የመኪና ባትሪዎችን መልሶ ጥቅም ላይ ለማዋል የሚሠራ ኩባንያ በኢትዮጵያ እየተገነባ ነው

0
712

መሠረቱን ኳታር ዶሀ አድርጎ በተለያዩ አገራት በተለያዩ የሥራ መስኮች ላይ ተሠማርቶ እንደሚገኝ የተነገረለት፣ ሱሄይል ግሩፕ (Suhail holding) የተሠኘ ኩባንያ፣ የአገልግሎት ጊዜያቸውን የጨረሱ ‹የሊድ አሲድ› የመኪና ባትሪዎችን መልሶ ጥቅም ላይ ለማዋል የሚችል አምራች ኢንዱስትሪ በኢትዮጵያ ሊከፍት መሆኑን ለአዲስ ማለዳ ገለጸ።

የኩባንያው ሥራ አስኪያጅ ቴዎድሮስ አበጋዝ፣ ኢንዱስትሪው አሁን ላይ በ21 ሚሊዮን 700 ሺሕ ዶላር ካፒታል እየተገነባ መሆኑን እና በሚቀጥለው ስድስት ወራት የግንባታ ሥራዎችን አጠናቆ ወደ ሥራ እንደሚገባ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በሰሜን ሸዋ ዞን ቱለፋ በተባለ ቦታ በ22 ሺሕ ካሬ ሜትር እየተገነባ ያለው ይህ ኢንዱስትሪ፣ ግንባታው ተጠናቆ ወደ ሥራ ሲገባ በቀን እስከ 120 ሺሕ ቶን የሊድ አሲድ ባትሪዎችን በመሰብሰብ፣ ፈጭቶና አቅልጦ ዕሴት ጨምሮ እንደሚያመርት ገልፀዋል።

ኢንዱስትሪው በአገሪቱ ያሉ ያገለገሉ ባትሪዎችን ለመጠቀም ነው ያቀደው ያሉት ሥራ አስኪያጁ፣ ሆኖም ያሉት ባትሪዎች ከአቅማችን በላይ ከሆኑ ግን ጎን ለጎን ሌላ ኢንዱስትሪ ለማቋቋም ዝግጁ ነን ብለዋል።

እስከሚቀጥለው ዓመት የመኪና ባትሪ ለማምረት ዕቅድ አለን፤ እስከዚያው ድረስ ግን ያገለገሉ ባትሪዎችን በመሰብሰብ አቅልጠን በማምረት ለውጭ ገበያ የምናቀርብ ይሆናል ሲሉ ተደምጠዋል። ምርቶች በዋናነት ወደ ቻይናና ኳታር እንደሚላኩም ተመላክቷል።

ዕቅዳችን በምናገኘው የውጭ ምንዛሬ በየዓመቱ ኹለትና ሦስት ፋብሪካዎች መጨመር ነው ያሉት ሥራ አስኪያጁ፣ ሆኖም ግን በቃል የሚነገረውና መሬት ላይ ያለው ይለያያል ብለዋል። አክለውም እስካሁንም ሌሎች ፕሮጀክቶችን እንዳንጀምር አስቸጋሪ ቢሮክራሲዎች ይዘውናል ነው ያሉት።

ፋብሪካው በቁጥር ከሚገለጸው በላይ ለበርካታ ወጣቶች የሥራ ዕድል እንደሚፈጠርም ተመላክቷል። በመላ አገሪቱ ባሉ አካባቢዎች ያሉ ያገለገሉ የሊድ አሲድ ባትሪዎችን ነው ወደ ፋብሪካው ማምጣት የምንፈልገው የሚሉት የኩባንያው ሥራ አስኪያጅ፣ ይህም በየከተሞች ላሉ ወጣቶች የሥራ እድል ይፈጥራል ሲሉ ዕምነታቸውን ገልጸዋል።

ወደፊትም ኩባንያው በተለያዩ ዕሴት የሚጨምሩ (Value added project) የማኑፋክቼሪንግ ዘርፎች ላይ ለመሠማራት ዝግጁ መሆኑን ነው ሥራ አስኪያጁ ጨምረው ያስገነዘቡት።

የኢፌዴሪ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን የሕዝብ ግንኙነትና የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር ተስፋዬ ጋሻው በበኩላቸው፣ ከዚህ በፊት ያገለገሉ ባትሪዎች ተሰብስበው ወደ ውጭ ገበያ የሚላኩበት ወይም መልሶ ጥቅም ላይ የሚውሉበት አሠራር አልነበረም። የፋብሪካው በኢትዮጵያ መከፈት ከሊድ አሲድ ባትሪዎች የሚወጣውን መርዛማ አሲድን መልሶ ጥቅም ላይ በመዋል በአካባቢና በማኅበረሰብ ላይ ሊደርስ የሚችል ጉዳትን በማስቀረት ረገድ ሠፊ ፋይዳ አለው ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

አክለውም፣ የውጪ ምንዛሬን ከማስገኘትና የቴክኖሎጂ ሽግግርን ከማምጣት ባለፈ፣ ከአካባቢ ጥበቃ አንጻር የሚታዩ ወደ ሥራ የገቡ የዚህ ዓይነት ፋብሪካዎች መኖራቸውን አመላክተው፣ ለአብነትም ያገለገሉ ማቀዝቀዣ ማሽኖችንና ኮምፒዩተሮችን መልሶ ጥቅም ላይ ለማዋል የሚሠራ በቅርቡ አዲስ አበባ ላይ ሥራ የጀመረ አንድ ኢንዱስትሪ መኖሩን ጠቅሰዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 178 መጋቢት 24 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here