የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት የኢፌዴሪ መንግስት ለሰብዓዊነት ሲባል ግጭት ለማቆም መወሰኑን እንዳስደሰታቸው ገለፁ

0
1334

አርብ መጋቢት 16 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ ክልል ለተቸገሩ ዜጎች የሚደርሰውን ሰብዓዊ እርዳታ በፍጥነት ለማቅረብ እንዲያስችል ግጭት ለማቆም መወሰኑን እንዳስደሰታቸው የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት ዛሬ ባወጡት መግለጫ ገለፁ።

የህብረቱ ሊቀመንበር የትግራይ ክልላዊ መንግስት የሰብአዊ ዕርቅ ሥምምነት ለማድረግ ከመንግስት የቀረበውን ሃሳብ መቀበሉን የሰጠውን መግለጫ ማስታወቁ እንዳስደሰታቸውን በመግለፅ፤ ይህም ሥምምነት ጦርነቱ አፋጣኝ እንዲቆም ስለሚያደርግ እንደሚደግፉትም ተናግረዋል።

ሙሳ ፋኪ አክለውም፤ ለጋሽ ማህበረሰቡ እና ግብረሰናይ ኤጀንሲዎች የትግራይ፣ የአማራ እና የአፋር ክልሎችን ጨምሮ በሁሉም የተጎዱ ክልሎች ያለውን አስከፊ ሰብዓዊ ችግርን ለመቅረፍ የሚያደርጉትን ጥረት አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።

የተቸገሩትን ሁሉ ለማድረስ ሁሉም አጋር አካላት የሰብዓዊ እርዳታ ጥረቶችን እንዲያሳድጉም ሊቀመንበሩ ጠይቀዋል።

ሊቀመንበሩ የግጭቱ ተዋናይ ወገኖች በድርድር ዘላቂ የሆነ ሁሉን አቀፍ የተኩስ አቁም እንዲያደርጉና በዚህ ግብ ላይ ውይይት እንዲያደርጉም በመግለጫቸው ጠይቀዋል።

በዚህ ረገድ ሊቀመንበሩ የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት እና የአፍሪካ ሕብረት የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ መልዕክተኛ ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ ከፓርቲዎች እና ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅርበት በመስራት ግጭቱን በፍጥነት ለመፍታት የሚያደርጉትን ጠንካራ ጥረት አጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል።

_________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here