“ሲቄ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ‹አለንጋ› የሚል ትርጉም አለው። በገዳ ትውፊታዊ አስተዳደር ውስጥ በባሏ ጥቃት የደረሰባት ሚስት፣ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ባሏ ላይ የካሣ ውሳኔ የምታሳልፍበት ስርዓት ሲቄ ይባላል።
አንዲት ሴት ከሚያስፈልጓት መሠረታዊ የሥነ ልቦና ዕሴቶች መካከል አንዱ እና ዋነኛው ነገር በራስ መተማመን መቻል ነው። በእርግጥ በራስ መተማመን ኹሉም ሰው ሊኖረው የሚገባው ማንነት ነው። በአብዛኛው ሴቶች ጋር በራስ የመተማመን ነገር አነስተኛ ሆኖ፣ አልያም አንዳንዴ ከነጭራሹ የሌለ ያህል ይሆናል። በዚህም የተነሳ ያመለጡ መልካም ዕድሎች ብዙ ናቸው።
በራስ መተማመን የራስን እውቀት እና ክብር፣ እንዲሁም የራስን ችሎታን የማወቅ ድምር ውጤት ነው። አጉል መታበይና የሌለውን ኹሉ አለ ብሎ ማቅረብ ግን አይደለም። ይልቁንም በራሷ የምትተማመን ሴት ምክንያታዊ በመሆን ምን ይመጣልን ከግምት ውስጥ በማስገባት እና አደጋን በመጋፈጥ ዓላማዋን ለማሳካት ትታትራለች። በአንጻሩ በራስ መተማመን ከሌላት፣ የምትሞክራቸው ነገሮች ሁሉ የሚሳኩላት አይመስላትም። ነገን በምታስብ ጊዜም መጥፎ ነገሮችና ውድቀት ፈጥኖ ስለሚታያት አቅሟን አሟጣ ለመጠቀም እንድትፈራ ያደርጋታል።
ያ ደግሞ የፈለገችወን ከመናገር እና ከማድረግ ይልቅ ሌላ ሰው ጋር ጥገኛ እንድትሆን ያደርጋታል። ይሄ ነገር ደግሞ ራሷን እንዳትችል እና ነገሮችን በራሷ እንዳትመራ የሚያስገድዳት ነው።
እህቴ! በራስ መተማመን የሚያሳጣሽን ነገር ከሕይወትሽ ወስጥ ማስወጣት ይኖርብሻል። አንቺ አዲስ ሰው የምትሆኚው የሚጎዳሽን እና የሚጠቅምሽን መለየት ስትችይ እና በራስ መተማመን ሲኖርሽ ነው። በራስ መተማመን የሌላት ሴት አብዛኛውን ጊዜ የምታሳልፈው በመዞር እና በወሬ ነው። ይህ የሚሆንበት ምክንያት ደግሞ ከሰዎች ዕርዳታን ለማግኘት ስትል ነው። በራስ መተማመን ከሌለሽ ጊዜሽን እና ጉልበትሽን የምታባክኝ ነው የምትሆኚው። የፈጠራ ሰው እንዳትሆኝ ነው የሚያደርግሽ። ያለ ሰው ዕርዳታ እና ተጽዕኖ ነገሮችን በራስሽ አቅም አድርጊያቸው፤ ስኬታማ ሰው ለመሆን ከፈለግሽ በራስሽ ችሎታ ላይ ትልቅ እምነት ሊኖርሽ ይገባል።
ከሌላ ከማንም ከመጠበቅሽ በፊት በቅድሚያ ራስሽን ማክበርና የማይተመን ዋጋ ያለሽ መሆንሽን ለራስሽ ማሳመን አለብሽ። የእኔ ዋጋ ከፍ ያለ ነው ብለሽ ማሰብ ይጠበቅብሻል። ራስሽን በጥልቀት በመመልከት ችሎታሽን አዳብሪ። በራስ መተማመንሽን የሚሸረሽሩ ሐሳቦችን ከሐሳብሽ በማውጣት ‹አልችልም! አይሳካልኝም! እወድቃለሁ!› የሚሉ አሉታዊ ሐሳቦችን አስወግጂ።
ለራስሸ አዲስ ብርሃን በመስጠት ግብሽን ተመልከቺ! ያንንም አሳካለሁ በማለት እና በማጉላት በራስ መተማመንሽን ከፍ አድርጊ! አንቺ ጎበዝ እንደሆንሽ እና ማሳካት እንደምትችይ በተግባር አሳይ። መሆን ትችያለሽ፤ ማድረግ ትችያለሽ። መቻልሽን ግን ካልሞከርሽ ልታውቂ አትችይምና በራስ መተማመንን አክለሽ ወደፊት ተራመጂ።
ልዩወርቅ ዲበኩሉ
ቅጽ 4 ቁጥር 176 መጋቢት 10 2014


