አገልግሎቱ ከቆመ ከአንድ ዓመት በላይ አስቆጥሯል
በአዲስ አበባ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ከመስቀል አደባባይ ወደ መገናኛ በሚወስደው የባቡር መንገድ ባምቢስ መሻገሪያ የሚገኘው የባቡር ትኬት መቁረጫ ስቴሽን አገልግሎት መስጠት ካቆመ ከአንድ ዓመት በላይ ማስቆጠሩን ተከትሎ ተገልጋዮቹ ወደ ሌላ ቦታ በመሄድ እየተጉላሉ መሆናቸውን ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።
የትኬት መቁረጫው በየካቲት 27/2013 ከሌሊቱ ስምንት ሰዓት ተነስቶ በነበረው የእሳት አደጋ መቃጠሉ የሚታወስ ሲሆን፤ ቅሬታ አቅራቢዎቹ የገለፁት ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በተጠቀሰው ቦታ ትኬት መቁረጥ አለመቻላቸውን ነው።
ቅሬታ አቅራቢዎቹ ለአዲስ ማለዳ የገለጹት፤ መካነ ኢየሱስ ህንጻ አጠገብ ያለው የባቡር ትኬት መቁረጫ ጣቢያ በወቅቱ ተከስቶ በነበረው የእሳት አደጋ ከመቃጠሉ በፊት ትኬት በመቁረጥ አገልግሎት ሲያገኙ የቆዩት በዚሁ ቦታ እንደነበር ነው። ነገር ግን የሚመለከተው አካል ለተፈጠረው ችግር መፍትሄ ባለመስጠቱ ምክንያት ከአንድ ዓመት በላይ በተጠቀሰው ቦታ አገልግሎት እያገኙ አለመሆኑን ነው የተናገሩት።
ከቅሬታ አቅራቢዎቹ መካከል ሳሙኤል ኡርዴታ የተባሉት ግለሰብ አገልግሎቱ መቋረጡን ተከትሎ ያላቸውን ቅሬታ፤ ‹‹ሰው በጣም እየተሰቃየ ነው። ባምቢስ መሻገሪያ ትኬት ሲቆርጡ የነበሩ በርካታ ሰዎች ነበሩ። አሁን ግን በመቋረጡ ምክንያት ብዙ ሰዎች እያማረሩ ነው›› ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
አገልግሎቱ ከተቋረጠ ከአንድ ዓመት በላይ ሆኖታል ያሉት ቅሬታ አቅራቢው፤ ባምቢስ መሻገሪያ የትኬት አገልግሎት ሲያገኙ የነበሩ በርካታ ሰዎች፤ ችግሩ ከተፈጠረ ወዲህ አገልግሎት የሚያገኙት ወደ ሌላ የትኬት መቁረጫ በመሄድ ነው ሲሉ የተመለከቱትን ጠቁመዋል።
ሳሙኤል አክለው የገለጹት የእሳት አደጋው በተከሰተበት ወቅት አንድ ትራንስፎርመር መቃጠሉን ሲሆን፤ ትራንስፎርመሩም እስካሁን (ይህ ዘገባ እስከተዘጋጀበት ጊዜ ድረስ) ጥገና እንዳልተደረገበት ነው።
እንደ ሳሙኤል ገለጻ ከሆነ፤ ከዚህ በፊት ባቡር ትኬት መቁረጫ ጣቢያው ጥገና እንዲደረግለት በጀት ተበጅቷል የሚል ጭምጭምታ ሰምተው እንደነበር የጠቆሙ ሲሆን፤ ጥገና ሲደረግበት ግን እንዳላዩ አረጋግጠዋል። በተያያዘም ቤታቸው ከትኬት መቁረጫ ቢሮው አጠገብ በተነሳው የእሳት አደጋ ከትኬት መቁረጫው አቅራቢያ የሚገኝ ቤታቸው ተቃጥሎባቸው እንደነበር ገልጸዋል።
ሌላኛዋ ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረጉት የሺወርቅ አንዱዓለም የተባሉት ግለሰብ በበኩላቸው አገልግሎቱ ከተቋረጠ እንደቆየ አንስተው፤ ትኬት ለመቁረጥ እየተቸገሩ መሆናቸውን ገልጸዋል። አስከትለውም ጉዳዩ ለወጣቶች ባይከብድም ለአዛውንቶች ግን ያስቸግራል ነው ያሉት።
እንደ ቅሬታ አቅራቢዋ ገለጻ ከሆነ፤ የችግሩ መፍትሄ አለመሰጠት ተሳፋሪዎቹ በእግራቸው ወደ ሌላ ቦታ መጓዛቸውን ተከትሎ በርካታ ተሳፋሪዎች በአንድ ቦታ በመሰባሰባቸው ወረፋ ለማግኝት እየተቸገሩ መሆናቸውንም ነው ማወቅ የተቻለው።
አዲስ ማለዳ በቦታው በአካል በመገኘት በተመለከተችው መሰረት፤ ቅሬታ አቅራቢዎቹ እንደገለጹት ባምቢስ መሻገሪያ የሚገኘው የባቡር ትኬት መቁረጫው ጥገና እንዳልተደረገለት ማረጋገጥ ችላለች።
አዲስ ማለዳ ለተነሳው ቅሬታ ያላቸውን ምላሽ ለማግኘት ወደ አዲስ አበባ ቀላል ባቡር ዋና ሥራ አስኪያጅ ሙሉቀን አሰፋ በተደጋጋሚ ስልክ ብትደውልም ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆኑም።
ፈቃደኛ ያልሆኑት አገልግሎት የማይሰጡ የባቡር ትኬት መቁረጫን በተመለከተ የሚነሳ ቅሬታ መኖሩን ከአዲስ ማለዳ ከሰሙ በኋላ፣ ጉዳዩን ወደ የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ኃላፊ መልሰዉታል። ኃላፊዋ አበበች ደርባም የሚመለከተው የአዲስ አበባ ቀላል ባቡርን ነው ሲሉ መልሰዋል።
አዲስ ማለዳ በተለያየ አጋጣሚ እንደታዘበችው፣ በተለያዩ አካባቢዎች ግልጽ ባልሆነ ምክንያት የተዘጉና አገልግሎት የማይሰጡ የትኬት መቁረጫዎች ይገኛሉ።
በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ባምቢስ መሻገሪያ የሚገኘው የባቡር ትኬት መቁረጫ የካቲት 27/2013 ከሌሊቱ ስምንት ሰዓት በተነሳው የእሳት አደጋ በመቃጠሉ የአንድ ሰው ሕይወት ማለፉ የሚታወስ ነው።
ቅጽ 4 ቁጥር 176 መጋቢት 10 2014


