ሰኞ መጋቢት 12 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎትና ሳፋሪኮም-ኢትዮጵያ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር የኮንክሪት ምሰሶ ኪራይ ሥምምነት ተፈራርመዋል፡፡
ሥምምነቱን የፈረሙት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሽፈራው ተሊላና የሳፋሪኮም-ኢትዮጵያ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ዋና ሥራ አስፈፃሚ አንዋር ሶውሳ ናቸው፡፡
በፌርማ ሥነ-ሥርዓቱ ወቅት ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሽፈራው ተሊ፤ የተፈረመው የምሰሶ ኪራይ ሥምምነት የኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማቶችን ለቴሌኮም አገልግሎት ለመጠቀም የሚያስችል መሆኑን ገልፀው፤ መሰረተ-ልማቶችን በጋራ መጠቀም መቻሉ ጥራት ያለውና አስተማማኝ አገልግሎት ለመስጠት ያስችላል ብለዋል፡፡
ዋና ሥራ አስፈፃሚው አክለውም የኪራይ አገልግሎቱ በአገሪቱ የተዘረጉ የኤሌክትሪክ ምሰሶዎች በጋራ ለመጠቀም የሚያስችል ከመሆኑም በላይ የተቋሙን ገቢ ለማሳደግም ፋይዳው የጎላ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የሳፋሪኮም-ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አንዋር ሶውሳ በበኩላቸው፤ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ጋር አብረው ለመስራት ዕድሉ በማግኘታቸው ደስተኛ መሆናቸውን ገልፀው፤ የተፈረመው የምሰሶ ኪራይ የኹለቱን ተቋማት ሃብት በጋራ ለመጠቀም የሚያስችልና ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የምሰሶ ኪራይ ሥምምነቱ ዋና አላማ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የተዘረጉ የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት በተለይም ደግሞ የኮንክሪት ፖሎችን በጋራ ለመጠቀም የሚያስችል መሆኑን በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ወቅት ተገልጿል፡፡
ሥምምነቱ ተግባራዊ የሚደረገው በታላላቅ የአገሪቱ ከተሞች ላይ በተተከሉ የኮንክሪት ምሰሶዎች ላይ ሲሆን፤ ውሉን የፈረመው ሳፋሪኮም በሚያገኘው አገልግሎት በዓመት 988 ብር ከ70 ሳንቲም ለአንድ ምሰሶ ኪራይ የሚከፍል መሆኑን ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በተከላቸው የኮንክሪት ምሰሶዎች ኪራይ ተጨማሪ፤ ገቢ ማግኘቱ በእርጅና ምክንያት የወደቁና የዘመሙ የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶችን ማሻሻልና የመልሶ ግንባታ ሥራ ማከናወን የሚያስችለው መሆኑም ተገልጿል፡፡
በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የኹለቱን ተቋማት ዋና ሥራ አስፈፃሚዎችን ጨምሮ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ዶ/ር ኢንጅነር ጌታሁን መኩሪያና ሌሎች የኹለቱ ተቋማት ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች ተገኝተውበታል።
_____
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n




