ተወርቶ የሚረሳው የነዳጅ ችግር

0
1113

በኢትዮጵያ የነዳጅ ዕጥረት በየወቅቱ የሚከሠትና ዘላቂ መፍትሔ ያልተገኘለት ችግር እየሆነ መምጣቱ የአደባባይ ወሬ ሆኗል። ነዳጅን በተመለከተ በተለይም ከጉዳዩ ጋር ቅርብ ትስስርና ኃላፊነት ያላቸው ኢትዮጵያዊያን በተደጋጋሚ ውይይት ሲያደርጉ ማየት ተለምዷል። የችግሩ ቀማሾች በተለያዩ ጊዜያት ቅሬታቸውን ያስተላልፋሉ፤ የዘርፉ ምሁራን ሠፋ ያለ ትንታኔን ይሰጣሉ። ከዚህም ባለፈ መንግሥት በበኩሉ ለሚሠነዘረው አስተያየት ነዳጁ ከውጭ የሚገባበትን የዋጋ ንረት እንደዋነኛ ምክንያት አደርጎ መጥቀሱን ተያይዞታል።

በየወቅቱ ቅሬታ የሚነሳበት የነዳጅ ዕጥረት፣ በአንድ ወቅት በዋጋው ላይ ጭማሪ ሲታይ ወይም ምርቱ ሲጠፋ ሰፋ ያለ ውይይት የሚካሔድበት መሆኑ ባይካድም፣ ዕጥረቱን ለመቅረፍ ከወሬ የዘለለ ተግባር ባለመከናወኑ ችግሩ ሊቀረፍ እንዳልተቻለ ብዙዎች ለተለያዩ የሚዲያ ተቋማት ከሚሠጡት አስተያየት መረዳት ይቻላል።

በጉዳዩ ላይ መፍትሔ ማምጣት የተቸገረ የሚመስለው መንግሥትም በበኩሉ መመሪያ አውጥቶ በየወሩ የነዳጅ የችርቻሮ መሸጫ ዋጋን ሲተምን ይስተዋላል። ለዚህም የሚኒስትሮች ምክር ቤት በመስከረም 23/2001 ባካሔደው ስብሰባ የነዳጅ ምርት ዋጋ በየወሩ እንዲከለስ መመሪያ መስጠቱ የሚታወስ ነው።

በመመሪያው መሠረት የነዳጅ የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ ክለሳውም ዘንድሮ ከጥር 26 እስከ የካቲት 30/2014 ተግባራዊ እንዲሆን የተወሰነ ሲሆን፣ ይህን ማድረግ አስፈላጊ የሆነበት ምክንያትም “ነባራዊ የዓለም የነዳጅ ምርቶች የመሸጫ ዋጋ በየወሩ በመጨመር ላይ በመገኘቱ” መሆኑን የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ጥር 26/2014 በሰጠው መግለጫ አመላክቷል።

በመግለጫው፣ ከዚህም በተጨማሪ “አንዳንድ ኩባንያዎችና የነዳጅ ማደያዎች ዕጥረት ለመፍጠር እያደረጉት ካለው ሕገ ወጥ እንቅስቃሴ እንዲታቀቡ እያሳሰብን፣ ይህን በሚፈጽሙ ላይ የማያዳግም ሕጋዊ ዕርምጃ እንደሚወሰድ” ማሳሰቢያ መሰጠቱ የሚታወስ ነው።
የሆነው ሆነና ብዙዎቹ ከሚዘነዝሩት አስተያየት መረዳት የተቻለው፣ የነዳጅ ዋጋ በየወሩ ተመን እንዲወጣለት ቢደረግም ከዚህ የተሻለ የመፍትሔ መንገድ አለመገኘቱና በየወሩ የዋጋ ተመን ማስቀመጡ ደግሞ ሸማቾችን ከሚገጥማቸው ችግር ሊገላግላቸው እንዳልቻለ ነው።

ይህን በተመለከተ አስተያታቸውን ለአዲስ ማለዳ የሰጡ መሐመድ አያሌው የተባሉ አንድ የአይሱዙ ሹፌር ናፍጣ ለማስሞላት አንድ ቀን አዳር መሰለፋቸውን ገልጸው፣ የነዳጅን ዋጋ በየወቅቱ መተመኑም ቢሆን ከወጪ እንዳልገላገላቸው ነው ያብራሩት። አስተያየት ሠጭው እንደሚሉት በየወሩ የነዳጅ ዋጋ መተመኑ እንደ መፍትሔ መቆጠሩ ቀርቶ፣ ሥር ነቀል ለውጥ ሊያመጣ የሚችል መፍትሔ ማስቀመጥ እንደሚያስፈልግ ነው።

ማደያ ውስጥ የሚሠሩ ሰዎች ከነጋዴዎች ጋር ተመሳጥረው በውድ ለመሸጥ ነዳጁን ለነጋዴዎች አሳልፈው ስለሚሰጧቸው ነው እንጂ ችግሩ የነዳጅ ዕጥረት ብቻ አይደለም የሚሉት መሐመድ፣ አንድ ሊትር ናፍጣ ከማደያ 28 ብር ከ31 ሳንቲም ማስሞላት ሲችሉ ከቸርቻሪዎች 40 ብር እንደሚገዙና ይህም ከዕቅድ ውጭ ለሆነ ወጪ እየዳረጋቸው እንደሆነ ነው የተናገሩት።

“መንግሥት ኹል ጊዜ የነዳጅ ዕጥረት አለ” ከማለት ወጥቶ ማደያ ውስጥ የሚሠሩ ሰዎችና ቸርቻሪዎች ለግላቸው ጥቅም ሲሉ የሚሠሩትን አሻጥር በጥልቀት ካልተከታተለና ዕርምጃ ካልወሰደ ችግሩ ይቀረፋል ማለት እንደሚያዳግት ነው መሐመድ ለአዲስ ማለዳ የገለጹት።
ችግሩን በተደጋጋሚ ማውራት ብቻ መፍትሔ ይሆናል?

በዘርፉ የሚስተዋለው ችግር በዋናነት ነዳጁን በአገር ውስጥ ለመሸጥም ሆነ ከውጭ አገራት ለማስገባት በየወቅቱ የሚታየው የዋጋ ንረት ነው። አሁን አሁን የዋጋ ጭማሬው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየናረ ከመምጣቱም ባሻገር፣ ይባስ ብሎ ነዳጅ በማደያዎች ውስጥ ማግኘት የማይቻልበት ደረጃ ላይ መደረሱ በበርካቶች እየተነሳ ነው። በተለይም በነዳጅ አማካይነት የዕለት ተዕለት ተግባራቸውን የሚያከናውኑ በርካታ ሰዎች በተደጋጋሚ አስተያየት ሲሠጡ ይስተዋላል።

የነዳጅ ዕጥረትና የዋጋ ጭማሪ ኢትዮጵያውያንን ለምሬት ከዳረጋቸው ዓመታትን ቢያስቆጥርም፣ በተለይም 2014 ጥር ወር መገባደጃና የካቲት ወር መግቢያ አንስቶ፣ በአገር ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ የነዳጅ ማደያዎች አቅርቦቱን በበቂ ኹኔታ ማግኘት እንዳልተቻለ ነው አዲስ ማለዳ ያረጋገጠችው።

ሠሞኑን የነዳጅ ዕጥረት ከተስተዋለባቸው ከተሞች መካከል በርካታ ተሸርካሪዎች የሚንሸራሸሩባት የአዲስ አበባ ከተማ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ናት። በመዲናዋ ውስጥ ነዳጅ የሚፈልጉ ሥራዎችን በመሥራት የሚተዳደሩ የማኅበረሰብ ክፍሎች የነዳጅ ዕጥረ ችግር እንደሆነባቸው በተለያዩ የሚዲያ ተቋማት ቅሬታ ሲያቀርቡ ሠንብተዋል።

በተለይም በነዳጅ ተጠቃሚነታቸው ከፍተኛውን ቦታ የሚይዙት የአገልግሎት ሰጪ ተሸከርካሪ ሹፌሮች በችግሩ መማረራቸው የሠሞኑ መነጋገሪያ ርዕሰ ጉዳይ ሆኗል። አዲስ ማለዳም ችግሩን ለማረጋገጥ በመዲናዋ ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ ማደያዎችን ተዘዋውራ የተመለከተች ሲሆን፣ በርካታ ተሸከርካሪዎች ቤንዚን ለማስሞላት ረጃጅም የሰልፍ ወረፋ ይዘው ለማየት ችላለች።

አዲስ ማለዳ ሹፌሮቹን ስለጉዳዩ የጠየቀች ሲሆን፣ ሹፌሮቹም የነዳጅ ዕጥረት በማይኖርበት ወቅት የሚፈልጉትን የነዳጅ ዓይነት ለማስሞላት ደቂቃዎች ብቻ ይወስድባቸው እንደነበር አስታውሰው፣ ሠሞኑን ግን ነዳጅ ለማግኘት ከአንድ ቀን በላይ እንደተሰለፉ ነው የገለጹት።
አዲስ ማለዳ የተከሠተውን ችግር መነሻ በማድረግ ያነጋገረቻቸው እና መዲናዋ ላይ በባጃጅ ሥራ የሚተዳደሩት ሳምሶን አንተነህ፣ ቤንዚን ለማስሞላት አንድ ቀን ሙሉ እንደተሰለፉና ይህም ሥራቸውን እንደተስተጓጎለባቸው ነው ያነሱት።
“ቤተሰብ የማስተዳድረው ሰዎችን በባጅጅ አመላልሼ እየለቃቀምኩ በምውለው ብር ነው” የሚሉት ሳምሶን፣ ችግሩ በዚህ ኹኔታ ከቀጠለ በርካታ ሰዎች የዕለት ተዕለት ኑሯቸውን ለመኖር እንደሚቸገሩ ነው የገለጹት።

የነዳጅ አመላላሽ ትራንስፖርት ባለንብረቶች ማኅበር በበኩሉ፣ በተደጋጋሚ መንግሥት ቸልተኛ በመሆኑ የነዳጅ አመላላሽ ቦቴዎች ቁጥር ከሦስት ሺሕ 500 በ20 እጅ እንደቀነሰ፣ መለዋወጫ በመወደዱ እና የብር ዋጋ በመውረዱ ምክንያት ጅቡቲ ደርሶ መልስ በሚሠሩበት ወቅት እየከሠሩ መሆናቸውን በአዲስ አበባ ዋቢ ሸበሌ ሆቴል ባደረጉት ስብሰባ የገለጹት።

የነዳጅ ትራንስፖርት ባለንብረቶችም በ10 ቀናት ውስጥ መንግሥት መፍትሔ ካልሰጠ ሥራ እንደሚያቆሙ ከወዲሁ ማስገንዘባቸው ተመላክቷል።

ነዳጅ በየወቅቱ ዕጥረት ከሚስተዋልባቸውና ዋጋቸው እየጨመረ ሔዶ ማኅበረሰቡን ካማረሩ ምርቶች ተርታ የሚሰለፍ ነው። ታዲያ ምርቱ በየጊዜው ለምን ይወደዳል? ችግሩን ከሥሩ የሚያደርቅ መፍትሔ ያልተገኘውስ ለምንድን ነው? የሚሉ ጥያቄዎች በተጠቃሚዎቹ በኩል በተደጋጋሚ ይነሳሉ።

ለመወደዱ ምክንያት የሚሆን የነዳጅ አቅርቦት ችግር እንደሌለም ኃላፊዎቹ ይናገራሉ። ከውጭ በሚመጣ ነዳጅ አቅርቦት ዕጥረት ምክንያት የጠፋበትን ጊዜ አላስታውስም የሚሉት የነዳጅ አቅራቢ ድርጅት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አለማየሁ ፀጋዬ ናቸው።
ነዳጅ እየቀረበ ነው ሲሉ ለአዲስ ማለዳ የገለጹት የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያው፣ ለዚህ ምስክር የሚሆነው ደግሞ በነዳጅ ዕጥረት ምክንያት የቆመ ተሸከርካሪ አለመኖሩ ነው ብለዋል።

የነዳጅ አቅርቦት ላይ ምንም ችግር የለም የሚሉት አለማየሁ፣ የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴርም እንደገለጸው የኢትዮጵያ ነዳጅ የሚሸጥበት ዋጋ ከቀጠናው በጣም ዝቅተኛ ስለሆነ ወደ ውጭ የሚወጣበት ዕድል አለ ሲሉ ገልጸዋል። እንደ ባለሙያው ንግግር ከሆነ፣ ይህ ድርጊት በማደያ ውስጥ የነዳጅ ዕጥረት ያለ እንደሚያስመስል ነው ያስረዱት።

በሌላ በኩል፣ ከዋጋ ጋር በተያያዘ ማደያዎች የሚፈጥሩት ሰው ሰራሽ ችግር ተጠቃሚውን በነዳጅ ምክንያት እንዲማረር ያደረገ መሆኑም ተጠቁሟል።
በማደያዎች ላይ የሚስተዋለው ችግርም ነዳጁን በመስለብ ለቸርቻሪና በድንበር አካባቢ ላሉ አካላት አሳልፎ መሸጥ መሆኑ ነው የተመላከተው።

ባለፉት ስደስት ወራት በ91 ቢሊዮን 677 ሚሊዮን 900 ሺሕ 100 ብር አንድ ሚሊዮን 941 ሺሕ 765 ሜትሪክ ቶን ነዳጅ ወደ አገር ውስጥ መግባቱን ሚናገሩት ኃላፊው፣ ይህ ደግሞ ኢትዮጵያ ከሚያስፈልጋት የነዳጅ ፍጆታ ስለማያንስ የነዳጅ አቅርቦት ችግር የለም ሲሉ አብራርተዋል።

የነዳጅ አቅርቦት ከሌሎች አቅርቦቶች በተሻለ መልኩ እንደሆነ በመረጃ ተደግፎ የተመላከተ ሲሆን፣ በተለይም ከወቅታዊ ኹኔታዎች ጋር በተያያዘ ሠላም ባልሰፈነባቸው ቦታዎች ነዳጅ ስለማይጓጓዝ እንኳን ዕጥረት ሊፈጠር ከእስከዛሬው በተሻለ መልኩ መትረፍረፍም ነበረበት ነው የተባለው።

አለማየሁ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት ከሆነ፣ መንገዱ ችግር ስላለበት ወደ ትግራይ ክልል፣ በከፊል ወደ አማራ ክልል፣ በኦሮሚያ ክልል በወለጋ፣ እንዲሁም ወደ ቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ነዳጅ እየተጫነ ስላልሆነ የኹሉንም ክልሎች ፍላጎት ይሸፍናል ተብሎ የመጣው 95 በመቶ ነዳጅ ወዴት ሔዶ ነው ዕጥረት የሚከሠተው ሲሉ ጠይቀዋል።

መፍትሔው
ለነዳጅ ዋጋ መጨመርና በተለያዩ ቦታዎች ነዳጅ የሚያስሞሉ አሽከርካሪዎችና ነዳጅን ለሌሎች አገልግሎቶች የሚያውሉ ኢንዱስትሪዎች ከማደያዎች በረጅም ሰልፍ ተሰድረው የሚታዩት የነዳጅ አቅርቦት ዕጥረት በመከሠቱ እንዳልሆነ ይነገራል።
እንደ ብዙኀኑ ገለጻ ከሆነ በነዳጅ በኩል ለሚስተዋለው ችግር ዋነኛ ምክንያቱ ነዳጅ ወደ ጎረቤት አገር በውድ ዋጋ በኮንትሮባንድ የሚሸጥበት አጋጣሚ ስላለ ነው።

የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ለችግሩ ዋነኛ ምክያንያት ነጋዴዎች ነዳጅን ወደ ጎረቤት አገራት ስለሚሸጡ መሆኑን በተደጋጋሚ ሲገልጥ ተስተውሏል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በበኩላቸው ይህንኑ ሐሳብ በፓርላማ ንግግራቸው ወቅት እንደምክንያት አንስተውታል።
የነዳጅ አቅራቢ ድርጅት የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያው አለማየሁ በበኩላቸው ለችግሩ መፈጠር መንስዔው ነዳጁ ወደ ጎረቤት አገር ስለሚሸጥ ነው ያሉ ሲሆን፤ ሆኖም ግን ይህ ጥልቅ ምርምርና ክትትልን ይሻል ሲሉ አስተያታቸውን ሠጥተዋል።

ይህን ተከትሎም የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር የነዳጅን ዋጋን በዘላቂነት ለመጨመር እንዳሰበ አሳውቋል። የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ገለጻ እንደሚያመላክተው ከሆነ፣ በአገር ውስጥ ያለው የነዳጅ መሸጫ ዋጋ በውጭ አገር ካለው ጋር ሲነጻጸር አነስተኛ በመሆኑ፣ ነጋዴዎች በኮንትሮባንድ ነዳጅን ወደ ጎረቤት አገራት ወስደው እንዲሸጡ በር ከፋቷል። ስለሆነም ዋጋው ከኹሉም አገራት ጋር ተመጣጣኝ መደረግ አለበት ተብሏል።


ቅጽ 4 ቁጥር 179 ሚያዝያ 1 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here