አርብ መጋቢት 23 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) ትላንት ዋስትና የተፈቀደላቸው የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ አባላት እና የአዲስ አበባ ወጣቶች ዛሬ የዋስትና መብታቸው ተሸሮ ተጨማሪ የ10 ቀን የጊዜ ቀጠሮ እንደተሰጠባቸው ፓርቲው አስታወቀ፡፡
በእነ ደረጀ ይበይን መዝገብ ቀጠሮ ተይዞላቸው የነበሩት የአዲስ አበባ እና የባልደራስ ወጣቶች ትላንት በነበረው የጠዋት ችሎት የ7 ሺህ ብር ዋስ ተፈቅዶላቸው የነበረ ሲሆን፣ ፖሊስ ከሰዓት በኋላ ይግባኝ አቅርቦ፤ ጉዳዩ ዛሬ ጠዋት ታይቷል፡፡
ፖሊስ ዛሬ ባቀረበው ክርክር፣ ተከሳሾችን የሚመለከት ምርመራ አለማጠናቀቁን፣ በምርመራ ሂደት ያገኛቸውን ማስረጃዎች በባለሙያዎች እያስተነተነ መሆኑን፣ ይህም ጊዜ የሚጠይቅ መሆኑን በመግለጽ ተጨማሪ የ14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ እንዲሰጠው ጠይቋል፡፡ ትላንት የነበረው ችሎት የሰጠው የዋስትና መብት አግባብ አይደለም በማለት ተቃውሟል፡፡
የተከሳሾች ጠበቆች በበኩላቸው፣ እስረኞቹ ለ1 ወር የሚጠጋ ጊዜ በእስር ላይ እየተንገላቱ መሆናቸውን፣ ፖሊስ በተደጋጋሚ የሚያቀርበው ምክንያት ተመሳሳይ መሆኑ ምርመራው ከልብ እየተሰራ አለመሆኑን እንደሚያመላክት፣ የባለሙያ ትንታኔ ያስፈልጋል የተባለው ደግሞ፣ የተከሳሾቹን በእስር መቆየት የማይፈልግ መሆኑን፣ ምስክሮች የተባሉትም ፖሊሶች እንደመሆናቸው መጠን መርማሪዎች በፈቀዱ ጊዜ ከጎናቸው ሊያገኙዋቸው የሚችሉ በመሆኑ የዋስትናው መብት ሊከበር እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡
ፍርድ ቤቱም የፖሊስን አቤቱታ በመቀበል፣ የሥር ፍርድ ቤቱ የሰጠውን የዋስትና መብት በመሻር፣ ተከሳሾቹ ለተጨማሪ 10 ቀናት እስር ቤት ሆነው ፖሊስ ምርመራውን እንዲያካሄድ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡
በአባ ሳሙኤል “የለበስነውን የአድዋን ቲሸርት አናወልቅም” በማለታቸው ፍርድ ቤት እንዳይቀርቡ የተከለከሉ እስረኞች ቁጥር ዛሬ ወደ 6 ማደጉንም ባልደራስ አስታውቋል።
ትላንት ማለዳ አራት እስረኞች የአድዋን ቲሸርት በማድረጋቸው ፍርድ ቤት እንዳይቀርቡ ተከልክለው የነበረ ሲሆን፣ ዛሬ ደግሞ ዳኛቸው ጉደታ /ቻቻ/ እና ዘካሪያስ ቶራ የተባሉ ኹለት የአዲስ አበባ ወጣቶች የአጼ ምኒልክ እና አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ሰንደቅ ዓላማ ያለበትን የአድዋ ክብረ በዓል ቲሸርት ለብሰው ወደ ፍርድ ቤት እንዳይሄዱ መከልከላቸውን ፓርቲው ለአዲስ ማለዳ በላከው መግለጫ ላይ ገልጿል፡፡
_____________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n



