አስኮራጅ ያልፈቀደው የሹመኞች ኩረጃ

0
1195

ባሳለፍነው ሳምንት መነጋገሪያ ከሆኑ ጉዳዮች አንዱ ባለሥልጣናት በደረሰ ሰብል መካከል ጠረጴዛ ተዘርግቶላቸው፣ ወንበር ተደርድሮላቸው የተካፈሉት ማዕድ(ውኃ) ነው። ይህ የሹመኞች ስብስብ በራሱ ቁጣን ባያስከትልም፣ አንድ አካባቢ ድርቅ ሁኖ፣ ሌላው በረሃብና ጦርነት እየታመሰ ባለበት በዚህ አስከፊ ወቅት እህል አስረምርመው ነው ወይስ አስነስተው በሚል ዓላማቸውን የተቹ ነበሩ።

ዝናብ እየመጣ ባለበት በዚህ ጊዜ፣ ዙሪያቸውን ባልተሰበሰበ የደረሰ እህል ተከበው ያለምንም መጠለያ እንደስብሰባ ጠረጴዛ ክብ ሠርተው የነበረበትን ሒደት የሚያሳይ ምስል በወጣበት ጊዜ አድናቆትን አላተረፈም ነበር። ለምን አደረጋችሁት የሚል ሰው በዝቶ ባይሰማም፣ አብዛኞች ግን ሌላ አገር ከዚህ ቀድሞ በተመሳሳይ የተደረገን ምስል አስደግፈው ኩረጃ በመሪዎች ጭምር መኖሩን አስመርኩዘው ልምዱን ነቅፈውት ነበር። በበቆሎ መካከል የተደረገ ግብዣን አመሳስሎ ከመሰብሰብ፣ በቆሏቸውን ያመረቱበትን ዘመናዊ ሒደት ቢኮርጁ ነበር ጥሩ የሚሆነው እያሉ በተግባሩ ላይ የተዘባበቱም ነበሩ።

“ሌባ ላመሉ ዳቦ ይልሳል” የሚለውን ብሒል ብዙዎች ሳንረዳው ብንጠቀምበትም፣ እንዲህ ዓይነት ያለጥቅም የሚኮረጅ ተግባር ሲታይ ግን ትዝ ይላል እያሉ ሒደቱ ላይ ያፌዙም ተሠምተዋል። በባለቤትነት መብት (ኮፒ ራይት) እንዳያስጠይቁን ብለው ምስሉን ከማሠራጨት እንቆጠብ በሚል፣ የመንግሥት አካላት አውቀውም ይሁን ሳያውቁት በተዘጋጀው መርሃ ግብር ላይ መሳተፋቸውን አነጻጽረው በትችት አሳይተዋል።

ኩረጃውን ያስፈፀመው ግለሰብ ምነው ይህን ብቃቱን ተጠቅሞ ወደአደጉት አገራት ተጉዞ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በመኮረጅ ከአገራት ተርታ የማያሳልፈን ሲሉም ኮራጅንም ቢሆን ለበጎ እንጠቀምበት ያሉም ተሰምተዋል። የስብሰባው ዓላማ ለብዙዎች ግልፅ ባይሆንም፣ ድርጊቱ ከውጭ አገር ተኮርጆ መደረጉ ላይ ትኩረት ተሠጥቶ መነጋገሪያ፣ መቀለጃም ሆኖ ነበር።

ይህ ልምድ አዲስ አለመሆኑን የሚናገሩ የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ደግሞ፣ ከዚህ በፊት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ‹ፑሻ አፕ› ማሠራታቸውን፣ መኪና መንዳት መውደዳቸውን፣ መንገድ ላይ ተኮራምተው ተቀምጠው እግራቸው ላይ በላፕቶፕ መሥራታቸውን፣ እንዲሁም የተለያዩ ኩረጃ የመሰሏቸውን ድርጊቶች እያነሱ ከሰብሉ መሃል ከነበረው ስብሰባ ጋር አገናኝተው ጽፈዋል።

በሌላ በኩል፣ አንዳንዶች ሒደቱን ተመርኩዘው በስላቅ ተከታታዮቻቸውን ሲያዝናኑም ነበር። አንድ ስሙን መግለጽ የማያስፈልግ ገጣሚ ስለአዝመራው ሲፅፍ፣ ይህን የመሰለ ሰብል ለእኔ ቢሰጠኝ ኑሮ ከነአረሙ ነበር የማጭደው ሲል፣ ከስንዴው መካካል ስለሚበቅል እንክርዳድ የተነገረን ብሒል አስደግፎ ለሕዝብ አድርሷል።

ያም ተባለ ይህ፣ ኩረጃ በተማሪ እንኳን ቢሆን የማይመከር እንደመሆኑ፣ ፈተናውም ሆነ ሒደቱ ድብቅ ባልሆነበት ኹኔታ ሳይናገሩ ሐሳብን ሰርቆ መጠቀም ተገቢ እንዳልሆነ ብዙዎች ይስማሙበታል። አባት ለልጁ ውሸትን ሲያስተምር፣ “ሠማይ ላይ ጤፍ ሲወቃ አየህ?” ሲለው፣ “እብቁ አይኔ ውስጥ ገባብኝ” ብሎ አባቱን ካስደመመው ልጅ የሚያስከነዱ ተማሪዎች ባሉበት ዘመን ላይ እንደመሆናችን፣ ሽምጥጥ አድርገው ከሚወቃው ጤፍ ቀዩና ነጩ ይህን ያህል ነው ማለታቸው አይቀርም።


ቅጽ 4 ቁጥር 177 መጋቢት 17 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here