የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕምባ ጠባቂ ተቋም መንግሥት የዜጎችን በሕይወት የመኖር መብት በተግባር ማረጋገጥ እንዳለበት አሳሰበ።
በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ያወጣው የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም፣ መንግሥት የሕግ የበላይነትን ለማስጠበቅ ከመቼውም በላይ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራ ውሳኔ ቢያሳልፍም፣ ችግሮቹ አሁንም እንደቀጠሉ ናቸው ብሏል። ‹‹ለዜጎች በሕይወት የመኖር መሠረታዊ መብት ትልቅ ስለሆነ፣ ያንን ማስጠበቅ የተግባራት ሁሉ ቀዳሚው ተግባር ሊሆን ይገባል›› ሲልም ተቋሙ ለመንግሥት ማሳሰቢያ ሰጥቷል።
የትኛውም መንግሥት ተቀዳሚ ተግባሩ የሕግ የበላይነትን ማስከበር እንደሆነ የጠቀሰው ተቋሙ፣ በተለይ የሽግግር ወቅት በሚሆንበት ሰዓት የሕግ የበላይነትን ማስከበር፣ የዜጎችን ሠላምና ደኅንነት መጠበቅ እጅግ አንገብጋቢ እና ወሳኝ ነው ብሏል። ዕምባ ጠባቂ በመግለጫው በዚህ ረገድ ባላፉት ጥቂት ዓመታት ግልጽ ጦርነት በተከፈተባቸው አካባቢዎችም ይሁን በአንዳንድ ጦርነት ባልተካሄደባቸው ቀጠናዎች በርካታ ዜጎች ተፈናቅለዋል፤ የአካል ጉዳትና ሞት ደርሷል፤ ንብረትም ወድሟል ብሏል።
ተቋሙ ትልቅ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ያለው ጉዳይ በአፋር፣ በትግራይ፣ በአማራ እና በቤንሻንጉል ጉምዝ እንዲሁ ተበትነው በተለያዩ አካባቢዎች ተጠልለው የሚገኙ ዜጎችን፣ ከክልሎች እና ከፌዴራል ተቋማት የተውጣጣ በዕቅድ የሚመራ ጥምር ኮሚቴ ወይም ግብረ ኃይል በማቋቋም ወደ ቀያቸው ተመልሰው በዘላቂነት ሊቋቋሙ የሚችሉበት ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚገባ አመላክቷል።
በሌላ በኩል፣ ባለፉት ሦስት ዓመታት የታዩት የሕግ የበላይነት አለመከበር ችግሮች፣ የኑሮ ውድነትና በመንግሥት ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ መፋዘዞች፣ እንዲሁም የሙስና ችግሮች ሁሉ በአንድ በኩል የመንግሥት ፖሊሲ ካለመኖር የተከሰቱ ናቸው። እንዲሁም ያሉት ፖሊሲዎችም ግልጽ ባለመሆናቸው የሚከሰቱ ናቸው ሲል ተቋም አስታውሷል። ብልጽግና ፓርቲ ባካሄደው ጉባኤ ላይ ያሳለፋቸውን ውሳኔዎች መሠረት በማድረግ፣ ኢትዮጵያ በግብርና፣ በትምህርት፣ በጤና፣ በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ በአጠቃላይ በማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ መስኮች የምትመራባቸው ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎችን በመንደፍ ተግባራዊ እንዲሆኑም ምክረ ሐሳብ አቅርቧል።
ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ በመጣው የኑሮ ውድነትን በመግለጫው ያካተተው የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕምባ ጠባቂ ተቋም፣ የኑሮ ሁኔታውን ለማረጋጋት በመንግሥት በኩል በጠቅላይ ሚነስትሩ የሚመራ የሚመለከታቸው የፌዴራል መሥሪያ ቤቶች፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና የኦሮሚያ ክልል መንግሥት የተካተቱበት የማክሮ ኢኮኖሚ ኮሚቴ ተቋቁሞ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን ጠቁሟል። 19.1 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪም መሠረታዊ ሸቀጦች (ወተት፣ ስንዴ፣ ፓልም የምግብ ዘይት እና ስኳር) ከታክስ ነጻ እንዲገቡ መደረጉ የሚበረታታ ቢሆንም፣ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ዘላቂ መፍትሔ ያስፈልጋል ብሏል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም በሕግ የተደነገጉ የሰዎች መብቶች እና ጥቅሞች በአስፈፃሚው አካላት መከበራቸውን በማረጋገጥ የሕግ የበላይነትን መሠረት ያደረገ ጥራት፣ ቅልጥፍናና ግልጽነት ያለው መልካም የመንግሥት አስተዳደር እንዲሰፍን የማድረግ ዋነኛ ዓላማን በመያዝ አስተዳደራዊ በደልን ለመከላከል፣ የቁጥጥርና ጥናት ሥራዎችን ማከናወን፣ የሚወጡ መመሪያዎች፣ ዉሳኔዎችና አሠራሮች ሕገ መንግሥቱን የማይቃረኑ መሆናቸውን መቆጣጠር፣ የተሻለ የመንግሥት አስተዳደርን ለማስገኘት ነባር ሕጎች ወይም አሠራሮች እንዲሁም መመሪያዎች እንዲሻሻሉ፣ አዳዲስ ሕጎች እንዲወጡ ወይም ፖሊሲዎች እንዲቀየሱ ማሳሰብ ከተሰጡት ሥልጣንና ተግባራት መካከል ናቸው።
ቅጽ 4 ቁጥር 176 መጋቢት 10 2014


