በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ወለጋ ዞን ሊሙ ወረዳ ውስጥ 24 የሚደርሱ የግለሠብ መኖሪያ ቤቶች በኦነግ ሸኔ፣ የቤኒ እና ሕወሓት ታጣቂዎች መቃጠላቸውን ችግሩ የደረሠባቸው ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ ተናገሩ።
አንድ ሥሜ እንዳይጠቀስ ያሉ በወረዳው መንደር ስድስት ቀበሌ ይኖሩ የነበሩ የአዲስ ማለዳ ምንጭ፣ ቤታቸው እንደተቃጠለባቸውና አንድም ንብረት ማውጣት ባለመቻላቸው ከቤተሰባቸው ጋር ችግር እንደተጋረጠባቸው ጠቁመው፣ ለጊዜው አንጻራዊ ሠላም ወዳለበት ወደ አንገር ጉትን ከተማ ሒደው ከዘመድ ጋ ተጠግተው እንደሚገኙ ተናግረዋል።
“ቤቴ በታጣቂዎች ተቃጥሎብኛል” የሚሉት የችግሩ ሠለባ፣ በቤታቸው የነበሩ ንብረቶች ከፊሎቹ እንደተቃጠሉ፣ ከፊሎቹ ደግሞ እንደተዘረፉ ለአዲስ ማለዳ ገልጸው፣ አያይዘውም “10 ከብቶቼን ተዘርፌያለሁ” ብለዋል።
ግለሰቡ አክለውም፣ ከዚህ በፊት በመንደር አምስት ከ50 በላይ፣ በመንደር ስድስት ደግሞ ከ30 በላይ ቤቶች እንደተቃጠሉ ያስታወሱ ሲሆን፣ “እስከ አራት መቶ ኩንታል እህል በማምረት የሚታወቀው የአካባቢው አርሶ አደር ንብረቱ ተዘርፎ ችግር ላይ ነው” ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
ምንጮቹ እንደገለጹት ከሆነ፣ ሠሞኑን በወረዳው የተከሠተው የቤት ቃጠሎ ብቻ ሳይሆን፣ ቤቶቹ በሚቃጠሉበት ወቅት ንብረታቸውን ለማውጣት የሞከሩ አርሶ አደሮች መገደላቸውንና መቁሰላቸውንም ነው ማወቅ የተቻለው፡
አንድ የአካባቢው ነዋሪ ከዚህ በፊት ኅዳር 10/2014 የአንድ ሰው ሬሳ እንደተቃጠለባቸውና አንድ በኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች የታገተን ሠው ለማስፈታት ሦስት መቶ ሺሕ ብር ክፈሉ ተብለው ብሩን ከከፈሉ በኋላ ሠውየው እንደተገደለ አስታውሰዋል። አያይዘውም፣ ባሳለፍነው የካቲት 29/2014 ከምሽቱ 12 ሰዓት በሊሙ ወረዳ መንደር ስድስት ንብረቱን ለማውጣት ሙከራ ያደረገ እንድሪስ አሕመድ የተባለ የ28 ዓመት ወጣት በታጣቂዎች መገደሉን ጠቁመዋል።
የአዲስ ማለዳ ምንጭ አክለውም፣ ከሟቹ ጋር የነበሩ ኹለት ሠዎች እንደታገቱና እስካሁን ያሉበት ኹኔታ እንደማይታወቅ ነው የጠቆሙት።
ከነዋሪዎቹ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ ከሊሙ ወረዳ ተፈናቅለው በአንገር ጉትን ከተማ የሚገኙ 45 ሺሕ ተፈናቃዮች አካባቢያቸውን ለቀው ከወጡ ወራትን ቢያስቆጥሩም፣ እስካሁን (ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ) አንድ ዙር እንኳ ድጋፍ አለማግኘታቸውን ነው።
ከሊሙ ወረዳ መንደር ስድስት ተፈናቅለው በጉትን ከተማ የሚገኙ ሥማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ ግለሰብ እንደተናገሩት ከሆነ፣ በሊሙ ወረዳ ሥር የሚገኙ የገጠር ቤቶች በሸኔ፣ ሕወሓትና ቤኒ ታጣቂዎች እየተቃጠሉ ነው ብለዋል።
በመከላከያ እየተጠበቀች ያለችው ገሊላ ከተማ ብቻ ናት ያሉት የአዲስ ማለዳ ምንጭ፣ በገጠሩ የሚገኙ መንደሮችና የአርሶ አደሩ አዝመራ ተቃጥሏል ብለዋል። አክለውም፣ ባሰለፍነው የካቲት 30/2014 በገሊላ ከተማ ካሉ የመከላከያ ኃይል ጋር የነበሩ አራት ሠዎች ታግተዋል ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
ኹለት ሞተርና አምስት ከብቶች ተወስደውብናል የሚሉት ግለሰቡ፣ ንብረታቸውና እህላቸውም እንደተቃጠለ ነው የጠቆሙት። በሊሙ ወረዳ የሚገኙ መንደር ኹለት፣ ሦስት፣ አምስትና ስድስት የነበሩ ቤቶች መቃጠላቸውን የጠቆሙት የአዲስ ማለዳ ምንጭ፣ “በቅሎዬ ከነጋሪው ተወስዳብኝ መንደር ስምንት ተዘጋጅተው በተቀመጡ ሽማግሌዎች አማካይነት ስድስት ሺሕ 500 ብር ከፍዬ ተመልሳልኛለች ነው” ያሉት።
አንድ ሺሕ 500 ብር ለሽማግሌዎቹ ነው የተከፈለው የሚሉት ግለሰቡ፣ ከተዘረፉት 10 የግለሰብ በቅሎዎች መካከል ሦስቱ ቢመለሱም፣ ሰባቱ ገና እንዳልተመለሱና በእነሱንም ለማስመለስ ታጣቂዎቹ እስከ 30 ሺሕ ብር ድረስ እየጠየቁ መሆኑን ጠቁመዋል።
አንገር ጉትን የሚገኙ ተፈናቃዮች እስካሁን ምንም ዓይነት ድጋፍ እንዳልተደረገላቸው የጠቆሙት የአዲስ ማለዳ ምንጮች፣ ድጋፍ መጣ ቢባል እንኳ ለተፈናቃዮች እንደማይሠጥ ነው ያመላከቱት።
“ትልቅ አፈና፣ ትልቅ ጭቆና ነው ያለው። ሊሙ ወረዳ ግን በኢትዮጵያ መንግስት ነው እየተዳደረ ያለው? እንኳን የድጋፍ ዕርዳታ፣ በቦታው ተገኝቶ የሚዘግብ ጋዜጠኛም አላገኘንም። መንግሥት ሠላም ነው እያለ ሪፖርት ቢያቀርብም ለችግሩ መፍተሔ አልተገኘም” ሲሉ ምንጮቹ ተናግረዋል።
አዲስ ማለዳ ጉዳዩን በማስልከት ከሊሙ ወረዳ አስተዳዳሪ ለሙ አኩማ ጋር ቆይታ ያደረገች ሲሆን፣ አስተዳዳሪውም በሊሙ ወረዳ መንደር ስድስት ተከሠተ ስለተባለው የቃጠሎ ሁኔታ ወቅታዊ መረጃ የለኝም የሚል ምላሽ ሠጥተዋል።
የወረዳ አስተዳዳሩ በጉትን ከተማ ለሚገኙ ተፈናቃዮች ከኹለት ወር በፊት ድጋፍ ተደርጓል ቢሉም፣ ከተፈናቃቹ መካካል አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ሠዎች ግን አንድ ጊዜ እንኳ ድጋፍ እንዳልተሠጣቸው ነው የገለጹት። የወረዳ አስተዳደሩ ስልካቸውን በመዝጋት በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆኑም።
ቅጽ 4 ቁጥር 175 መጋቢት 3 2014


