ሥራ መሥራት አለባት። የልጇ አባት አጠገባቸው ስለሌለና ሊረዳትም በሚችልበት ቅርበት ባለመሆኑ፣ ልጇን ከወለደች እለት ጀምሮ ኑሮን ለብቻዋ መግፋትን ለምዳዋለች። ሥራው፣ የቤት ኪራይ ቀን ጠብቆ መክፈል፣ በልቶ ለማደር የሚያስችል ገቢን ማምጣትና የመሳሰለውን ለእርሷ ቀላል ጉዳይ ይሆን ነበር። ነገር ግን ኦቲዝም ያለባትን ልጇን ለማን ጠብቁልኝ ብላ አደራ ትሰጣለች? የትስ ታቀምጣታለች? ማን ይጠብቅላታል?
አማራጭ አላገኘችም። የምሳሳላት ልጇ ላይ ምንአልባት ጨካኝ የሚያስብላትን አካሄድ ተጠቀመች። ጠዋት ከቤት ወደ ሥራ ለመሄድ ስትወጣ፣ የልጇን እጅና እግሮች በብረት ሰንሰለት አስራ፣ ልብስ ማጠቢያዎቿን የምታስቀምጥበት ጎማ (የመኪና ጎማ) ሥር የሰንሰለቱን ማሰሪያ አድርጋ ትሄዳለች።
የኒያ ፋውንዴሽን ጆይ የኦቲዝም ማዕከል መሥራች የነበሩት ዘሚ የኑስ ነበሩ ከአራት ዓመት ገደማ በፊት ይህን ታሪክ ያወጉኝ (ለዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ)። ከኦቲዝም ጋር የሚኖሩ ልጆችና ወላጆቻቸው ምን ያህል ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ እንደሆኑና የችግሩን ግዝፈት ለማስረዳት የመረጡት ታሪክ ነበር።
ሕልማቸውም እንዲያ ያለችውን፣ በልጇ ኦቲስቲክ መሆን የተነሳ ከሰው መገለል፣ ከማኅበረሰብ መነጠል የገጠማትን እናት፤ በአጠቃላይም የሕይወት ትግል የከበዳቸውን ወላጆች ማገዝና ኦቲስቲክ የሆኑ ልጆችም የሰውነት መብታቸው እንዲከበር ማድረግ ነበር። ለዚህም የኒያ ፋውንዴሽን ጆይ ኦቲዝም ማዕከልን አስገንብቶ ፍጻሜውን ለማየት በእጅጉ ይጓጉ ነበር።
ዘሚ አሁን በአካለ ሥጋ አብረውን ባይገኘኙም፣ ሕልምና ርዕያቸውን የሚያስቀጥሉ ልጆችን ያገኙ ይመስላል። ማዕከሉም ይህ እርግጥ መሆኑን ለማሳየት 20ኛ ዓመቱን ዘንድሮ ሲያከብር በቅድሚያ 9616 አጭር የጽሑፍ መልዕክት ገቢ ማሰባሰቢያን ይፋ አድርጓል። በቀጣይም የማዕከሉን ግንባታ ለማገዝና ለማፋጠን የደም ልገሳን ጨምሮ የእግር ጉዞ እንዲሁም የግንባታ ዕቃዎች በዓይነት የሚለገሱበትን መርሃ ግብር አሰናድቷል።
ኦቲዝምና የሰዎች አመለካከት
ሚያዚያ ወር ዓለም ዐቀፍ የኦቲዝም ቀን የሚታሰብበት ወር ነው። ባሳለፍነው ዓመት የወጣ ዘገባ እንደሚያስረዳው፣ ከ57 ሰዎች መካከል አንድ ሰው ኦቲስቲክ ይሆናል። በዚህም ከሴቶች ይልቅ ወንዶች የበለጠ ተጋላጭ ናቸው።
ኦቲዝምን ብዙዎች የኃጢያት ውጤት ወይም እርግማን አድርገው ይቆጥሩታል። ይህም የግንዛቤ ዕጥረት ነው። በዛ ላይ ጉዳዩ ወደ መገናኛ ብዙኀን ቢወጣም ላግዛችሁ ብሎ የሚደግፍ በብዛት አይገኝም። ለኦቲስቲክ ልጆች የተሠሩ ትምህርት ቤቶች በጣት ቁጥር እንኳ አይሞሉም። የግለሰብ አቅም ውስን በመሆኑም የመንግሥት ተሳትፎና ኃላፊነትን መወጣት የግድ ይላል።
በጉዳዩ ላይ ሐሳብ የሚሰጡ ባለሙያዎች ችግሩ ላይፈታ የቻለው በግንዛቤ ዕጥረት እንደሆነ ይናገራሉ። የግንዛቤ ዕጥረቱ ከመንግሥት አስፈጻሚዎች ጀምሮ የሚስተዋልና፣ በኦቲዝም ላይ ብቻ ሳይሆን በአካል ጉዳተኝነት ላይም የሚታይ መሆኑ እሙን ነው።
የኒያ ፋውንዴሽን ጆይ የኦቲዝም ማዕከል የቦርድ ሰብሳቢ ናቸው፤ ሰሃራ ሐሰን። ማዕከሉ ባሳለፍነው ረቡዕ መጋቢት 14/2014 የማዕከሉን 20ኛ ዓመት፣ እንዲሁም 14ኛውን የዓለም የኦቲዝም ቀንን በተመለከተ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ባደረጉት ንግግር ይህ ችግር በቅድሚያ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ነው ሲሉ አንስተዉታል።
‹‹ኦቲዝም በአገራችን በአግባቡ ተደራሽ ካልተደረጉ የአእምሮ ዕድገት እክል ችግሮች ውስጥ ዋነኛው ነው። በአገራችን ከዚህ ዕክል ጋር የሚኖሩ ከአንድ ሚሊዮን የማያንሱ ሕጻናትና ወጣቶች፤ ተገቢ የሆነ የትምህርት፣ የጤና፣ የሥነልቦና እንዲሁም ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ክትትልና ድጋፍ አያገኙም። ስለዚህም ቤተሰብ፣ ወላጆች በተለይም እናቶች ለከፍተኛ እንግልት እንዲጋለጡ ሆነዋል›› ብለዋል።
ከዚሁ ጋር አያይዘው በኢትዮጵያ ያለውን የግንዛቤ አናሳነት በመጥቀስ፣ አሁን ከኦቲዝም ጋር የሚኖሩ በርካታ ልጆች በየቤቱ ተቀልፎባቸው፣ ታስረው፣ ከማኅበረሰብ ተገልለው፣ የፈጣሪ ቁጣ ነው እየተባለና የተኮነኑና የተረገሙ ተደርገው በመታየት ውስጥ ኑሯቸውን በመግፋት ላይ ናቸው ብለዋል።
ይህን ችግር ለመቅረፍም በጉዳዩ ላይ እገሌ ከእገሌ ሳይባል መንግሥትና የኃይማኖት ተቋማትን ጨምሮ ኹሉም እንዲሳተፉና፣ ከኦቲዝም ጋር የሚኖሩ ልጆች መጪ ሕይወታቸው ብሩህ እንዲሆን ጠይቀዋል። ይልቁንም ግንዛቤ መፍጠር ላይ ይበልጡን እንዲሠራ ሲሉ አሳስበዋል።
ስለ ማዕከሉ
በኒያ ፋውንዴሽን የጆይ ኦቲዝም ማዕከል፤ ከ20 ዓመታት በፊት ኦቲዝምን በተመለከተ በቂ እውቀት በሌለበት ወይም ጨርሶ ምንም ግንዛቤ ባልነበረበት ወቅት የተቋቋመ ድርጅት ነው። ማዕከሉ ‹ግንዛቤ በጣም ወሳኝ ነው› የሚል መርህ አለው። ኦቲዝምን መረዳት ቀዳሚ ዕርምጃ እንደሆነም ነው በማዕከሉ የሚታመነው። በዚህና ተያያዥ በሆኑ ሥራዎች ኦቲስቲክ ለሆኑት ልጆች ድምጽ በማሰማት፣ የግንዛቤ ለውጥ እንዲመጣ እና ታስረው የነበሩ እንዲወጡ ጥሯል፤ አስችሏልም።
የማዕከሉ የቦርድ ሰብሳቢ ሰሃራም ምንም እንኳ ፈተናዎች ባይጠፉም ስኬቶችም እንደነበሩ አንስተዋል። በዚህም ለበርካታ ሕጻናትና ወጣቶች አገልግሎት በመስጠት፣ ለወላጆችም እፎይታ እንዲያገኙ በማገዝ፣ በኢትዮጵ የኦቲዝም ግንባር ቀደም አገልግሎት ያበረከተ ተቋም ነው ብለዋል።
ማዕከሉ በአንድ ነገር ያምናል፤ ኦቲስቲክ የሆኑ ልጆችን ባለሙያ በማድረግ። ይህንንም ተስፋ ሳይቆርጡ በማሠልጠን እና በማስተማር ባሳለፍነው ዓመት አምስት ልጆች ወደ መደበኛ ትምህርት እንዲገቡ አድርጓል። 60 እናቶች ደግሞ የራሳቸው ገቢ የሚያገኙበት መንገድ ተመቻችቶላቸው ነበር።
ዘንድሮ ደግሞ ዐስር ልጆች ይመረቃሉ። እነዚህ ልጆች አምራች እንደሆኑና እንደሚችሉ ለማሳየት ይህ ጥሩ አጋጣሚ እንደሆነ ሰሃራ አስረድተዋል። መንግሥትም ለእነዚህ ልጆች የሥራ ዕድል ተጠቃሚ የሚሆኑበትን አሠራር እንዲያበጅ ለሚመለከተው ኹሉ ጥሪ አቅርበዋል።
አክለውም እንዲህ አሉ፤ ‹‹የእነዚህ ዐስር ተማሪዎች መመረቅ ለእኛ ትልቁ ድላችን ነው። ዛሬ እነዚህ ልጆች ኅብረተሰቡ ጋር ተቀላቅለው መሥራት መቻላቸው፣ የዘሚም የእኛም ትልቁ ሕልም ዕውን የሆነበት ነው።››
ይህን ሥራ ለማስቀጠል ነው እንግዲህ በዓይነቱ በአፍሪካ የመጀመሪያ እንደሚሆን ይጠበቃል የተባለለት የኦቲዝም ልኅቀት ማዕከል ግንባታ በሒደት ላይ ነው። ይህን አስፈጽሞ ከግብ ለማድረስ ነው፣ ማዕከሉ በኻያኛ የምሥረታ በዓሉ ላይ የገቢ ማሰባሰቢያ 9616 ይፋ ያደረገውና የተለያዩ መርሃ ግብሮች እንደሚኖሩ ያስታወቀው።
የኦቲዝም ቀን በኢትዮጵያ ሲከበር ለ20ኛ ጊዜ ሲሆን በዓለም ዐቀፍ ደግሞ ለ14ተኛ ጊዜ ነው። ይህም የሆነበት ምክንያት ኒያ ፋውንዴሽን ጆይ የኦቲዝም ማዕከል በቀዳሚነት ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጥ የኦቲዝም ቀን እንዲከበር በማስጀመሩ ነው። የ2014 የዓለም ኦቲዝም ቀን ‹‹ከኦቲዝም ጋር ያሉ ዜጎች ወደ ሥራ የመሠማራትና የመካተት መብት ይረጋገጥ›› በሚል መሪ ሐሳብ ይታሰባል።
ቅጽ 4 ቁጥር 177 መጋቢት 17 2014



