በአማራ ብሔራዊ ክልል ሕወሓት በከፈተው ጦርነት ምክንያት በተጎዱ አካባቢዎች የወደሙትን የውኃ መሠረተ ልማቶች ለመገንባትና ለማኅበረሰቡ ውኃ ለማቅረብ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ያስፈልጋል ሲል የክልሉ ውኃና ኢነርጂ ቢሮ ለአዲስ ማለዳ ገለጸ።
የአማራ ክልል ውኃና ኢነርጂ ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አደም ወርቁ እንደገለጹት፣ በጦርነቱ የተጎዱ የምሥራቅ አማራ አካባቢዎች ውኃ እንዲያገኙ ለማድረግ በተደረገው ጥናት ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል ነው ያሉት።
ሆኖም ግን፣ በዚህ ወቅት ይህን ለማድረግ መሠረታዊ የበጀት ዕጥረት መኖሩ ዋነኛ ማነቆ መሆኑን ጠቅሰው፣ ቢሮው ከክልሉና ከፌደራሉ መንግሥት ጋር በመነጋገር የአደጋ ጊዜ በጀት እንዲመደብ በማድረግ ሥራዎች እንደሚሠሩ ተናግረዋል።
ለዚሁ ሥራ በመንግሥት የካፒታልና የመደበኛ በጀት ይመደባል ያሉት ኃላፊው፣ ቢሆንም ግን ከፍተኛ የበጀት ዕጥረቱን በመኖሩ በአሁኑ ሰዓት በምሥራቅ አማራ ያለውን የውኃ ችግር ለማቃለል በሦስት መንገድ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።
የመጀመሪያው የመብራት መቆራረጥ ባለባቸው አካባቢዎች በጄኔሬተር ኃይል በመታገዝ ውኃ እየቀረበ እንደሆነ ጠቅሰዋል።
ከፍተኛ ውድመት በደረሰባቸውና በመብራት ኃይል ውኃ ለማቅረብ አስቸጋሪ በሆኑባቸው ቦታዎች ደግሞ፣ ውኃ በቦቴ እየቀረበ መሆኑን አመላክተዋል። መለስተኛ ጥገና በሚያስፈልጋቸው እንደ ደሴ፣ ኮምቦልቻ እና ከሚሴ አካባቢዎች በአንጻሩ ቀድሞ አገልግሎት ይሰጡ የነበሩት መሠረተ ልማቶችን በመጠገን ውኃ እየቀረበ መሆኑን ነው የገለጹት።
ኃላፊው አያይዘውም፣ በአሁኑ ወቅት በምሥራቅ አማራ አካባቢዎች ከፍተኛ የውኃ ችግር መኖሩን ጠቁመዋል። ቆቦ ላይ ከፍተኛ የውኃ ችግር አለ የሚሉት ኃላፊው፣ አካባቢው መብራት የሚያገኘው ከወደ ትግራይ በመሆኑ ችግሩን የከፋ እንዳደረገው አመላክተው፣ ቢሆንም በጄኔሬተር በመታገዝ ያለው ውኃ እየቀረበ ነው ሲሉ አብራርተዋል።
በተመሳሳይ መልኩ፣ ሐይቅ በጦርነቱ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባት ከተማ መሆኗን ተከትሎ፣ በመብራት ኃይልም ይሁን በጀነሬተር ውኃ ማቅረብ ባለመቻሉ በቦቴ እየቀረበ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በባቲም እንዲሁ ተመሳሳይ ችግር በመኖሩ፣ ደጋን በሚባል አካባቢ ኹለት የውኃ ጉድጓዶች ተቆፍረው አሁን ላይ በበጀት ዕጥረት ምክንያት አገልግሎት ማስጀመር ያልተቻለ ቢሆንም፣ የበጀት ችግሩ ሲፈታ ፓምፕና ጀነሬተር ተገጥሞላቸው፣ የከተማውን ማኅበረሰብ ሙሉ በሙሉ ተጠቃሚ ያደርጋሉ ነው ያሉት።
በመርሳና ሌሎች አካባቢዎችም እንዲሁ ችግሮች በሥፋት መኖራቸውን ጠቁመው፣ ችግሮችን ለመፍታት ምዕራብ አማራ ላይ ያለው ትኩረት ተትቶ፣ ምሥራቅ አማራ ላይ እየተሠራ ነው ብለዋል።
ካለው መሠረታዊ የበጀት ዕጥረት ባለፈ፣ የውኃ ግንባታዎች በሚሠሩበትና መስመር በሚዘረጋበት ወቅትም የግለሰቦችን መሬት ስለሚነካ ይህም አንድ ተግዳሮት መሆኑን ያነሱት ኃላፊው፣ እስከ 500 ሜትር ወደታች ተቆፍሮ ውኃ ላይገኝ የሚችልበት አጋጣሚ አለ በማለት በሥራ ወቅት የሚያጋጥሙ ተጨማሪ ችግሮችን አብራርተዋል።
አያይዘውም፣ የዕቃ አቅርቦት ችግር መኖሩን አንስተው፣ ትክክለኛውን ፓምፕና ጀነሬተር ገበያ ላይ ማግኘት አዳጋች ሆኗል ነው ያሉት።
ባለሙያ በመመደብ፣ ጉድጓድ በመቆፈር፣ የውኃ ግንባታ መስመር በመዘርጋት፣ እንዲሁም ጀነሬተርና ፓምፕ ግዥ ላይ የሚያግዙ ወደ 13 ገደማ ግብረ ሠናይ ድርጅቶች በአካባቢው እንዳሉም ተመላክቷል።
በምሥራቅ አማራ ያለውን የውኃ ችግር በዘላቂነት ለመፍታትም ከኹለት እስከ ሦስት ዓመት እንደሚፈጅ ነው የተጠቆመው።
ቅጽ 4 ቁጥር 175 መጋቢት 3 2014


