የሰው ልጅ መፆምን መቼ እንደጀመረ እርግጠኛ ሆኖ የሚናገር ተመራማሪ ሳይንቲስት ባይኖርም፣ የኃይማኖት አባቶች ግን ፆም በመጀመሪያው ሰው በአዳም እንደተጀመረ ያስተምራሉ። ዘመኑና ምክንያቱ ይለያይ እንጂ አብዛኞቹ ኃይማኖቶች ተከታዮቻቸው እንዲፆሙ ይመክራሉ፤ አልያም ያስገድዳሉ።
ፆምን መፆም ከአንድ ምዕመን የሚጠበቅ ግዴታ ነው ቢባልም፣ ከመፆም የሚገኘው ሥጋዊም ሆነ መንፈሳዊ ጥቅም ከኃይማኖት ኃይማኖት ይለያያል። በአብዛኛው ከዓለማዊ ክፉ ሥራ ለመራቅ፣ መንፈሳዊ ፀጋን ለመላበስ፣ ምድራዊ ኃጢያትን ለማሠረ እንዲሁም የተለያዩ ሥጋዊም ሆነ መንፈሳዊ ጥቅሞችን ለማግኘት አስፈላጊ እንደሆነ ይነገራል፤ ይታመናልም።
‹ሬድ ኢንዲያን› ከሚባሉት የጥንት የአሜሪካ ነዋሪዎች በባህላቸው መሠረት ከሚፆሙት ፆም አንስቶ፣ የተለያዩ ኃይማኖቶች እንደ አንድ መስፈርት አድርገው ጊዜና ሥርዓት ተበጅቶለት የሚከናወን በርካታ ዓይነት ፆም አለ። በአንዳንድ እምነቶች ምዕመኑ እንደፈለገ በአሰኘው ጊዜና መንገድ ከፍላጎቱ በመቆጠብ የሚፆማቸው ዓይነቶች ቢኖሩም፣ በአብዛኛው ግን ተመሳሳይ ይዘት አላቸው።
እድሜ ልካቸውን ሥጋ ነክ ነገሮችን ከመብላት ተቆጥበው ከሚኖሩት የሒንዱ እምነት ተከታዮች ጀምሮ፣ ምግብ ሳይመርጡ የሚበሉ፣ ሰዓት በማራዘም የሚፆሙ እንዲሁም ኹለቱንም ጊዜንና የሚበሉትን ዓይነት መርጠው የሚያከናውኑ አሉ። በአንድ እምነት ተከታዮች ዘንድም ልዩነት ያላቸው ዓይነትና የጊዜ ምርጫ ቢኖሩም፣ በአፈፃፀምና በሚመርጡት የምግብ ዓይነት ግን በአብዛኛው ተመሳሳይ እንደሆነ ይታወቃል።
የአይሁድ፣ የኦርቶዶክስ፣ የእስልምና፣ የካቶሊክ፣ የሒንዱ፣ የቡዲሒዝምና የሌሎች እምነት ተከታዮች ሕግና ሥርዓት ባለው መንገድ ወጥ በሆነ ሒደትና ጊዜ ይፆማሉ። የእምነቱ ተከታዮችም ከሚታዘዙት ዋና ዋናዎቹ አፅዋማት በተጨማሪ፣ በግላቸው ሱባዔ ለመያዝ አልያም ከሠሩት ኃጢያት ለመንፃት ታዘውም ሆነ በፍላጎታቸው መፆም ይችላሉ። መፆምን የሚከለክል ኃይማኖትም ሆነ የፍልስፍና አስተሳሰብ እስካሁን ስለመኖሩ የተሠማ ነገር ባይኖርም፣ በአብዛኛው ጠቃሚነቱ ለነፍስ እንደሆነ ስለሚታሰብ ለመንፈሳዊ ተጋድሎና ጥቅም ብቻ የሚፆም ተደርጎ ይወሠድ ነበር።
ከሠሞኑ ይፋ የተደረገ ሳይንሳዊ የጥናት ውጤት ግን፣ ፆም ለነፍስና ለመንፈሳዊ እርካታ ብቻ ሳይሆን፣ ለዓለማዊ ኑሯችን ለሥጋችንም ጭምር እንደሚጠቅም የተረጋገጠበት ነው። መፆም ራስን ማድከምና ለበሽታ ማጋለጥ እንደሆነ በተለምዶ ጥቂቶች ይናገሩ የነበረውን አስተሳሰብ ውድቅ ያደረገው ይህ የጥናት ግኝት፣ ኹሉም ሰው በፆመ ቁጥር ጥርት አድርጎ ማሰብን ጨምሮ ጤናማ ስሜት እንዲሰማውና መንፈሳዊ እርካታን በአንድ ላይ ማግኘት እንደሚችል ያመላከተ ነው።
ራሳችንን ወደ ፈጣሪያችን የምናቀርብበት መንገድ እንደሆነ በብዙዎች ዘንድ የሚታመንበት ፆም፣ ከክፉ ምግባር የምንርቅበት ብቻ ሳይሆን ከበሽታና ከመጥፎ አስተሳሰብ የሚከለክል እንደሆነም ይታመናል። ሰው የሚፈልገውና የሚመኘው ነገር ለመንፈሳዊ ዕድገቱ መሠናክል እንደሚሆነው ስለሚታመን፣ ፍላጎቱን መገደብና ሥጋዊ ፍላጎቱን ማስቀረት እንደፆም ስለሚወሰድ፣ ይህ መንፈሱንም ሆነ ሥጋውን የሚጎዳ ነገርን መቀነስ ጥቅሙ አጠያያቂ እንደማይሆን ይነገራል።
በሳይንሳዊ መንገድ፣ አንድ ሰው ሲርበው ምን ዓይነት ስሜት እንደሚሰማውና ምን ዓይነት የጠባይ ለውጥ እንደሚያመጣ ማወቅ ይቻላል። ውስጣዊ የሰውነት ለውጦችን እንዲሁም ውጫዊ ልዩነቶችን በማጥናት ምን ጥቅም እንደሚያስገኝ መለካት ይቻላል። እንደተመራማሪዎቹ ዕይታ፣ በፆም ውስጥ ያለ ሰው ከሚሰማው እርካታ በተጨማሪ፣ ረጋ ብሎ ማሰብ እንዲችል እና ብልሃት እንዲኖረው ያደርጋል።
ከአሪስቶትል ዘመን ጀምሮ መፆም ለጤና ይጠቅማል ስለሚባል ታማሚዎች በተለይ ከቀዶ ጥገና በፊት እንዲያከናውኑት ይመከር ነበር። አሁን ድረስ ለሚጥል በሽታም ሆነ ምግብ አልፈጭ እያለ ለሚያስቸግራቸው ፆም እንደሚጠቅም ባለሙያዎች ይናገራሉ። ለስኳር በሽተኞች፣ ለልብ ሕሙማን እና ለሪህ ታማሚዎች ሕክምና እንደሚያግዝም ተመራማሪዎች ይናገራሉ ሲል ‹ሳሎን› የተሰኘ ድረ-ገጽ ስለምርምር ውጤቱ አስነብቧል።
ከዓመታት በፊት ስለፆም የተደረጉ ጥናቶች እንደጠቆሙት፣ ሰውነት ምግብ እንዲያጥረው በተደረገ ቁጥር፣ እንዲሁም ከፍተኛ ካሎሪ ያላቸው ፕሮቲን ነክ ምግቦችን ትተው ወደ ካርቦሃድሬት በማዘውተር ሰዎች አመጋገባቸውን ከቀየሩ ሰውነታቸው ውስጥ የሚፈጠር ኬሚካል ደስተኛ እንደሚያደርጋቸው ነው። ‹ኢታኖል› የተሰኘውን አልኮል ከመውሰድ ጋር እምብዛም ልዩነት የሌለው ደስታ ይሰጣል ብለው ሳይንቲስቶቹ ቢናገሩም፣ የኃይማኖት መሪዎች ግን ‹ሀሴት› ብለው የሚጠሩትን ውስጣዊ ደስተኛነት እንደሚያጎናፅፍ ይናገራሉ።
‹ኒውትሪየንትስ› በተሰኘው የሆላንድ መጽሔት ላይ ስለፆም ጠቃሚነት በወጣ የጥናት ውጤት ላይ እንደተገለፀው፣ ቢያንስ ለስድስት ወራት እያቆራረጡ የሚፆሙ ሰዎች ስሜታቸው ጥሩ እንደሚሆን ተረጋግጧል። ይህ ዓይነት ጥናት ሲካሄድ የመጀመሪያው ሳይሆን ከዚህ በፊት መሠል ጥናቶች በቻይና እና በተለያዩ አገራት ተካሂደዋል። የተለያዩ ኃይማኖቶች የሚያደርጉትን የፆም ሒደት በመከተል ጥናት ተደርጎ እንደሚታመነው፣ ፆም ለነፍስ ብቻ ሳይሆን ለሥጋም/ለሰውነትም ጠቃሚ እንደሆነ ተነግሯል።
በጥናት እንደተረጋገጠው ፆም ሰዎች ድብርት እንዳይሰማቸው፣ እንዳይናደዱ፣ ውጥረት እንዳይሰማቸው፣ ግራ መጋባት እንዳያጋጥማቸው ከማድረጉ ባሻገር፣ አእምሮ ውስጥ ‹ዶፕሚን› የተሠኘው ንጥረ ነገር እንዲመነጭ በማድረግ በተለይ ዕድሜያቸው በገፋ ሰዎች ላይ የደስታ ስሜት እንዲመጣ ያደርጋል።
ይህ የፆም ጥቅም ከሰው ሰው የተለያየ ስለሆነ፣ በባለሙያዎች ዘንድ አሁንም አከራካሪ እንደሆነ ይነገራል። ከፆም ዓይነቶችና መንገዶች አኳያ የሚያመጣው ተጽዕኖም የተለያየ እንደሆነ የሚታመን ሲሆን፣ በአብዛኛው ግን አሁን እንደተጠናው ጠቃሚነቱ ላይ ይስማሙበታል።
በአንጻሩ ብዙዎች ፆም የሚያስገኘው ጥቅም ላይ ቢስማሙም፣ ጥቂቶች ደግሞ የማይቆይና የማይዘልቅ ስለሆነ በተከታታይ መሆን እንዳለበት ይናገራሉ። መፆም ማለት ራስን ከአቅም በላይ ማስራብ እንዳልሆነ የሚናገሩት ተመራማሪዎቹ፣ ጉዳት እንዲያስከትል ሳይሆን ሠውነትም ሆነ መንፈስ እንዲጠቀምበት መሆን አለበት ይላሉ።
ፆም የማሰብ ብቃትን እንደሚያጎለብት የሚናገሩት ሳይንቲስቶቹ፣ ንፁኅ የሆነ አእምሮ ይፈጥራል፣ ያለምንም ውጥረት ጥሩ ጥሩ እሳቤዎች እንዲኖሩ ያደርጋል ይላሉ። በመደበኝነት የሚፆሙና የካሎሪ መጠናቸውን የሚገድቡ ሰዎች ደግሞ የበለጠ ጤናማ ከመሆናቸው ባሻገር፣ ዕድሜያቸው በጨመረ ቁጥር ቶሎ እንዳይገረጅፉ ያደርጋቸዋል ተብሏል። ይህም ብቻ ሳይሆን ፆም የማስታወስ ብቃትን ለመጨመርም እገዛ እንደሚኖረው መታወቁ ተነግሯል። ለመርሳት በሽታ ሕክምናም ሊያገለግል እንደሚችል ጥቆማ የተሰጠ ሲሆን፣ ለወደፊቱ በምርምር የሚረጋገጥ ይሆናል ሲሉ አሳውቀዋል።
ለረጅም ጊዜ ሳይበሉ መቆየት ከመደበኛ ፆም አንፃር ምን ያህል የተለየ ጥቅም እንደሚያመጣ ገና አልታወቀም ያሉት ተመራማሪዎቹ፣ በዘርፉ የተለያዩ ጥናቶች እንደአስፈላጊነቱ ተደርገው ይፋ መደረግ እንደሚኖርባቸው ጠቁመዋል። ፆም ብዙ ያልታወቁ ጠቀሜታዎች እንደሚኖሩት ቢገመትም፣ እስከ አሁን ግን በእርግጠኝነት አስተሳሰብ ላይ በጎ የሆነ ለውጥ በማምጣት የሚፆመውን ሰው እንደሚጠቅም ለማወቅ ተችሏል።
አንድ ሰው ሲፆም የሚያገኛቸው ጥቅሞች እንደሚፆመው የሰዓት ልዩነት ይለያያል የሚሉ ተመራማሪዎች በበኩላቸው፣ በመጀመሪያው ወቅት የተከማቸ ስብን ለማስወገድ ይረዳል ይላሉ። በቀጣይነት በደም ውስጥ የሚገኝ የስኳር መጠን እንዲቀንስ ያደርጋል ብለዋል። አክለውም ‹ታይፕ2› የተሠኘውን የስኳር በሽታ ለመከላከል ያግዛል ሲሉም ያስረዳሉ። በመቀጠል የበለጠ ሰዓት በተፆመ ቁጥር አስተሳሰብ የተቃና እንዲሆን በማድረግ ሰዎች በአንድ ጉዳይ ላይ ማተኮር እንዲችሉ እንዲሁም ያልተረበሸ አእምሮ እንዲኖራቸው ያደርጋል።
ለ20 ሠዓት ያለማቋረጥ መፆም የሚችሉ ደግሞ ሰውነታቸው ራሱን በቀላሉ የማደስና ቁስል ቶሎ የመጠገን ዕድል እንዲኖረው ያደርጋል ሲሉ ስለፆም ጠለቅ ያለ ጥናት ያደረጉ ባለሙያዎች ሲናገሩ ይሰማል። ‹ዶክተር ክሊትዝ› የተሠኘው ድረ-ገጽ ላይ ስለአጠቃላይ የፆም ጥቅም የተዘረዘረ ሲሆን፣ ከላይ ከጠቀስናቸው ባሻገር ሰውነት ያለምንም እንከን ተግባሩ እንዲሳለጥና ውጤታማ እንዲሆን፣ ጤነኛና ደስተኛ ለመሆን ያስችላል ሲሉ ያመለክታሉ።
ቅጽ 4 ቁጥር 176 መጋቢት 10 2014



