ብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር የአጭር መልዕክት ሎተሪ ሊጀምር ነው

0
1459

ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር የነበረው የትርፍ ክፍፍል አለመግባባት ተፈትቷል

የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር የተያዘው በጀት ዓመት ሳይጠናቀቅ የአጭር መልዕክት ሎተሪ ሽያጭ አገልግሎት እንደሚጀምር ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።

የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር በ2013 በጀት ዓመት በአጭር መልዕክት (ኤስ.ኤም.ኤስ) የሎተሪ ሽያጭ ለማከናወን ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በኹለት ጉዳዮች ማለትም፣ በጽሑፍ መልዕክት እና ከገቢ ክፍፍል ጋር በተያያዘ መግባባት አለመድረሳቸውን ተከትሎ አገልግሎቱን ሳይጀምር እንደቆየ ገልጾ፣ አሁን ላይ ኹለቱ የመንግሥት ተቋማት መስማማት በመቻላቸው የተያዘው በጀት ዓመት ሳይጠናቀቀ አገልግሎቱን እንደሚጀምር የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው ቴዎድሮስ ንዋይ ለአዲስ ማለዳ ጠቁመዋል።

አስተዳደሩ አዲሱን የሎተሪ ሽያጭ ለማስጀመር ከኢትዮጵያ ኮምዩኒኬሽን ባለሥልጣን ባገኘው ፈቃድ መሠረት፣ የአጭር መልዕክት አገልግሎት አቅራቢ ከሆነው ኢትዮ ቴሌኮም ጋር በገቢ ክፍፍል ላይ ስምምነት ላይ መድረሱን ኃላፊው ለአዲስ ማለዳ ጠቁመዋል። በኢትዮ ቴሌኮምና በአስተዳደሩ መካከል የነበረው የ‹ሲስትም› አቅርቦትና የትርፍ ክፍፍል አለመግባባት መፈታቱን የጠቆሙት ኃላፊው፣ የገቢ ክፍፍል ስምምነቱ በኹለቱ ተቋማት እንደሚፈረም ተናግረዋል። ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር የተደረገው የገቢ ክፍፍል ስምምነት መጠን ምን ያህል እንደሆነ ግን ከመግለጽ ተቆጥበዋል።

አስተዳደሩ የአጭር መልዕክት ሎተሪ ሽያጭ አገልግሎት ለማስጀመር ሥራ የጀመረው ከ2011 በፊት ሲሆን፣ አስተዳደሩ ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በድርሻ ክፍፍል ምክንያት ሒደቱን ማስቀጠል አለመቻሉን አዲስ ማለዳ ከዚህ በፊት መዘገቧ የሚታወስ ነው። በወቅቱ ስምምነት ላይ ያልተደረሰው ከሚገኘው ገቢ 40 በመቶ የሚሆነውን ኢትዮ ቴሌኮም ይገባኛል የሚል ጥያቄ በማንሳቱ ነበር።

ይህ የአጭር መልዕክት ሎተሪ ሽያጭ አገልግሎት ሲጀምር ሰባት መደበኛ የሎተሪ ዓይነቶችን ማለትም እንቁጣጣሽ፣ ገና፣ ትንሣኤ፣ ልዩ ዕድል፣ ዝሆን እና ቶምቦላ ሎተሪ ሥራ ላይ የሚውሉ ሲሆን፣ የሚፋቁ ሎተሪዎችን ግን በአዲሱ የሎተሪ ሽያጭ እንደማይካተቱ እና የመደበኛ ወይም የወረቀት የሎተሪ ሥርጭትና አገልግሎትም እንደማይቋረጥ ኃላፊው ተናግረዋል።

አስተዳደሩ የሚጀመረው የአጭር መልዕክት የሎተሪ ሽያጭ አገልግሎት በወረቀት ታትሞ በሎተሪ አዟሪዎች ከሚሸጠው ጎን ለጎን የሚከናወን ሲሆን፣ ብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር እስከ 2022 በቴክኖሎጂ የተደገፈ የሎተሪ አገልግሎት በማቅረብ የሽያጭ አድማሱን ለማስፋት ዕቅድ እንዳለው ኃላፊው ጠቁመዋል። በዚህ መሠረትም በቴክኖሎጂ የተደገፉ የሎተሪ ሽያጭ አገልግሎቶችን በማቅረብ የገበያ ተደራሽነቱን እንደሚያስፋፋ ነው አያይዘው የገለጹት።

ኃላፊው አክለውም አስተዳደሩ ከላይ የተጠቀሰውን አገልግሎት ሲጀምር የሎተሪ አዟሪዎች ከዚህ ቀደም የሚያገኙት ጥቅም እንደተጠበቀ ሲሆን፣ እነርሱን በተመለከተ የተቀመጠ ተጨማሪ አቅጣጫ አለመኖሩንም ተናግረዋል። የአጭር መልዕክትና የ‹ኦንላይን› ሎተሪ ሽያጭ ከወረቀት ሎተሪ ሽያጭ ጎን ለጎን የሚካሄድ ሲሆን፣ በአሁን ወቅት ገበያ ላይ እየዋሉ ያሉ ሎተሪዎች ከህትመት ጀምሮ ከፍተኛ ድክመት ያለባቸው እና በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢ የሚገኙ ደንበኞች ዘንድ ተደራሽ እስከሚሆኑ መዘግየት የሚስተዋልባቸው ናቸው። በዚህ የተነሳም በተያዘው በጀት ዓመት የአጭር መልዕክት አገልግሎት ለመጀመር የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር መገደዱን ኃላፊው ገልጸዋል።

ይህ የአጭር መልዕክት ሎተሪ ሽያጭ ሲጀመር አገልግሎቱን ፈጣንና ቀልጣፋ ከማድረግ ባሻገር፣ ወጪ ቆጣቢ እና ደንበኞችን የሚያዝናና ዘመናዊ የሎተሪ መቁረጫ አገልግሎት ይሆናል ተብሏል። ብሔራዊ ሎተሪ የአጭር መልዕክት ሎተሪ ሽያጭ አገልግሎት ፈቃድ ያገኘው በመዝናኛ ዘርፍ መሆኑ ተመላክቷል።

አስተዳደሩ በ2014 በጀት ዓመት ስምንት ወራት ዘጠኝ የሎተሪ ዓይነቶችን ለገበያ በማቅረብና ከዕድል ጨዋታ ኮሚሽን ከ687 ሚሊዮን ብር በላይ ጠቅላላ ገቢ መሰብሰቡን አዲስ ማለዳ ባለፈው ሳምንት ዕትሟ መዘገቧ የሚታወስ ነው።


ቅጽ 4 ቁጥር 178 መጋቢት 24 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here