ቀይ መስቀል ተጠልለው የነበሩ የሕወሓት ታጣቂዎች ለዳግም ጦርነት እንዲሰለፉ እየተገደዱ ነው

0
451

ወደ ሱዳንና ካርቱም ሸሽተው የነበሩና ትጥቃቸውን ለሱዳን መከላከያ ሠራዊት አስረክበው ወደ ቀይ መስቀል የተጠጉ የቀድሞ የሕወሓት አባሎች፣ በሕወሓት ታጣቂዎች ተገደው ወደ ጦርነት እንዲሰለፉ እየተደረጉ መሆኑን በሁመራ ወረዳ የሚገኙ ታማኝ ምንጮች ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

አለው፣ ዲማ እና ልበዲ በተባሉት አካባቢዎች ከመጋቢት 12 ጀምሮ የተኩስ ድምጽ እንደሚሰማ የጠቆሙት የአዲስ ማለዳ ምንጮች፣ ሠሞኑን ከሱዳን የመጡና የሕወሓት አባላትን የሚያስተባብሩ ሰዎች እንዳሉ ጠቁመዋል።

እነዚህ ከሱዳን የተለያዩ አካባቢዎችና ከካርቱም የመጡ ታጣቂዎች፣ ከዚህ በፊት የሕወሓት አባል የነበሩና ወደ ሱዳን ሸሽተው ትጥቃቸውን ለሱዳን መከላከያ በመስጠት ወደ ቀይ መስቀል የተጠጉ ሰዎችን እንደገና አስገድደው ወደ ጦር ግንባር የማሰለፍ ሙከራ እያደረጉ መሆናቸውን ነው ምንጮቹ አያይዘው የገለጹት።

ሥማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የአዲስ ማለዳ ምንጭ፣ ከድንበር አካባቢ ሸሽተው ወደ ሱዳን ገብተው የነበሩና ትጥቃቸውን ለሱዳን መከላከያ ሠራዊት የሰጡ ከ200 በላይ ሰዎችን ቀይ መስቀል እየተቀበላቸው ነበር ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
አያይዘውም፣ የሕወሓት ታጣቂዎች ከዚህ በፊት በስደተኛ ሥም በሁመራና በሌሎች አካባቢዎች የሚኖሩ የሕወሓት አባል የነበሩ ከ10 ሺሕ በላይ ሰዎችን መልምለው አሰልጥነው ነበር ነው ያሉት።

የአዲስ ማለዳ ምንጭ እንደሚሉት ከእነዚህ ከሰለጠኑትና በጦር ግንባር ከነበሩት ታጣቂዎች መካከል፣ ከግንባር የሸሹ የሕወሓት ታጣቂዎች ትጥቃቸውን ለሱዳን መከላከያ ሠራዊት አስረክበው ነበር ወደ ቀይ መስቀል የተጠጉት ብለዋል።
እስካሁን ከስደተኛነት ተመልሰው በነጀነራል ፍስሀ ማንጁስ እና በነ ሰፊው ምትኩ፣ እንዲሁም በድሮው የሕወሓት የዞንና የወረዳ አመራሮች የሚመሩ ታጣቂዎች በሁመራ አካባቢ እንዳሉም እናውቃለን ሲሉ የአዲስ ማለዳ ምንጭ ተናግረዋል።

የሚያሰለጥኗቸውም ከሱዳን የመጡ ታጣቂዎች ናቸው ያሉት የአዲስ ማለዳ ምንጭ፣ ድርጊቱ ከዚህ በፊትም በተደጋጋሚ ሲደረግ ተስተውሏል ሲሉም አክለዋል።

አዲስ ማለዳ ጉዳዩን በማስመልከት ከቀይ መስቀል ተቋም ኃላፊዎች ጋር ቆይታ ያደረገች ሲሆን፣ ትጥቃቸውን ፈትተው በቀይ መስቀል ተጠግተዋል ስለተባሉት የሕወሓት አባሎችም የሚከተለውን ምላሽ ሰጥተዋል።
የቀይ መስቀል የሕዝብ ግንኙት ኃላፊ ሰለሞን አሊ፣ ታጣቂዎቹ ወደ ቀይ መስቀል ስለመጠጋታቸው የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ነው ለአዲስ ማለዳ የገለጹት።

በሌላ በኩል፣ ስድስት ነጥብ አራት ሚሊየን በላይ ዜጎች በድርቅ ምክንያት እንደተጎዱና መጠነ ሠፊ ዕርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ሰለሞን ለአዲስ ማለዳ የገለጹ ሲሆን፣ የፍላጎትና የዕርዳታ አቅርቦት መጠኑም የተራራቀ ነው ሲሉ አክለዋል።
የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው አክለውም፣ በችግር ላይ ያሉ ዜጎች ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸውና በቀይ መስቀል የተሰባሰበው ብር ግን ሊያዳርስ እንደማይችል አብራርተዋል።

አክለውም፣ ድርጅቱ ያሰባሰበው ብር 53 ሚሊዮን ብቻ ሲሆን፣ ለስድስት ነጥብ አራት ሚሊዮን ሰዎችም ዕርዳታ ማዳረስም አዳጋች እንደሆነ ነው የገለጹት። በመጨረሻም፣ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዕርዳታ እንዲያደርግላቸው እና በኢትዮ ቴሌኮም በተከፈተው 900 የብር ማሰባሰቢያ መስመር አንድ ብር በቀን እንዲለግሳቸው ጠይቀዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 178 መጋቢት 24 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here