አርብ መጋቢት 16 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) በአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት እና በአስፈፃሚው አካል መካከል የዕቅድ ስምምነት የፊርማ ሥነ ሥርዓት ተከናውኗል፡፡
የአዲስ አበባ ምክር ቤት የህዝቡን ውክልና ሥራዎችና አስፈፃሚውን የመከታተልና የመቆጣጠር በአግባቡ መስራት እንዲያስችለው የቋሚ ኮሚቴዎችን አደራጅቶ ወደ ሥራ መግባቱ ይታወቃል፡፡
በመሆኑም የምክር ቤቱ አስፈፃሚውን የመከታተልና መቆጣጠር ስልጣን ተግባራዊ ለማድረግ ብሎም የተጠያቂነትን ሥርዓት ለማስፈን ይረዳ ዘንድ በምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴዎችና በአስፈፃሚው አካላት (የቢሮ ሃላፊዎች ) መካከል የተቋማቱን እቅድ መሰረት ያደረገ የሥምምነት ፊርማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ እና የአዲስ አበባ ምክር ቤት አፈጉባኤ ቡዜና አልቃድር በተገኙበት ተካሂዷል፡፡
ይህ በዛሬው ዕለት የተቋማት ሀላፊዎች እና አስፈጻሚ አካላት ጋር ያደረጉት የፊርማ ሥነ ሥርዓት ቀዳሚ ዓላማ ሥራን ቀጥሮ ሰጥቶ ቆጥሮ የመረከብ አሠራር ሥርዓትን ተግባራዊ የሚድረግ፣ ምን ተግባር መቼ እና በምን ያህል በጀት እንደሚከናወን ቀድሞ አውቆ ክትትል ለማድረግና ሪፖርት ለመጠየቅ የሚያመች እንዲሁም ለአስፈጻሚው ምክር ቤት አባል ልክ እንደ ማንቂያ ደወል ሆኖ የሚያገለግል ነው ተብሏል፡፡
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በፊርማው ሥነ ሥርዓት ላይ እንደተናገሩት ዛሬ ያደረግነው ሥምምነት ለይስሙላ የሚደረግ ሳይሆን አስፈጻሚውን አካል ለመቆጣጠር የሚያስችል ዓላማ ያነገባና ሥራን በተገቢው መንገድ ለማከናወን የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡
ምክር ቤቱና ሕዝባችን የጣለብንን ኃላፊነት በተሟላ እንድንፈጽም የሚያስችል የተጠያቂነት ሥርዓትን ከንግግር ባለፈ መሬት ላይ ለማውረድ የሚረዳ ፤ የተሻለ የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ለምክር ቤቱ እንድናቀርብ የሚያስችለንም ነው ማለታቸውን ከከንቲባ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
____
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n








