በሐረሪ ክልል የሚገኘው የጀጎል ግንብ እና በዙሪያው ያሉ በቅርስነት የተመዘገቡ ቤቶች ላይ አደጋ እንደተጋረጠ የሐረሪ ክልል የባህል፣ ቅርስና ቱሪዝም ቢሮ ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።
በዓለም ዐቀፍ የሳይንስ የትምህርት እና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በዓለም ቅርስነት የተመዘገበው እና አምስት መቶ ዓመት ገደማ ዕድሜ ያስቆጠረው የጀጎል ግንብ እና በዙሪያው የሚገኙ ቤቶች፣ በክረምት ወራት እንዲሁም በየወቅቱ በሚጥል ዝናብ ሳቢያ ጉዳት እየደረሰባቸው ነው። እንዲሁም በአካባቢው የሚኖሩ ሰዎች በየወቅቱ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ በሚያደርሱት ጉዳት ምክንያት ቅርሶቹ አደጋ እንደተጋረጠባቸው የክልሉ የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ተወለዳ ሀዱሽ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
ቅርሶቹ በክልሉ በኩል በየዓመቱ ራሱን የቻለ በጀት ተመድቦ የጥገና ሥራ ቢደረግላቸውም፣ ከሚያጋጥማቸው ችግር መላቀቅ እንዳልቻሉ ተወለዳ ተናግረዋል። ኃላፊው አክለውም፣ ባለፈው ዓመት ቅርሱ ችግር ላይ እንደሚገኝ ለመጀመሪያ ጊዜ ለፌዴራል መንግሥት ማሳወቃቸውንና ድጋፍ እንዲደረግላቸው ጥያቄ ማቅረባቸውን አውስተዋል። በተያያዘም ቅርሱ ላይ ጥገና እንዲከናወን ለማስቻል ቅድሚያ የጥናት ሥራ ለማድረግ ከክልሉ ቤቶች ልማት ጋር በጥምረት የጥናት ሥራ ተጀምሮ የነበረ ቢሆንም፣ የጥናት ሥራው ሙሉ ለሙሉ ባለመጠናቀቁ እና በወቅቱ በአካባቢው በነበረው የፀጥታ ችግር ምክንያት ቅርሱ ጥገና ሳያገኝ ቀርቷል ብለዋል።
ክልሉ በቻለው አቅም የጥገና ሥራውን እያከናወነ መሆኑን የጠቀሱት ኃላፊው፣ ይሁንና ከደረሰበት አደጋ መከላከል ግን እንዳልተቻለ አስረድተዋል።
የሐረሪ ክልል የባህል፣ ቅርስና ቱሪዝም ቢሮ በተያዘው ዓመትም ለኹለተኛ ጊዜ ለፌዴራል መንግሥት ጥያቄ ማቅረቡን ተወለዳ አስታውሰዋል። ሆኖም ግን እስከአሁን ምላሽ እንዳልተገኘ እና እየተሰጠ ያለው ትኩረትም አናሳ መሆኑን ኃላፊው ጠቅሰው፣ ቅርሱን ለመታደግ የሚደረገው ርብርብ ግን አሁንም እንዳልቆመ አስታውቀዋል።
አዲስ ማለዳ ስለ ጉዳዩ የጠየቀቻቸው እና ሥማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉት በፌዴራል ቅርስና ጥበቃ ሚኒስቴር ውስጥ ያሉ ባለሙያ፣ በጀጎል ግንብና በዙሪያው የሚገኙ ቅርሶች ላይ አደጋ መጋረጡ እንደማይሸሸግ አንስተዋል። ባለፈው ዓመት ከዓለም ዐቀፍ የቅርስ ጥበቃ ኮሚቴ ጋር በመተባበር ለቅርሱ ጥገና የሚውል ራሱን የቻለ በጀት ተመድቦ የነበረ ቢሆንም፣ በክልሉ ተፈጥሮ በነበረው የፀጥታ ችግር ምክንያት ቅርሱን መጠገን አልተቻለም ብለዋል።
ከዚህ በተጨማሪ በ2013 የበጀት ዓመት ለቅርሱ ጥገና ተይዞ የነበረው በጀት ለሌላ ሥራ እንደዋለ እና በተያዘው 2014 በጀት ዓመት በመጀመሪያዎቹ ወራት ወደ ሥራ ይገባል ተብሎ የነበረ ቢሆንም፣ እስከ አሁን ባለው መረጃ ምንም ዓይነት የተጀመረ ሥራ እንደሌለ ገልጸዋል።
የፌዴራል ቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን አሁን ላይ ለቅርሱ ጥገና ለማድረግ ከዓለም ዐቀፍ የቅርስ ጥበቃ ኮሚቴ እና ከባለ ድርሻ አካላት ጋር እየተነጋገረ እንደሚገኝም ተጠቁሟል።
የሐረሪ ክልል የባህል፣ ቅርስና ቱሪዝም ቢሮ በከተማዋ ያለውን ቅርስ ለመታደግ ከሚያደርገው ጥረት ጎን ለጎን፣ በሐረር ከተማ ዙሪያ የሚገኝ ‹አወር ሄሌ› የሚል ሥያሜ የተሠጠውን የሚዳሰስ ቅርስ የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ እየሠራ መሆኑን ኃላፊው ተናግረዋል።
ቅጽ 4 ቁጥር 178 መጋቢት 24 2014



