የአዲስ አበባና ኦሮሚያ ተጎራባች ወጣቶች ልዩነታቸውን ያጠበቡበት መድረክ

0
1793

የሠላምና ልማት ማዕከል ለትርፍ ያልተቋቋም፣ መንግሥታዊ ያልሆነ አገር በቀል ድርጅት ሲሆን፣ ከማንኛውም የፖለቲካም ሆነ የሌላ ወገንተኝነት የጸዳ፣ በአገሪቱ የሠላም ባህል እንዲስፋፋ፣ በውይይት እና በንግግር የሚያምን ማሕበረሰብን ለመፍጠር የሚሰራ ተቋም ነው።
ተቋሙ ከተመሰረተበት 1982 ዓ/ም አነስቶ በተለያዩ የሠላም ግንባታ ሥራዎች ላይ ተሰማርቶ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል። በተለይም ደግሞ ግጭትን ለመፍታት እና የሠላም ባህልን ለመገንባት የሚያስችሉ አገር በቀል እውቀቶችን በማዳበር በተለያዩ አካባቢዎች የሚከሰቱ አለመግባባቶች በውይይት እንዲፈቱ ሲያደርግ ቆይቷል። በተለይም ደግሞ በቦታ እና በሁኔታ አለመመቸት ምክንያት ለብዙ ተቋማት ለመድረስ አመቺ አይደሉም የሚባሉ የአገራችን አካባቢዎች ጭምር ሳይቀር በመግባት ከታችኛው የማሕበረሰብ አደረጃጀቶች ጋር ሰፊ የሠላም ግንባታ ሥራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል። ተቋሙም በተሰማራበት የሥራ ዘርፍ ምንም እንኳ እንደአገር ያለብን ችግር ዘርፈ ብዙ እና ሰፊ ቢሆንም የአቅሙን በማበርከት ላይ ከመሆኑም በላይ አመርቂ የሚባሉ ውጤቶችን በማስመዝገብ ላይ ይገኛል። ተቋሙም አሁን ያሉ ፕሮጅክቶችን በማስፋት እና ወደተጨማሪ ቦታዎች በመንቀሳቀስ፣ እንዲሁም የተለያዩ ማሕረሰብ አቀፍ የሆኑ የሰላም ጥረቶችን በመደገፍ እንዲሁም አቅማቸውን ጭምር በመገንባት ለችግሮች ተመጣጣኝ የሆነ ምላሽ ለመስጠት የበኩሉን አስተዋፅኦ በማበርከት የሚቀጥል ይሆናል።
ሠላምና ልማት ማዕከል

ኢትዮጵያ ውስጥ ጎራ ለይቶ የሚካሔድ ግጭትና አለመግባባት በየቦታው እንደሚከሠት በየጊዜው የምንሠማቸው ዜናዎች አመላካች ናቸው። ማንነትንም ሆነ የተለያዩ ምክንያቶችን መሠረት አድርገው ከሚጋጩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ውስጥ ትልቁን ድርሻ የሚወስዱት ወጣቶች ናቸው።

ወጣቱ የሕብረተሰብ ክፍል ለልማትም ሆነ ለጥፋት ግንባር ቀደም ተሰላፊ መሆኑ ይታወቃል። በመላው ዓለም አለመግባባቶች ወደግጭት እንዳያመሩ ወይም ያመሩት በዕርቅ እንዲያልቁ ትልቁን ድርሻ የሚወስዱት ደግሞ ሽማግሌዎች መሆናቸው ይነገራል። ይህ የራሱ በጎ ጎን እንዳለው ቢታመንም፣ በአገራችን ጭምር የአለመግባባቶች አስኳል የሚሆኑት ወጣቶች ያልተካተቱበት የዕርቅ መንገድ ያን ያህል ውጤታማ እንደማይሆን ይገመታል።

ወጣቱ የተገለለበት የሠላምና የልማት መንገድ የታሰበውን ያህል ውጤታማ እንደማይሆንና እንደማያዛልቅ አምኖ ለዓመታት በአገራችን ሲሠራ የቆየው የሠላምና ልማት ማዕከል፣ የተለያዩ አካባቢ ያሉ ግጭቶችን ለማብረድም ሆነ አለመግባባቶችን ለማስወገድና ሕብረተሰቡን ለማቀራረብ በርካታ እንቅስቃሴዎችን ሲያደርግ ቆይቷል። የዚህ ተግባሩ አካል በሆነ እንቅስቃሴም፣ የአዲስ አበባና የአጎራባች ኦሮሚያ ክልል ወጣቶች መካከል ያለ አለመግባባት ተቀርፎ ወደሠላማዊ ኑሮ ወጣቱ እንዲመለስ እየሠራ ይገኛል።

ማዕከሉ ወጣቶችን ትኩረት አድርጎ ከሚሠራባቸው የተለያዩ አካባቢዎች መካከል ለዛሬ የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማና የተጎራባቾቹን የኦሮሚያ ክልል ወጣቶችን አለመግባባት ለመፍታት የሔደበትን መንገድ እናቀርብላችኋለን። ኮዬ እየተባለ በኮንደሚኒየም ውዝግብ በሚታወቀው የኹለቱ አስተዳደራዊ ወሰንተኞች በሚገናኙበት አካባቢ ከሚኖሩ ወጣቶች በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የሚኖሩ ወጣቶችን አነጋግረን ስለውይይት መድረኩ ያላቸውን ምልከታ አጋርተውናል።

በ23 ዓመቷ የመምህርነት ሙያን ዘንድሮ የተቀላቀለች በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ላለፉት የተወሰኑ አመታት የምትኖር ወጣት፣ የሠላምና ልማት ማዕከል የኹለቱን አካባቢ ወጣቶች ለማቀራረብ እንቅስቃሴ ከመጀመሩ በፊት የነበረውን አለመግባባት ታስታውሳለች። በአካባቢው ብሔርና ቋንቋን መሠረት ያደረጉ አለመግባባቶች እስከቅርብ ጊዜ ድረስ ይከሠቱ እንደነበር የምታስታውሰው ይህች ወጣት፣ በግጭቶቹ ሳቢያ አካል ሲጎል፣ ንብረት ሲወድም እንዲሁም የማኅበረሰቡ ሕይወት ሲስተጓጎልና በኢኮኖሚ ጫና ጭምር ተጎራባቾቹ እኩል ሲጎዱም አስተውላለች።

ኮዬ እየተባለ በሚታወቀው ኮንደሚኒየም አካባቢዎች ችግሩ ገዝፎ ይታይ እንደነበር የምታስታውስ ሲሆን፣ በማይረቡ ትንንሽ ጉዳዮች የተነሱ አለመግባባቶች ወደ ትልልቅ ግጭቶች ሲያመሩም ተመልክታለች። ወጣት እንደመሆኗ ልዩነቶቹን ለማጥበብም ሆነ አለመግባባቶቹን ለመፍታት አቅም ሳይኖራት መዝለቋን የምታስታውሰው ይህች ወጣት፣ እንደተማሪነቷ የችግሩን ግዝፈት ባለመረዳቷ የሚፈጠረውን ጉዳት ብቻ ትመለከት ነበር። በዚህ አለመጋባባት ሳቢያ ሰፈርም ሆነ ትምህርት ቤት ለመቀየር የተገደዱንም እንደምታወቅ ጭምር ዕማኝነቷን ትሠጣለች።

ለአለመግባባቱም ሆነ ግጭቱ ዋና መንስዔ የምታደርገው ወጣቱ በአስተሳሰብ እንዲለያይ መደረጉን ሲሆን፣ በተለይ ከትምህርት ቤት ጀምሮ ሕብረተሰቡ መለያየቱና በጎራ መከፈሉ ለችግሩ ሁሉ መንስዔ እንደሆነ ታምናለች። ወጣቶቹ ከልጅነታቸው ጀምሮ በአስተዳደጋቸው እንዲከፋፈሉ ባይደረግ ይህ ኹሉ አይደርስም ነበር የምትለው መምህር፣ አሁንም ስላልረፈደ ግንዛቤ በመስጠት አመለካከትን መቀየር ይቻላል ትላለች።

የሠላምና ልማት ማዕከል መርሃ ግብር እንዳለ በሠማች ጊዜ ይህን ያህል ውጤታማ ይሆናል ብላ እንዳልገመተች የምትናገረው ይህች የአቃቂ ነዋሪ፣ በውይይቱ ለመሳተፍ ከተመለመሉ መካከል ሆና ሒደቱን መከታተል ስትጀምር ግን ከጠበቀችው በላይ ውጤታማ መሆኑን እንደተመለከተች ትናገራለች። በተለይ ትልልቅ ግጭቶችን ያስከተሉ ጉዳዮች ላይ የተሳተፉ ወጣቶች ተቀራርበው ችግራቸውን በውይይት ይፈታሉ የሚል ግምት ያልነበራት ይህች ወጣት፣ የማዕከሉን የማቀራረቢያና የማወያያ መንገድ ከተመለከተች በኋላ የታየው ውጤት እንዳስገረማት አልደበቀችም።

እሷን ጨምሮ የተወሰኑ ወጣቶች ተመርጠው የአወያይነት ሥልጠና ከኹለቱም ወገን አስቀድመው እንዲወስዱ ተደርጎ የነበረ በመሆኑ፣ ሒደቱን ራሳቸው ወጣቶች እየመሩት መካሔዱን ተናግራለች። የማዕከሉ ኃላፊዎች መድረኩን ከማሰተባበርና ከመንግሥተ አካላት ጋር በመሆን ከማስተባበር ውጭ በጉዳዩ ጣልቃ ሳይገቡ ችግሩን ለመፍታት መሥራቱን ታስረዳለች። የመጀመሪያ ዙር ሠልጣኞች የየአካባቢዎቻቸውን ወጣቶች ለይተው የሚያነሱት ቅሬታም ሆነ ሐሳቦች ላይ እንዲወያዩ ከተደረገ በኋላ ለጋራ መድረኩ ነጥቦች ተመርጠው ነበር። በተመረጡት ጭብጦች ላይ 30 የሚሆኑ ከኹለቱም አካባቢዎች ተወክለው ለመጡ ወጣቶች ማብራሪያ ከተሰጠ በኋላ፣ በውይይት አንዳችን በሌላኛችን ጫማ ውስጥ ሆነን እንድናስብና እርስበርሳችን እንድንተሳሰብ የተደረገበት መድረክ ነበር ትላለች።

መድረኩ አንዱ ስለሌላው የነበረው አመለካከት እንዲቀየርና የነበረ አለመግባባት ቀርቶ ወጣቱ እንዲቀራረብ አድርጓል የምትለው ይህች ወጣት፣ አለመግባባት ወደውድመት ሳይቀየር የሰውም ሕይወት ሳይጠፋ ችግር እንዲፈታ የሚያደርገው የማዕከሉ ጅማሬ ጥሩ ቢሆንም፣ ገና በሠፊው መሠራት አለበት ትላለች። እሷም ሆነች አብረዋት ውይይቱን የተካፈሉት፣ ቢያንስ ለ30 ሰው ያገኙትን ክህሎት በማስተላለፍ እንደእነሱ ሌሎች ወጣቶችም የአመለካከት ለውጥ እንዲያደርጉ እንደሚጥሩ ተናግራለች። መምህር እንደመሆኗም፣ ይበልጥ መሠራት ያለበት ከሕፃናት ጀምሮ ነው ብላ የምታምን ሲሆን፣ ይህን ለማድረግ መምህራንን ጨምሮ ወላጆችና ማኅበረሰቡ ትልቅ ኃላፊነት አለበት ትላለች።

ሌላው የውይይት መድረኩ አስተባባሪ ሆኖ የተሳተፈው የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወጣት ሶፎንያስ ወጣ ነው። ገላን ኮንደሚኒየም የሚኖረው ይህ የ26 ዓመት ሥራ ፈላጊ ስለአካባቢው ወጣቶች አለመግባባት ሲያስታውስ፣ ያን ያህል ከባድ ግጭት የሚባል እንዳልነበር ያነሳል። አልፎ አልፎ በትንንሽ ጉዳዮች የሚነሱ ብዙ ዓይነት ግጭቶች መኖራቸውን የሚያምን ሲሆን፣ ቅን ሕሊና ያለው አስተዋይ ወጣት ግጭቶች ውስጥ ስላልነበረ ትንሿ ነገር ልታጋጭ ትችል ነበር ብሏል።

የሠላምና ልማት ማዕከል ውይይትን ከተካፈለ በኋላ በወጣቶች መካከል ያለው ትልቅ የአመለካከትና የአስተሳሰብ ችግር መሆኑን ለመገንዘብ ችሏል። ከተሳታፊዎቹ ሐሳብና ምልከታ የተረዳው ቢኖር ወጣቶች እንደመሆናቸው የመልካም ሰብዕና ችግር እንደነበረባቸው ነው። ችግሩ ከራስ ይጀምራል የሚለው ሶፎንያስ፣ ከቤተሰብ ጀምሮ ሰብዕናን በራስም ሆነ በማኅበረሰቡ በበጎው ማነጽ አለመቻሉ ላለንበት ችግር ዳርጎናል ይላል። ትምህርት ቤትም ሆነ ሕብረተሰቡ ትልቅ ሚና መጣወት እንደሚችል የሚያምን ሲሆን፣ ከሕፃናት ቢጀመር ትልቅ ለውጥ በቀላሉ ማምጣት ይቻላል ሲል ሐሳቡን ያስቀምጣል።

ወጣት እንደእሳት ስለሆነ ምግብ ሊያበስልም ሆነ ቤት ሊያቃጥል ስለሚችል፣ እኛ ነን አጠቃቀሙን አስተካክለን ምግብ የሚያበስሉ በርካታ ወጣቶችን ማፍራት ያለብን ይላል ወጣቱ። የውይይቱ ዓላማ ወጣቱ የራሱን አመለካከት እንዲቀይር ሲሆን፣ ኹሉም ራሱን ከራሱ ማስታረቅ እንደሚጠበቅበትም ይናገራል።

ሠላምና ልማት ማዕከል ሠላምን ለማምጣት እንደሚሠራ የሚመሰክረው ሶፎንያስ፣ እውነትን በመግለጥ ሐሰት አቅም እንዲያጣ ለማድረግ ቅን ልቦና ያላቸው ወጣቶችን ለማፍራት ይጥራል። ቀጣዩ ትውልድ እኛን ወቃሽ ከመሆኑ በፊት ብዙ መሥራት ይጠበቅብናል የሚል ሲሆን፣ ወጣቱ ተበላሽቶ ከቀረ ማኅበረሰቡም ይበላሻል ይላል።

በወጣቶች ላይ የሚሠራ ማናቸውም የማቀራረብ ሥራ የሌሎች ተሳትፎ ከሌለው ያን ያህል ውጤት ላያመጣ ይችላል ያለው ይህ ወጣት፣ የሚዲያዎችና የአንቂ ሰዎች ሚና ከፍተኛ በመሆኑ ኹሉም ሊተባበር እንደሚገባ አጽንዖት ሠጥቶ ይናገራል። ኹላችንም ሳናውቀው ዘረኛ ልንሆን እንችላለን ያለ ሲሆን፣ በተደጋጋሚ ስለመርዝ የሚሠማ ራሱ መርዝ ሊረጭ ስለሚችል ጆሮ የምንሰጣቸውን ሚዲያዎችንም ሆነ ሰዎችን መምረጥ ይገባናል ብሏል። አብዛኛው አማኝ የሆነባት አገር እንደመኖራችን የሚያስታርቁ የኃይማኖት አባቶቻችንንም ብንሰማ መልካም ይሆናል ሲል ምክሩን ይለግሳል።

ማዕከሉ ባሰናዳው መድረክ አስተባባሪ እንደመሆኑ ወጣቶቹ ወንድማማቾች እንደሆኑ እንዲያውቁ ተደርጓል ያለን ሶፎንያስ፣ በምንም ጉዳይ የሚነሳ አለመግባባት ቅን ልቦና ካለ እንደሚፈታ የውይይት መድረኩ አስተምሮናል ሲል ይገልጻል። የሠላምና ልማት ማዕከል ሥራ ሕክምና ነው ያለ ሲሆን፣ ሠልጣኞች የክፉ አስተሳሰብ ሐኪሞች መሆን አሊያም ከበሽታቸው ያገገሙ ሕመምተኞች መሆን እንደሚጠበቅባቸው ይናገራል።


ቅጽ 4 ቁጥር 179 ሚያዝያ 1 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here