በዋግ ምኽራ ብሔረሰብ አስተዳደር የ12ኛ ክፍል ፈተና ከወሰዱ 2923 ተማሪዎች 2218 ወደቁ

0
488

በብሔረሰብ አስተዳደሩ ከሚገኙ 16 የመሰናዶ ትምህርት ቤቶች ውስጥ 15 ትምህርት ቤቶች ተማሪዎችን ያስፈተኑ ሲሆን፣ ከተፈተኑ 2923 ተፈታኞች 705 ብቻ የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ያመጡ ናቸው። ከነዚህ ውስጥ 1107 የሚሆኑ የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች ለፈተና ቀርበው 369 ወይም 33 በመቶ ያለፉ ሲሆን፣ በማኅበራዊ ሳይንስ የትምህርት ዘርፍ ደግሞ 1816 ተማሪዎች ተፈትነው ማለፊያ ነጥብ ያመጡት 336 ናቸው።

በብሔረሰብ አስተዳደሩ ወደ ከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ነጥብ ያመጡ ተማሪዎች 24 በመቶ ብቻ መሆናቸውን የብሔረሰብ አስተዳደሩ ትምህርት መምሪያ አስታውቋል።

ከ1636 ለፈተና ከቀረቡ ሴት ተማሪዎች ውስጥ 380 ወይም 23.2 በመቶ የሚሆኑት ማለፍ ችለዋል። ወደ ከፍተኛ ትምህርት ማለፊያ ምዘና ከተሰጡ 15 ትምህርት ቤቶች ሦስት ትምህርት ቤቶች ምንም ያለፈ ተማሪ የሌለ ሲሆን፣ ከአንድ ትምህርት ቤት አንድ ተማሪ ብቻ ማለፍ ችሏል።

የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ትምህርት መምሪያ ኃላፊ ሰይፉ ሞገስ እነዚህ ተማሪዎች የተፈተኑበት ወቅትና ጊዜ፣ ትምህርት የሚማሩበት ስላልነበረና ይልቁንም በወቅቱ የዋግ ወጣቶችና ተማሪዎች ክላሽን እንጂ እስክርቢቶ ያልጨበጡ በመሆናቸው ውጤቱ ይኸው ሆኗል ማለታቸውን ከዋግ ኽምራ ኮምዩኒኬሽን የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

መምሪያ ኃላፊው አክለውም፣ ለፈተና የተቀመጡበት ጊዜ፣ አይደለም ስለፈተና ማሰብ በሕይወት ተረጋግተው ለመቀመጥ እንኳን ያስቻለ ጊዜ አልነበረም። ስለሆነም የዋግ ተማሪዎች ለመማር፣ ለማንበብም ሆነ ለፈተና የሚያበቃቸው ጊዜ ስላልነበራቸው፣ ወቅቱን፣ ችግሩና ሁነቱን የዋጀ ውሳኔ መወሰን ነበረበት ብለዋል።

እንደ መምሪያ ኃላፊው ገለጻ፣ በመፈናቀልና በውጊያ ላይ፣ እንዲሁም በዱር በገደል የነበሩ አርበኛ የዋግ ተማሪዎች፣ ለፈተና መቅረባቸው ሳይበቃ ክፍል ገብተው ዓመቱን ሙሉ እንደተማሩ ተደርገው እንዲመዘኑ መደረጋቸው እንዲወድቁ አድርጓቸዋል ሲሉ ተናግረዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 176 መጋቢት 10 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here