ውጤትን መሠረት ያደረገ የድጎማ መርሀ ግብር አደጋ ላይ ይጥላል ተባለ

0
362

ምዕራባውያን ለጋሾች ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ባላቸው አገሮች የትምህርት ዘርፍ ድጋፍ የሚሰጡበት ውጤት ተኮር የድጎማ መርሃ ግብር (Programme for Results) ውጤታማነቱ እንደታሰበው እንደማይሆን ተነገረ።
በመጋቢት 21/2014 በካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ የወጣው አዲስ ጥናት በውጤት ላይ የተመሠረተ ‹‹የፋይናንሲንግ ፓኬጅ›› የሚጠበቀውን ያህል ውጤታማ እንደማያደርግ የኢትዮጵያን ተሞክሮ በመፈተሽ መታወቁ ተነግሯል።

ኢትዮጵያን ለመሳሰሉ ድሃ አገራት የሚሰጥ የትምህርት ሥርዓትን ለማገዝ የሚደረጉ ድጎማዎች ቅድመ ሁኔታዎችን ያስቀመጡ እንደሆኑ የተጠቆመ ሲሆን፣ ለጋሾች ድጋፋቸውን ከማድረጋቸው አስቀድሞ የትምህርት ሥርዓታቸውን ለማዘመን ከሚፈልጉ አገራት ጋር በቅድሚያ ስምምነት ያደርጋሉ።

የስምምነቱ ዓላማ አገራቱ እርዳታውን ለማግኘት ማሟላት የሚጠበቅባቸው ውጤት እንደመስፈርት የሚቀመጥበት ሲሆን፣ ይህ አሰራር ግን እንደታሰበው ሳይሆን በትምህርት ስርዓት ላይ መንግሥት የሚያስበውን ለውጥ ለማምጣት እንቅፋት ይሆናል ተብሏል።
ዓለም ባንክን የመሳሰሉ ዓለም ዐቀፍ ግዙፍ ተቋማት ጭምር የሚጠቀሙበት ይህ አሠራር፣ ለዓመታት አገልግሎት ሲሰጥ የነበረና ውጤታማነቱ በጥናት ያልተረጋገጠ ነበር።

የካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ጋር በመተባበር ባካሄደው ጥናት የእርዳታ አሰጣጡ ሒደት መፈተሸ እንዳለበት ተጠቅሷል። 75 የሚሆኑ ለጋሽ ድርጅቶችን እንዲሁም የተለያዩ የመንግሥት ባለሥልጣናትን በመጠየቅና የተለያዩ መንገዶችን በመጠቀም የእርዳታ አሰጣጡ ሂደት መፈተሹን ጥናቱን ያጠኑት ባለሙያዎች ተናግረዋል።

የጥናቱ ውጤት እንደሚያሳየው የተለመደው አሰራር ገና ከመንግሥት ጋር ውይይት ከሚጀመርበት ከመነሻው ጀምሮ እንከን አለበት።

ለጋሽ አገራትና ዓለም ዐቀፍ ተቋማት ይህንን ውጤትን እንደመስፈርት አድርጎ የሚያስቀምጥ የድጋፍ አሰጣጥ አሰራርን አማራጭ እንደሌለው መፍትሄ አድርገው መውሰድን ማቆም እንዳለባቸው ተነግሯል። እንዲህ ዓይነት አሰራር ኢትዮጵያን ለመሳሰሉ የትምህርት ስርዓታቸውን ለማሻሻል ለሚጥሩ አገራት በመጥቀም ፋንታ የባሰውን ሊጎዳ ይችላል ተብሏል።

ምንም እንኳን ጥናቱ የገንዘብ ድጋፍን ከውጤት ጋር የማገናኘት መርኅን በሰፊው የሚደግፍ ቢሆንም፣ የነበረው አሰራር በርካታ ገፅታዎች ከመጀመሪያው ጀምሮ ለዓላማ የማይበቁ መሆናቸውን አረጋግጧል። ጥናቱ እንደሚያሳው ከሆነ፤ ዕርዳታዎችን ቀድሞ ከመስጠት ይልቅ ተቀባይ መንግሥታት ከለጋሾች ጋር አስቀድመው የተስማሙትን የታለሙ ሁኔታዎች እንዲያሟሉ እንደሚጠይቅና ገንዘቡ የሚለቀቀው እነዚህ ሁኔታዎች ከተሟሉ በኋላ እንደሆነ ነው።

ይህም ተቋማቱን ከአሠራራቸው እንዲያፈነግጡ በር ከፍቷል የተባለ ሲሆን፤ በጥናቱ በኩል ሲመረመርም የተቀመጡት አብዛኛዎቹ ግቦች ከድጋፍ ጋር የተቆራኙና አገራት ከራሳቸው የትምህርት ማሻሻያዎች በታች እንዲወድቁ የሚያደርግ ሆኖ ተገኝቷል።
በገንዘብ ድጋፍና በውጤት አሰራር ላይ ያተኮረው የጥናት ውጤት እንደሚያመላክተው ከሆነ፤ የዓለም ባንክን ጨምሮ በዓለም ዐቀፍ ተቋማት እየተደገፈ ያለው የትምህርት ዕርዳታን ለማድረስ ውጤትን መሠረት ያደረገ የክፍያ አሰራር አንዳንድ አገራት ላይ የጥፋት አደጋ ጋርጦባቸዋል።

በዚህ ጥናት ውስጥ ሌሎች የታሰቡ ውጤቶች ካልተገኙ ተጠያቂው ማን እንደሚሆን እና መንግሥት በመጨረሻ ምን አይነት የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያገኝ ሙሉ በሙሉ ግልፅ አይደለም ሲል ጥናቱ አስቀምጧል። እስከዛሬ የሚሠራበት ውጤትን መሠረት ያደረገው አሠራር ሙሉ በሙሉ ውጤታማ አልነበረም ማለት እንደማይቻል የጠቆመው ጥናቱ፣ በአንዳንድ ጉዳዮች በተለይም አስቀድሞ በሚለዩ ግቦች አንፃር እንዲሁም ውጤታማነታቸው በሚለካበት መንገድ ላይ ክፍተት እንደሚኖር ያመላከተ ነው ብሏል።

በሌላ በኩል ችግሩ ለመጀመሪያ ጊዜ የተስተዋለ ክስተት እንዳልሆነም የተጠቆመ ሲሆን፤ ለአብነትም 2015 በኢትዮጵያ የፓይለት ፕሮግራም፤ በ2021 በሞዛምቢክ ኔፓል እና ታንዛኒያ የገንዘብ ድጋፍ ፕሮግራሞች ጨምሮ በሌሎች በርካታ ግምገማዎች ተመሳሳይ ችግሮች ጎልተው ታይተዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 178 መጋቢት 24 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here