሉም የቀደመውን መረጋጋት ሲላበስ አንቺም ከዚህ በላይ ደምቀሽ እንግዶችሽን የምትቀበይበት ጊዜ ሩቅ እንዳይሆን የጣና አድባራት ይለመኑሽ፤ ቸር ይግጠመን።
ሠላም !


ቅጽ 4 ቁጥር 175 መጋቢት 3 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here