ከሳዑዲ አረቢያ ለሚመጡ ስደተኞች የ561 ሚሊዮን ብር ዕርዳታ ያስፈልጋቸዋል ተባለ

0
832

ከሳዑዲ አረቢያ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ ስደተኞች 11 ሚሊዮን ብር የሚደርስ ዕርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው የዓለም ዐቀፍ የስደተኞች ድርጅት (IOM) ካወጣው መረጃ ማወቅ ተችሏል።

በኢትዮጵያና በሳዑዲ አረቢያ መንግሥት መካከል በተደረገው ስምምነት መሠረት፣ ከ100 ሺሕ በላይ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ወደ አገራቸው እንደሚመጡ ይጠበቃል። ለተመላሾቹ የዕርዳታ ድጋፍ ለማድረግ፣ የመንግሥት የዕርዳታ ድርጅቶች፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኤጀንሲዎች፣ እንዲሁም ሌሎች ሰብዓዊ ዕርዳታ አቅራቢዎች፣ ለጋስ አካላት ድጋፍ እንዲያደርጉላቸው ጥያቄ ማቅረባቸውም ተጠቁሟል።

ከዓለም ዐቀፍ የስደተኞች ድርጅት የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው፣ ከ100 ሺሕ በላይ የሚሆኑ ተመላሾች ሙሉ ለሙሉ ወደ ኢትዮጵያ ሲገቡ ከዓለም ዐቀፍ የስደተኞች ድርጅት እና ከሌሎች አጋር አካለት ዘንድ የሰብዓዊ ዕርዳታና የጥበቃ አገልግሎት እንደሚያገኙ ነው ማወቅ የተቻለው።

ወደ አገር የሚገቡ ስደተኞች ቁጥር በርካታ መሆኑን ተከትሎም ፍላጎታቸውን ለማሟላት ለመንግሥት፣ ለዓለም ዐቀፍ የስደተኞች ድርጅት፣ እንዲሁም ለሌሎች አጋር አካላት ትልቅ ፈተና ሊሆን እንደሚችልም ተመላክቷል።
ይህ ዘገባ እስከተዘጋጀበት ጊዜ ድረስ (ማለትም እስከ መጋቢት 22/2014) 900 የሚደርሱ በሳዑዲ አረቢያ ይኖሩ የነበሩ ስደተኞች አዲስ አበባ ቦሌ ዓለም ዐቀፍ የአውሮፕላን ማረፊያ መድረሳቸውን ከድርጅቱ በተገኘው መረጃ ማረጋገጥ ተችሏል።

ከስደት የሚመለሱት በቅድሚያ አዛውንቶች እና ሕፃናትን የያዙ እናቶች ናቸው የተባለ ሲሆን፣ የተመለሱት እናቶች እና ሕፃናት በዓለም ዐቀፍ ስደተኞች ድርጅት ሠራተኞች ዕርዳታ ተደርጎላቸው እንደተመዘገቡም ተጠቁሟል። በተያያዘም፣ ለስደተኞቹ የምግብ፣ የጊዜያዊ መጠለያ፣ የሕክምና ዕርዳታ እና የምክር አገልግሎት ድጋፍ እንደተደረገላቸው ተገልጿል።

በአሁኑ ወቅት ወደ 750 ሺሕ የሚሆኑ ኢትዮጵያዊያን በሳዑዲ አረቢያ መንግሥት ሥር የሚገኙ ሲሆን፣ እንዲሁም ወደ 450 ሺሕ የሚሆኑ ዜጎች መደበኛ ባልሆነ መንገድ ተጉዘው ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ ገና የተሟላ ዕርዳታን እንደሚሹ ይገመታል። መንግሥት በሺሕዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ወደ አገራቸው የመመለስና መልሶ የማቋቋም መርሃ ግብሮችን ለማጠናከርና ዜጎቹ ወደ አገራቸው የሚመለሱበትን ኹኔታ ለማረጋገጥ ጥረቱን እንደሚቀጥልም ተመላክቷል።

ይህንንም በማቀድና ተግባራዊ በማድርግ ረገድ የቁልፍ አካላት አጋርነትና ተሳትፎ እንደሚያሻ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ኃላፊዎች ማስረዳታቸውን ከድርጅቱ በተገኘው መግለጫ ማወቅ ተችሏል።

ባለፉው አራት ዓመት ውስጥ ወደ 350 ሺሕ የሚጠጉ ስደተኛ ኢትዮጵያዊያን ወደ አገራቸው የተመለሱ ሲሆን፣ ተመላሾቹም የተለያዩ ፍላጎቶችን፣ ሥጋቶችን እና ተጋላጭነትን የሚያሳዩ፣ እርጉዝ እና የሚያጠቡ ሴቶች፣ አረጋውያን እና የአእምሮ ጤና መታወክ እና ሌላ የጤና ዕክል ያለባቸው ናቸው።

በሌላ በኩል፣ በሺሕዎች የሚቆጠሩ ከሳዑዲ አረቢያ የሚመለሱ ስደተኞችን በመቀበል ሒደት የዓለም ዐቀፍ የስደተኞች ድርጅት ከኢትዮጵያ መንግሥት እና አጋሮቹ ጋር በቅርበት እየሠራ ነው ተብሏል።

ከስደት ተመላሾች ሕክምና፣ ምግብ፣ መጠለያ፣ ሥነ-ልቦናዊ ድጋፍና ልዩ የጥበቃ አገልግሎት እንዲያገኙ፣ ብሎም አስቸኳይ ፍላጎቶቻቸው፣ ሥጋቶቻቸው እና ተጋላጭነታቸውን ተቃሎ ወደ ቤታቸው በደኅንነት እና በክብር እንዲመለሱ ለማድረግ የተቀናጀ ዘርፈ ብዙ ምላሽ እንደሚያሻም ተመላክቷል።


ቅጽ 4 ቁጥር 178 መጋቢት 24 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here