በአንድ ዓመት በኩንታል አራት ሺሕ ብር ጨምሯል
የዶሮ መኖ ዋጋ ከፍተኛ ጭማሪ ማሳየቱንና የግብዓት ዕጥረት መከሠቱን ተከትሎ ዶሮ አርቢዎች ሥራ እያቆሙ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ዶሮ አርቢዎችና አቀነባባሪዎች ማኅበር ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።
የዶሮ መኖ የግብዓት ዕጥረት ከማገጣሙ ባሻገር፣ ዋጋውም በመወደዱ የሥራው አዋጭነት እየቀዘቀዘ በመምጣቱ ዶሮ አርቢዎች ሥራቸውን እያቋረጡ ስለመሆናቸው የማኅበሩ ሥራ አስኪያጅ ብርሃኑ ሚሊዮን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
የመኖ የግብዓት ዕጥረትና የዋጋ መጨመር አለ የሚሉት ብርሃኑ፣ ከሦስት ወር በፊት አራት ሺሕ ብር ሲገዙት የነበረውን አንድ ኩንታል ፋጉሎ አሁን ላይ የሚገዙት አምስት ሺሕ ብር እንደሆነ ገልጸዋል። አያይዘው በአንድ ዓመት ውስጥ የመኖ ዋጋ ከዕጥፍ በላይ እንደጨመረም የገለጹ ሲሆን፣ ከዓመት በፊት መቶ ኪሎ ወይም አንድ ኩንታል መኖ ይገዙ የነበረው አንድ ሺሕ አንድ መቶ ብር እንደ ነበር አስታውሰዋል።
አዲስ ማለዳ በጉዳዩ ላይ ከአንድ ዓመት በፊት በሠራችው ዘገባ፣ ዶሮ አርቢዎች አንድ ኩንታል በቆሎ አንድ ሺሕ አንድ መቶ ብር ይገዙ እንደነበር መዘገቧ የሚታወስ ነው።
በአንድ ዓመት ውስጥ የአንድ ኩንታል መኖ ዋጋ ከአንድ ሺሕ አንድ መቶ ብር፣ የአራት ሽሕ ብር ጭማሪ አስመዝግቦ፣ አሁን ላይ አምስት ሺሕ ብር መግባቱ ተመላክቷል።
በቆሎና አኩሪ አተር ለዶሮ መኖ ዋና ዋና ግብዓቶች መሆናቸውን የጠቆሙት የማኅበሩ ሥራ አስኪያጅ፣ እንቁላል ለማምረት ዶሮዎችን ብዙ መመገብ/ማብላት ግድ ቢልም፣ የመኖ ዋጋ ጭማሪው በሥራው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩን ተናግረዋል።
ብርሃኑ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት ከሆነ፣ የመኖ ዋጋ መጨመሩን ተከትሎ ብዙ ሰዎች ከሥራ እየወጡ ነው። ብርሃኑ ዶሮ አርቢዎች ከሥራው እየወጡ ነው ያሉ ሲሆን፣ ከ15 እስከ 20 የሚሆኑ የዶሮ ዕርባታ ድርጅቶች (ፋርሞች) ሥራ ማቋረጣቸውን ጠቁመዋል።
ዶሮ አርቢዎች ሥራ እያቋረጡ የሚወጡት የመኖውን ዋጋ መጨመርና የግብዓት ዕጥረቱን መቋቋም ስላቃታቸው መሆኑን ያብራሩት ሥራ አስኪያጁ፣ ሥራ አቋረጡ የተባሉት ከ15 እስከ 20 የሚሆኑ የዶሮ ዕርባታዎች (ፋርሞች) ከትልልቆቹ ድርጅቶች ብቻ ነው ያሉ ሲሆን፣ ከአነስተኛ የዕርባታ ድርጅቶችም ውስጥ በርካታ ሥራ ያቋረጡ እንደሚኖሩ ተናግረዋል።
በሌላ በኩል፣ ከኹለት ሳምንት በፊት በተጀመረው የዐቢይ ጾም ምክንያት የእንቁላል ዋጋ መቀነሱ የተገለጸ ሲሆን፣ የመሸጫ ዋጋው ለመኖ መግዣ ከሚወጣው ወጪ ጋር ሊመጣጠን እንደማይችል ነው የተነገረው። የእንቁላል ዋጋ በፍስክ ወቅት በዶሮ ዕርባታ ድርጅቶች በኩል ሰባት ብር ይሸጥ እንደነበርና አሁን ግን ወደ አምስት ብር ከአምሳ ሳንቲም ዝቅ እንዳለ ብርሃኑ ለአዲስ ማለዳ አመላክተዋል።
ጾም ከመግባቱ በፊት የእንቁላል ዋጋ ሰባት ብር ነበር ያሉት ብርሃኑ፣ በዚህም ከአንድ እንቁላል ብቻ ኹለት ብር ከአምሳ ሳንቲም ትርፍ ይገኝ ነበር። አሁን ግን አንድ እንቁላል አምስት ብር ከአምሳ ሳንቲም ተሽጦ ምንም ትርፍ የለውም ብለዋል።
አንዲት ዶሮ እንቁላል ለመጣል በመጀመሪያ ለአራት ወር ተኩል ከተመገበች በኋላ በምትጥለው እንቁላል ወጪውን መመለስ የሚቻል ሲሆን፣ ይህም ከአንድ እንቁላል ቢያንስ ከኹለትና ሦስት ብር ትርፍ ማግኘትን ይጠይቃል። አንዲት ዶሮ በአራት ወር ተኩል ውስጥ የምትመገበው 400 ብር ዋጋ ያለው መኖ መሆኑንም ብርሃኑ አስረድተዋል።
ችግሩን ለመቅረፍ ከሚመለከተው አካል ጋር በጋር እየሠሩ መሆናቸውን የጠቆሙት ሥራ አስኪያጁ፣ መንግሥት ለችግሩ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ሲሉም አሳስበዋል።
በአገራችን በብዛት የሚገኙ የእንቁላል ጣይ ዶሮ ዝርያዎች ዋይት ኮረኒሽ (የእንግሊዝ ዝርያ)፣ ብርሃማን (የሕንድ ዝርያ)፣ ዋይት ሌግሆርን (የጣሊያን ዝርያ) እንዲሁም ቦቨን ብራውን (የሆላንድ ዝርያ) እንደሆኑ ይነገራል።
በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ አዲስ የተሻሻለ የዶሮ ዝርያ ተገኘ – Addis Maleda
በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የዶሮ ክትባት እና ምርመራ መስጫ ላብራቶሪ ተከፈተ – Addis Maleda
በአገር ውስጥ ያሉ የዶሮ አርቢዎች ቁጥር ከግማሽ በታች ቀንሷል – Addis Maleda
ቅጽ 4 ቁጥር 176 መጋቢት 10 2014



