በኢትዮጵያ ‹ለውጥ› የሚል ቃል ለአንደበት እንግዳ መሆን ካቆመ አራት ዓመታት ተጠግተዋል። በፖለቲካው የታየው የመገራት አኳኋን፣ በሕዝቡ ውስጥ የታየው ተስፋና መነሳሳት ‹ፀሐይ ከዚህ በኋላ በኢትዮጵያ ሰማይ ላይ እስከ ዘለዓለም አትጠልቅም› የተባለ ያህል ብዙዎችን ያበረታ ነበር። አሁን ላይ ግን ያ ሁሉ ንቃት እንደ ጠዋት ጤዛ ድራሹ እንኳ ያለ እስከማይመስል ደርሷል።
ብዙዎች የለውጡ ማለዳ ላይ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ንግግር ያወሳሉ። ንግግር ብቻ አልነበረም። በተግባር የታዩ ከፖለቲከኞች ጋር የተደረጉ ዕርቆችና ርቀው ለነበሩ የተከፈቱ በሮች፣ ከኤርትራ ጋር የነበረው አለመግባባት መቋጨቱና የመሳሰለው በጊዜው ‹እውነት ነው!› ያሰኘው ብዙዎችን ነው። ከዛም አልፎ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአንደበታቸው አውጥተው ‹‹መጪው ጊዜ በኢትዮጵያችን የፍትሕ እና የይቅርታ ጊዜ ነው›› ብለው ለደረሱ ጥፋትና ውድመቶች ሁሉ ይቅርታ ጠይቀው ነበር።
ሕዝቡ ተስፋ ያደረገው እንደ አገር በትልቁ ዕድገትና እውነተኛ ለውጥን ሲሆን፣ ለዛም የሚያደርሰው ትንሽ የሚመስለው ከቀበሌና ወረዳ ጀምሮ ያለው አሠራር እንደሚቀየር ተጠብቋል። ታጥረው የኖሩ መሬቶች ሲገለጡ ፍትሕን፣ ተዘግተው የነበሩ በሮች ሲከፈቱ እኩልነትን፣ በይቅርታ እቅፎች ሲዘረጉ እምነትን ብዙዎች ይዘው ነበር። ሙስና ሊቀር ባይሆን እንኳ ሊቀንስ፣ ዘመድና የአገር ልጅ መርጦ ማስቀደም ላይኖር፣ ያ ባይሆነ እንኳ ሊገደብ ይችላል የሚል ጽኑ እምነት ያደረባቸው ብዙዎች ናቸው።
በኋላ ላይ የተከሠቱ እጅግ አግባብ ያልሆኑ ግጭቶችና መፈናቀሎች እንኳ ሲከሠቱ፣ ‹የለውጥ ዋዜማ እንዲህ ያለ ነውጥ አያጣውም። ደንቡ ነውና እንታገስ!› ያለው ብዙ ነው። ‹እንደውም ምርጫው ካለፈ በኋላ ሁሉም ይስተካከላል› የሚል የተስፋ ማራዘሚያን ብዙዎች ይዘው ዘልቀዋል። ግን አልሆነም። ከዚህ የባሰም አለ ብሎ ለመጽናናት እንኳ በማያመች መልኩ ኢትዮጵያ እጅግ የተወሳሰበና የሚያስቀይም ሁኔታ ውስጥ የተገኘችበት ጊዜ ላይ ደርሰናል።
ለውጥ መጣ በተባለበት ወቅት ብዙዎች በቀደመው ሥርዓት የነበረውን በማንሳትና ከዛ ጋር በማነጻጸር ነባራዊውን ሥርዓት ሲያመሰግኑ ነበር። የቀደመው ሥርዓትም ከሙስና እና ዝርፊያ፣ ስርቆትና ሌብነት ጋር በተያያዘ በብዙ ተወቅሷል። ተቋማትም ቀድሞ የነበሩበት አቋም ተተችቶ ሊሻሻሉ በሚችሉበት መንገድ ተቃኝተው የተለያየ ሥም፣ ቅርጽና አወቃቀር ይዘው ዳግም ተወልደዋል። የአዳራሽ ድግስ፣ ለቲ-ሸርትና ኮፍያ እየተባለ የሚወጣው ወጪ ተገስጿል። በጾታ እና በችሎታ ባለሙያዎች በየመስኩ ተመድበው አስቀድሞ በነበረው ሥርዓት የነበረው አካሄድ ተወቅሷል።
እንደ መገናኛ ብዙኃን አዲስ ማለዳን ጨምሮ ጥቂት የማይባሉ የኅትመት፣ እንዲሁም የብሮድካስት ሚዲያዎች ዘርፉን ተቀላቅለዋል። ሥራቸውንም ከዕስር የተፈቱ ጋዜጠኞችንና በነጻነት እንዲሠራ ዕድል ያገኘውን ጋዜጠኝነት በማውሳት ጀምረዋል። ሁሉም በየጊዜው ‹ባለፉት ኻያ ምናምን ዓመታት› እያለ ከቀደመው የተሻለ ጊዜና ሥርዓት መጣልን እያለ ሲያወድስ ቆይቷል።
አዲስ ማለዳ ባለፉት ዓመታት የሆነውን በወፍ በረር ስታነሳ፣ ከአንባቢዎቿ እውቀት የተሠወረ ነው በሚል አይደለም። ይልቁንም መለስ አድርጋ እንደ አገር ሕዝቡ፣ እንደ አመራርም መንግሥት ራሱ፣ ባለሥልጣናትና ኃላፊዎቹ ሁሉ ሲሰፍሩበት የነበረውን ቁና፣ ሲመዝኑበት የነበረውን ሚዛን ለማስታወስ በመፈለግ ነው።
ዛሬስ የት ደርሰናል ካልን የምናነሳው በሰሜኑ ክፍል የተነሳውን ጦርነትና በየአካባቢው የሚደርሰውን የሰዎች አሰቃቂ ሞት ብቻ አይደለም። ራስ ወዳድነት፣ ዝርፊያና ስርቆት ተባብሷል። ይህ የመንግሥት ሥርዓት ችግር ብቻ የሚመስለው ካለ ትክክል አይደለም። ይህ ሁሉም እያንዳንዱ እኔንም ይመለከተኛል ሊልበት የሚገባ ጉዳይ ነው።
መንግሥትና አመራሮች በሰፈሩበት ቁና እንዳይሰፈሩ ልብ ይበሉ። ትንሹን ምሳሌ ብናነሳ መንግሥት የቀደመውን ሥርዓት ይኮንንበት በነበረው ያለአግባብ የሆነ ወጪን ማውጣትና ድግስ ማብዛት ላይ ራሱ ተገኝቷል። በየተቋማቱ ያሉና የጠፉ የመሰሉ ብልሹ ይባሉ የነበሩ አሠራሮች ተመልሰው ብቅ ብቅ ማለት ጀምረዋል። በጥፋት ከሥልጣን የወረዱ ሰዎች ቦታ ቀይሮ መሾም፤ ዛሬ ላይ ከቀደመው ሥርዓት በምልሰት የምናስታውሰውና በተግባር እያየነው ያለ ጉዳይ ሆኗል።
ጋዜጠኞች ይታሰራሉ፤ ታስረው ለቀናትና ለወራት የት እንደሆኑ እንኳ ሳይታወቅ ይከርማሉ። አቤቱታ ለማሰማት በለውጡ ማግስት የተመሠረቱ ማኅበራትና ቅንጅቶችም ሰሚ ያላቸው አይመስልም። ቅርሶች ከዛሬ ነገ ይፈርሳሉ በሚል ሁሉም መንገዱን እያማተረ ይራመዳል። ቅርሶችና ታሪኮች የተናቁበት ጊዜ ቢያልፍም፣ ጭራሽ የሚፈርሱና የሚጣሉበት አኳኋን ልብን የሚሰብር ሆኗል። ትልቁ ጉዳይ ቀርቶ በትንሹ ጉዳይ ጊዜ ለጭቅጭቅ እየተሰዋ ነው። ‹እንፈታዋለን!› የተባለ ችግር ተባብሶ ያድራል። ይህም ሁሉ ተዳምሮ እያደር የሕዝብን አመኔታ የሚያሳጣ ከመሆኑ በላይ የቀደመው ሥርዓትም በዚሁ ዘርፍ በእጅጉ ሲወቀስ እንደነበር ማስታወስ ይገባል።
ሕዝብም በሰፈረበት ቁና እንዳይሰፈር ያስተውል። ራስ ወዳድነት፣ ጠባብነት እና ‹ሰርዶ አይብቀል› የመሳሰለ መንፈስ በየጎዳና፣ በየመንገዱ የሚታይ ጉዳይ ሆኗል። ከመረጋጋት ይልቅ ስሜታዊነት አይሏል። ለቆመው ሁሉ በማጨብጨብ፣ ባለማገናዘብና ከአጀንዳ አጀንዳ እየዘለሉ ሁሉም ጉዳይ ላይ አስተያየት በመስጠት ለውጥ አይመጣም። ነው ሲባል አብሮ ነው፣ አየደለም ሲባል አይደለም ብሎ ‹መንጋ› ሆኖ በመሰለፍም ችግር አይፈታም።
የጅምላ የአደባባይ ፍርድና ግድያዎች፣ ፍረጃና በደሎች ምንም እንኳ በመንግሥት ቸልታ ይፈጸሙ እንጂ፣ መንጋ ሆኖ ነገሩን በዝምታ የሚያየው ማኅበረሰብና ሰፊው ሕዝብም አብረው ተጠያቂ መሆናቸው እንደማይቀር አዲስ ማለዳ ልታሳስብ ትወዳለች።
መንግሥትም ሆነ ሕዝብ ኢትዮጵያን አክብረው፣ ፈጣሪን ፈርተው አልያም ለሕሊናቸው ብለው በጎውን ነገር ማድረግ ካልቻሉ ቢያንስ በተረካቢ ትውልድ ዐይን ውስጥ መሆናቸውን ያስታውሱ። መዛኙ፣ ጠያቂውና ዳኛው ተረካቢ ትውልድ ነው። ከምንም በላይ ደግሞ የሚያስቀይመው በመዘኑበት ሚዛን፣ በሰፈሩበት ቁና ለመሰፈር መታጨት ነው። ከዛም የሚከፋው ደግሞ ከዛም አንሶ መገኘት ነው።
እርግጥ ነው! ከአራት ዓመት በፊት በተለኮሰ የለውጥ ሻማ ብዙ ተጨማሪ ሻማዎች በርተዋል። በአንጻሩ ብዙ ሳይጠፉ የነበሩ ሻማዎች እንደነበሩም ሲጠፉና ሲጎድሉብን ልብ ብለናል። ለውጥን ማመስገን ተገቢ ነው፤ ችግር ሲኖርም ማሳሰብ እንደዛው።
አዲስ ማለዳ ለኢትዮጵያ አሁንም ብሩኅ ተስፋ እንዳለ ታምናለች። ሰው በሕይወት እስካለ ድረስ ጤና ባይኖር እንኳ እስኪድን እንደሚታገል፤ እንዲያ ባለ ትግል ውስጥ እንደምትገኝ ታውቃለች። ያለፈው እንደሚያልፍ ሁሉ ነገም የተሻለ ቀን እንደሚመጣ ጥርጥር የላትም። ይህን ክፉ ጊዜ ለማለፍ ግን መንግሥት በበኩሉ፣ ሕዝብም በድርሻው አስተውሎትን ሊላበሱ ያሻል ስትል በአጽንዖት ትገልጻለች። በሰፈርንበት አንሰፈር፤ በሰፈራችሁበት አትሰፈሩ!
ቅጽ 4 ቁጥር 176 መጋቢት 10 2014



