አርቲስቶች ሙዚቃን ለሚጠቀሙ ተቋማት የጠየቁት ክፍያ ለስምንት ዓመት ተጓቷል

0
856

የኢትዮጵያ የሙዚቃ ቅንጅትና ተዛማጅ መብቶች የጋራ አስተዳደር ማኅበር ሙዚቃን ከሥራቸው ጋር በተያያዘ የሚጠቀሙ አካላት/ተቋማት ብር እንዲከፍሏቸው የወጣው አዋጅ ተግባራዊ ሳይደረግ ለስምንት ዓመት ያህል መጓተቱን ከኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ባለሥልጣን ከተገኘው መረጃ ማወቅ ተችሏል።

ጉዳዩ ለስምንት ዓመት መጓተቱን የገለጹት በባለሥልጣኑ የቅጅ መብት ጥበቃና ልማት ተጠባባቂ ዳይሬክተር ወሰን ሙሉ፤ ለመጓተቱ ዋነኛው ምክንያት ሙዚቃን በይበልጥ የሚጠቀሙ አካላት/ተቋማትን ለመለየትና በሌሎችም ተያያዥ ሥራዎች ምክንያት ነው ብለዋል።

ወሰን ለአዲስ ማለዳ እንዳብራሩት፣ ማንኛውም ሙዚቃን የሚጠቀም ሬስቶራንት፤ ቴሌ፤ ተሽከርካሪ፤ የሚዲያ ተቋም እንዲሁም ሌሎች አካላት ክፍያ መክፈል እንዳለባቸው የተወሰነ ሲሆን፤ በቅድሚያ ብዙ ጊዜ ሙዚቃን በዕለት ተዕለት ሥራቸው የሚጠቀሙት የሚዲያ ተቋማት ክፍያውን እንዲከፍሉ ለማድረግ አስተያየታቸው እየተሰበሰበ ነው።

አርቲስቶች ሙዚቃቸውን የሚጠቀም አካል ብር እንዲከፈላቸው ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት በመገናኛ ብዙኀን በኩል ያለው ሂደት፤ ለ27 ሚዲያና የብሮድካስት ማኅበር ምላሽ ተሰባስቦ የሚያልቀው እስከ መጋቢት 10/2014 ነው ብለዋል። የብሮድካስት ማኅበራቱም አንከፍልም ስለማይሉ ውሳኔው ሊጸድቅ ይችላል ብለዋል።

ማንኛውም ሰው ሙዚቃን ሲጠቀም ብር የመክፈል ግዴታ እንዳለበት አዋጁ የወጣው በ2006 ነው ያሉት ዳይሬክተሩ፤ ቅዳሜ መጋቢት 10/2014 የመገናኛ ብዙኀን ምላሽ ተሰብስቦ ስለሚያልቅ ጉዳዩ ስምምነት ላይ ከተደረሰ በኋላ ክፍያው እንደሚጀመር ጠቁመዋል።

ወሰን ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ የሙዚቃ ቅንጅትና ተዛማጅ መብቶች የጋራ አስተዳደር ማኅበር ንብረታቸውን ጥቅም ላይ የሚያውለው አካል ብር እንዲከፍላቸው ፍቃድ ተሰጥቷቸዋል። በተያያዘም ይህ የንብረቱ ባለቤቶች መብታቸው ነውም ሲሉ ወሰን ጨምረው ገልጸዋል።

ይህ በአገር ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ ሊጀመር ነው የተባለው የሙዚቃ ክፍያ መጠንም ባለንብረቶቹ እንዲከፈላቸው ባሳወቁት የብር መጠን ሲሆን፤ እንዲከፈል የተወሰነውን የብር መጠን ለማጽደቅ የቴሌቪዥን እና ለሬዲዮ ጣቢያዎች ምላሽ መመልከት እንደሚያሻ ወሰን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ የሙዚቃ ቅንጅትና ተዛማጅ መብቶች የጋራ አስተዳደር ማህበር የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ለሚጠቀሙት አንድ ሙዚቃ አንድ ብር በመክፈል አንድ የቴሌቪዥን ጣቢያ በ24 ሰዓት ውስጥ 360፤ በዓመት 65 ሺሕ 700 ዘፈን ቢጠቀም በዓመት 131 ሺሕ 400 በር እንዲከፍላቸው ነው የወሰኑት።

እንዲሁም የሬዲዮ ጣቢያ ለሚጠቀሙት ሙዚቃ እንዲከፍሉ ማኅበሩ ያቀረበው ቀመር፤ ለሬዲዮ ጣቢያዎች ለሚጠቀሙት አንድ ሙዚቃ አርባ ሳንቲም እንዲከፍሉ ሲሆን፤ በ18 ሰዓት 270 ዘፈን ቢጠቀሙ በዓመት 39 ሺሕ 420 ብር ሊከፍሏቸው እንደሚገባ ተቀምጧል።

የሙዚቀኞች የጋራ ማህበሩ ከዚህም በተጨማሪ የበዓል ቀናቶችን በተመለከተም የክፍያውን መጠን ወስኗል። ይኸውም እያንዳንዱ የቴሌቪዥን ጣቢያ በበዓል ዕለት ለሚጠቀመው አንድ ሙዚቃ 50 ብር እንደሚከፍልና በ24 ሰዓት ውስጥ 180/360 ሙዚቃ ቢጠቀም በቀን ዘጠኝ ሺሕ/ 18 ሺሕ ብር መክፈል እንዳለበት ነው።


ቅጽ 4 ቁጥር 176 መጋቢት 10 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here