ኢትዮጵያ በፖለቲካው አለመረጋጋት ሳቢያ በኢኮኖሚም ሆነ በሰብዓዊ መብት ጥሰት ረገድ ወርዳበት የማታውቅ አዘቅት ውስጥ መግባቷን እያደር እየተመለከትነው ያለ ሐቅ ነው። የታጠቁ ኃይሎች የሚፈጥሩት መከራና እንግልት ኅብረተሰቡ ላይ የሚያሳድረው ጫና እየበረታ ባለበት በዚህ ወቅት፣ አለመግባባቶችን ሊያስወግድና የሕዝብን ሠላም በቀዳሚነት ሊያስጠብቅ ይገባው የነበረው መንግሥት በራሱ ጎራ ለይቶ መተላለቅ የጀመረበት ወቅት ላይ እንገኛለን።
ለብዙዎች ዕልቂት ምክንያት የሆነው መደበኛ የሚባለው የሰሜኑ ጦርነት ሳይቋጭ በአንድ ወገን ተሰልፎ ሲዋጋ የነበረ ቡድን እርስ በርሱ ለመጣላት በድጋሚ ሲወቃቀስ እየተሠማ ነው። ሕወሓትን ከሥልጣን ለማስወገድ ስምምነት ላይ የነበሩና አዲስ ፓርቲን አቋቋምን መንግሥት መሠረትን ያሉ ፖለቲከኞች፣ አጠፋነው ያሉትን የዘር ልዩነት እንደገና እየሳቡ እርስ በርስ በግልፅ ሲተቻቹ ዕየታየ፣ እየተሰማ ነው።
በአንድ አካባቢ ለተፈጠረ ክስተት፣ ኹሉንም ሊያሳትፍ የሚችል ግጭት ውስጥ ሊያስገባ የሚችል መግለጫና አስተያየት እየተሠጠ መሆኑንም እየተከታተልን እንገኛለን። ይህ ዓይነት ጡንቻ የመለካካት ሒደት ወደሚቀጥለው ደረጃ ከተሸጋገረ የኹለቱን ተገማማች ኃይላት አቅም የሚያሟጥጥ ብቻ ሳይሆን፣ መዘዙ ለኹሉም ኢትዮጵያዊ የሚተርፍ መሆኑን መንግሥት ነኝ ብሎ የሚያስብ አካል ሊረዳው እንደሚገባ አዲስ ማለዳ ማሳሰብ ትወዳለች።
በርካታ ቁጥር ያለው ሕዝብን በውስጣቸው የያዙት እነዚህ ክልሎች እስካሁን በካድሬዎቻቸው ሲያደርጉት የነበረው የእርስ በርስ ሽኩቻ ምን ያህል ሕዝቡን እያራራቀው እንደሆነ፣ የተለያዩ ክስተቶች በተፈጠሩ ወቅት የተመለከትናቸው የማኅበረሰቡ ተግባራት አመላካች ናቸው። በቋፍ ላይ ያለ ሕዝብን ይዞ የታጠቀና ወገኑን ያስታጠቀ አካል ለከት የሌለው የቃላት መጠዛጠዝ ውስጥ መግባቱ የሚያስፈራው ኹላችንንም መሆን አለበት።
ኩሬዋ ውስጥ ሆና እሳቱ አይደርስብኝም ብላ ስትዘባበት እንደነበረችው እንቁራሪት፣ መቃጠል ላይቀርላቸው ባለሥልጣናቱ ሕዝቡን ይዘው ለመጠፋፋት የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ታሪካቸውን ላስተዋለ በቀላሉ እንደማይበርድ ግልፅ ነው። ኹለቱም አካላት ተያይዘው እንዲጠፉ የሚፈልግ አካል በርካታ እንደመሆኑ፣ ለፖለቲካ ሲሉ ሕዝብን የሚማግዱበት እሳት እራሳቸውንም አመድ ሊያደርጋቸው እንደሚችል ሊገነዘቡት ይገባል።
ብዙዎች እንደሚሉት አገርን የሚያጠፋ ተግባር ላይ የተሳተፉ ባለሥልጣናትም ሆኑ ሹመኞች ክፉ ነገር ሊደርስባቸው ቢል ሕዝብን አጋፍጠው ጥለውት ሊሔዱ እንደሚችሉ ለማሳየት በቅርቡ ጦርነቱ ወደ መሀል አገር ሲደርስ አንዳንዶቹ አደረጉት የተባለውን ማውሳቱ በቂ ነው። ኹሉም ጥሎ መሸሽ ይቻለዋል ባይባል እንኳን በዚህ ቴክኖሎጂ በተራቀቀበት ወቅት ተደብቆ መቆየትም ሆነ የሚያስጥል ኃያል ማግኘት ከባድ እንደሚሆን የዓለምን ወቅታዊ ኹኔታ ተረድተው አካሔዳቸውን እንዲያስተካክሉ አዲስ ማለዳ ትመክራለች።
የአማራና ኦሮሚያ ክልል ባለሥልጣናትም ሆኑ ነዋሪዎች እንዳይቀራረቡ ብቻ ሳይሆን በባላንጣነት እንዲተያዩ ለዘመናት ሲሠራበት የነበረው አስተሳሰብ ፍሬ አፍርቶ የውጤቱ ጎምዛዛነት እየታየ ባለበት በዚህ ዘመን፣ ኹለቱን ሕዝቦች እርስበርስ ለማቀራረብ ብዙ ተለፍቶ ነበር። እንቦጭን ለማስወገድ በሚል የተሠራው የማቀራረብና ጥላቻን የማጥፋት ተግባር ፖለቲካዊ ተልዕኮ ስለነበር ሥር ሳይሰድ በአጭሩ ተቋጭቷል። የጋራ ጠላትን ለማስወገድ በሚል አንድነት መሥርቶ የነበረው ጎራ፣ ከበላይ አመራሮቹ በስተቀር አንድ ላይ መሥራት ሲቸገር ማየት እየተለመደ መጥቷል።
በሱማሌና ኦሮሚያ ክልል ባለሥልጣናት መካከል ድሬዳዋና ሐረር ላይ በይገባኛል ሴራ የጀመረው አለመግባባት ከካድሬ አልፎ ለብዙዎች ሞትና ለበርካቶች መፈናቀል ምክንያት የሆነው በአመራሩ ጦስ መሆኑን ማንም የሚያውቀው ሐቅ ነው። ከዚህም ባለፈ፣ በሚሊዮኖች እንዲፈናቀሉ የተደረገበት የጉጂውም ሆነ የሲዳማው፣ የአፋሩም ሆና የሱማሌው ግጭት አመራሮች የፈጠሩት እንደሆነ ግልፅ ነው። በወለጋና በቤኒሻንጉል በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን ለስቃይ፣ በርካቶችን ለሞትና መፈናቀል የዳረገውና አሁንም ያልበረደው ክስተት በባለሥልጣናቱ ድክመት የቀጠለ መሆኑን ለማወቅ መርማሪ አይሻም።
እርስ በርስ እየታየ ያለው ሽኩቻ አድማሱን እያሰፋና ሕዝብን ነጥሎ እያፈራረጀ መተላለቅ ያስከተለው በሹመኞች እንዝህላልነት እንደሆነ አዲስ ማለዳ ማስገንዘብ ትፈልጋለች። በሥልጣን ጥመኝነት እና በግዛት ማስፋፋት የሚነሱ የማኅበረሰብም ሆኑ የፖለቲከኞች ጥያቄዎች በአግባቡ፣ በተገቢው መንገድና ፍጥነት ምላሽ ማግኘት ባለመቻላቸው ይህ ኹሉ እየደረሰብን መሆኑ ሊታወቅ ግድ ይላል።
በተረኛ አምባገነንነት የሚታማው የኦሮሚያ ብልጽግና መንግሥት ሕወሓት ይኮነንበት የነበረውን ተግባር እየደገመው ስለመሆኑ ሲነገር መስማት እየተለመደ ነው። ከኹሉም ከአጎራባች ክልሎች ጋር በሠላም መቆየት እንደተሳነው የሚነገርለት ክልሉ፣ በባለሥልጣናቱ አማካይነት ወደማይመለስበት ቁልቁለት እየተንደረደረ፣ ከኹሉም ጋር ለመላተም እየተፋጠጠ ይገኛል። ከሱማሌ፣ አፋር፣ አማራ፣ ሲዳማ፣ ደቡብ፣ ቤኒሻንጉል አንዲሁም በግልፅ ባይታይም ከጋምቤላ ክልል አመራሮች ጋር ውዝግብ ውስጥ የቆየው ይህ ክልል፣ ከክልሎቹ ጋር እንዲህ ዓይነት የመጠፋፋት አቅጣጫ የያዘበትን ምክንያት ሊያጤነው ይገባል። ክልሉና የክልሉ አመራር ነገሮች ሳይረፍዱ ከሹመኞች ጋር ብቻ ሳይሆን ተራ እየተባለ ከሚገለጸው ሕዝብ ጋር ያለውንም ግንኙነት እያሻከረ እንዳይሔድ ለማድረግ መሥራት ይኖርባቸዋል።
ከአዲስ አበባ፣ ድሬዳዋና ሐረር ሕዝቦች ጋር ያለው ግንኙነት ምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ በመገምገም፣ ከክልሉ ውጭ ካሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ብቻ ሳይሆን፣ ውስጡ ከሚኖሩ የተለያዩ ማኅበረሰቦች ጋር ያለውን ግንኙነትም ሊያጤን ይገባዋል ስትል አዲስ ማለዳ ትመክራለች።
ባለሥልጣናቱ የክልሉ ሕዝብ ከሌሎች ሕዝቦች ጋር በጋራ እንዳይኖር ከሚያደርጉ የማንአለብኝነት ተግባር ሊቆጠቡ ይገባል። ነዋሪውም ፖለቲከኞቹን ዝም ከማለት ይልቅ ከሌሎች ሕዝቦች ጋር አታናቁሩን፣ ሥማችንም በእናንተ ሳቢያ አይጉደፍ ሊላቸው ይገባል።
እንዲህ ዓይነት ሕዝብን ከሕዝብ ሊያጋጭ የሚችል ተግባር በአንድ ክልል ብቻ ሳይሆን በሌሎችም ክልሎች ይፈፀማል። የአንዱ ክልል ተግባር አፍጦ ታዬ እንጂ የራሳቸውን ስንፍና አቅመ-ደካማነት በሌላ አመካኝቶ የጋራ ጠላት ለመፈለግ የሚቦዝኑ የክልል ፖለቲከኞች እንዳሉ ለዘመናት አብሮ የኖረው ሕዝብ ይረዳል።
በሲዳማና ኦሮሚያ፣ በቤኒሻንጉልና ኦሮሚያ፣ በአማራና ኦሮሚያ፣ በአማራና ቤኒሻንጉል፣ በደቡብና ኦሮሚያ ባለሥልጣናት መካከል፣ በሚነሱ አለመግባባቶች በሕዝብ ዘንድ ሠሞኑን የደረሱ ግጭቶችን እየተመለከትን እንገኛለን። ይህ ኹሉ ችግር የተከሠተው በሹመኞቹ ቆስቋሽነት ነው ብሎ በማስረጃ አስደግፎ መኮነን ባይቻልም፣ ችግሮቹን ወዲያውኑ ማስቆምም ሆነ መጀመሪያውኑም እዚህ ደረጃ እንዳይደርሱ የማድረግ ኃላፊነታቸውን ቢያንስ በአግባቡ ፖለቲከኞቹ እንዳልተወጡ አመላካች ነው።
ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ግጭቶች ኹሉ በባለሥልጣናቱ እኩይ ሴራና ድክመት ብቻ የሚከሠቱ ናቸው ማለት አይቻልም። አንዳንድ ጊዜም በማኅበረሰብ አባላት መካከል የሚነሱ አነስተኛ ጠቦች ወደለየለት የጎሳና ሕዝብ ግጭት የሚያመሩበት ኹነት እንዳለ ይስተዋላል። በቅርቡ በመኪና አደጋ ሳቢያ የተፈጸመ የበቀል ዕርምጃ ወደ ጎሳ ግጭት ያመራበትን አጋጣሚ ማውሳት ይቻላል። እንደነዚህ ዓይነት እየተባባሰ የሚሔድ ግጭትን ማስቀረት የማይቻለው በመጀመሪያ ሕዝቡ እርስ በርሱ ተፈራርጆ ተራርቆ ለአገዛዝ እንዲመች ተደርጎ ተለያይቶ እንዲኖር ስለተደረገ እንደሆነ አዲስ ማለዳ ታምናለች።
አርቲስት ሐጫሉ ሁንዴሳ የተገደለ ሠሞን፣ እንዲሁም ጀዋር መሐመድ “ተከበብኩ አለ” የተባለ ወቅት ሕዝብ አብሮት ለዘመናት በኖረ ወንድሙ ላይ እንዲነሳ ያደረገው፣ በቀደመው ጊዜ በተሠበከ የጥላቻ ትርክት መሆኑን ማንም ያውቃል። ይህ ቢሆንም ግን ለክፉ አስተሳሰብና ተግባር የድሮው ማስተባበያ እየሆነ በተመሳሳይ መንገድ እንዲቀጥል ሊደረግ አይገባም።
በቅርብ ጊዜ የአገራችን ኹኔታ ያልተማሩ ባለሥልጣናት፣ በተለይ በአንድ ፓርቲ ውስጥ ታቅፈናል የሚሉት፣ ሕዝቡን ለቀጣይ ዕልቂት ሊዳርጉት አለመግባባታቸውን ወደአደባባይ በመግለጫ ሲያወጡት እየተመለከትን ነው። እንደሌላው ተግባራቸው ይህንንም በምስጢር ሊያደርጉት ሲገባ፣ አለመስማማታቸውን በሕዝብ ግጭት ሊያሳርጉ ያቀዱ ይመስል ማስጠንቀቂያ መሰል መግለጫዎቻቸውን ለሕዝብ የሚያደርሱት በኋላ ላይ ብዬ ነበር ብሎ ለመወቃቀስ ይመስላል።
ነዋሪው ለገበያ ነቅሎ ሲወጣ “አትሒዱ ቤታችሁ እንዳይቃጠል” እያለች ስታስጠነቅቅ የነበረች የአእምሮ በሽተኛ፣ ሰው አልሰማ ሲላት ቤቶቹን ራሷ አቃጥላ በመሸሽ ፈንታ “አላልኳችሁም ነበር” እንዳለችው፣ የዘመናችንም ባለሥልጣናት እርስ በርስ ሲያስጠነቅቁ ማየቱ ግራ የሚያጋባ ነው።
ቅጽ 4 ቁጥር 179 ሚያዝያ 1 2014



