በምሥረታ ላይ የሚገኘው የጃኖ ባንክ አመራሮች ቢሮ ዘግተው መጥፋታቸውን ባለድርሻዎች ገለጹ

0
761

አመራሮቹ ብሔራዊ ባንክ ውሳኔ ስላልሰጠን ነው ብለዋል

በምሥረታ ላይ የሚገኘው የጃኖ ባንክ አመራሮች ቢሮ ዘግተው መጥፋታቸውን ባለድርሻዎች ገለጹ

በምሥረታ ላይ የሚገኘው የጃኖ ባንክ አመራሮችና ሠራተኞች፣ የባንኩ ባለድርሻዎች የገዙትን አክሲዮን ገንዘብ ሳይመልሱ ተከራይተውት የነበረውን ቢሮ ለቀው እንደጠፉና ስልካቸውንም እንዳጠፉባቸው አክሲዎን የገዙ ሰዎች ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።
ቅሬታ አቅራቢዎቹ እንደሚሉት፣ ጃኖ ባንክን ለመመስረት ከኹለት ዓመት በፊት አክሲዮን መሸጥ የተጀመረ ሲሆን፣ የተወሰነ ከተሸጠ በኋላ ብሔራዊ ባንክ አዲስ የሚመሠረቱ ባንኮች የመነሻ ካፒታላቸው አምስት ቢሊዮን ብር ማድረስ እንዳለባቸው መመሪያ ማውጣቱን ተክትሎ በምሥረታ ላይ የነበረው ባንክ ይህንን ማሟላት ባለመቻሉ ወደ ማይክሮ ፋይናንስ እንዲወርድ ተወስኖ ነበር።

ነገር ግን፣ በምሥረታ ላይ የነበረው ጃኖ ባንክ ይህን ለማድረግ መሥራቾችን እንዲያስፍርም ከብሔራዊ ባንክ ትዕዛዝ ቢሰጠውም፣ አብዛኛዎቹ መሥራቾች የባንኩ ምስረታ ወደ ማይክሮ ፋይናንስ በመቀየሩ ላይ አለመስማማታቸው ተሠምቷል።
በዚህም፣ መሥራቾቹ ብሔራዊ ባንክ የገባው ሰነድ ፈርሶ ገንዘባቸው እንዲመለስ ቢፈልጉም አመራሮቹን ማግኘት እንዳልቻሉ ጠቅሰው መፍትሔ ይሰጠን እያሉ ነው።

አዲስ ማለዳ ስለጉዳዩ ለጃኖ ባንክ መስራቾች ሰብሳቢ መንገሻ አድማሱ (ፕ/ር) ጥያቄ ያቀረበች ሲሆን፣ ብሔራዊ ባንክ ትዕዛዝ ሲሰጥ “ከቴሌ ጋር ተነጋግረን አባሉን ጠይቀን፣ አንዳንዶቹ ምንም መለስ አልሰጡም። አንዳንዶቹ ገንዘቡ ይመለስልን እያሉ አሉ። አንዳንዶቹ ደግሞ በማይክሮ ፋይናንስ ሒደን እንቀጥላለን” የሚል ምላሽ ነው የሠጡን ብለዋል።

ቅሬታ አቅራቢዎቹ በበኩላቸው፣ ብሔራዊ ባንክ በምሥረታ ላይ የነበረውን ጃኖ ባንክን ወደ ማይክሮ ፈይናንስ ለማውረድ ደንበኞችን ማስፈረም እንዳለበት ቢገልጽም ባልድርሻዎቹ ግን እንዳልተሠማሙ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
መንገሻ አክለውም፣ “ሙሉ መረጃ ለብሔራዊ ባንክ ሠጥተን ብሔራዊ ባንክ አሁን ማይክሮ ፋይናንስ ሆናችሁ መቀጠል ትችላላችሁ ብሎ መፍቀድ ካለበት ጊዜ ከሦስት ወር በላይ ሆኖታል። እየጠበቅን ነው” ብለዋል።

ቅሬታ አቅራቢዎቹ የጃኖ ባንክ ወደ ማይክሮ ፋይናንስ እንዲወርድ አለመፍቀዳቸውን የጠቀሱ ሲሆን፣ ሰብሳቢውም አንዳንዶች “ገንዘቡ ይመለስልን ያሉ አሉ” ብለዋል። ነገር ግን ገንዘባቸው እንዲመለስ ለፈለጉ አካላት ገንዘቡ ሳይመለስ የብሔራዊ ባንክን ውሳኔ እየጠበቁ መሆናቸውን ነው መንገሻ የገለጹት።

“ገንዘባቸው ያለው በባንክ እጅ ነው፤ በማንም እጅ ሊገባ አይችልም። ይመለስልን ያሉት ይሠጣቸዋል። እንቀጥላለን ያሉት ይቀጥላሉ” ሲሉም ነው ለአዲስ ማለዳ የተናገሩት። አክለውም፣ “አይቀጥልም ካለም ደግሞ በእንደዚህ ዓይነት ቦታ እየሔዳችሁ ውሰዱ የሚል ትዕዛዝ የሚሠጠው ብሔራዊ ባንክ ነው” ሲሉ ሰብሳቢው ተናግረዋል።

ቅሬታ አቅራቢዎቹ በምሥረታ ላይ የነበረው ጃኖ ባንክ ሠራተኞች ቢሮ መልቀቃቸውና ስልክ ማጥፋታቸውን የጠቆሙት ትክክል መሆኑን ያመኑት ሰብሳቢው፣ ሠራተኞቹ “የቢሮ ስልክ ነው የያዙት፤ መመለስ ነበረባቸው። ለኹሉም እየነገርኩ ነው፤ እናስተካክላለን የሚል ምላሽ ሠጥተዋል” ብለዋል።

ቅሬታ አቅራቢዎቹ፣ “የገዛነውን አክሲዮን የት እንዳደረሱት ሳይታወቅ ተከራይተው ከነበረበት ቦሌ መድኃኒዓለም ሕንጻ 7ኛ ፎቅ ወጥተው ሠራተኞችና አመራሮች በሙሉ ስልካቸውን ዘግተው ጠፍተዋል” ብለዋል።
ሰብሳቢው በበኩላቸው፣ ለመድኃኒዓለም ‹ሞል› በወር 25 ሺሕ ብር እየከፈሉ የነበረ በመሆኑና ይሄ ደግሞ ገና በሒደት ላይ ያለ ባንክ ስለሆነ ወጪው ከመሥራቾች ገንዘብ ስለሚከፈል ወጪ ለመቀነስ ሲባል ቢሮ እንደለቀቁ ተናግረዋል።

ሰብሳቢው አክለውም፣ “የትም ይሁን የትም ቁልፍ ይዘው ጠፉ የተባሉት ሠራተኞች እኔ ያቀረብኩትን ጥያቄ መመለስ አለባቸው፤ እኔ አስተካክላለሁ። ቀጣይ ሳምንት ይህን መፍትሔ እናደርጋለን” ሲሉ ገልጸዋል።
አዲስ ማለዳ ከብሔራዊ ባንክ በኩል ያገኘውችው ምላሽ እንደሚያመለክተው ከሆነ፣ አክሲዎን የገዙ ሰዎች ገንዘባቸው እንደማይቀርና ውሳኔውን በተመለከተ ግን ጉዳዩ በጥልቀት መታየት ያለበት መሆኑን ነው።


ቅጽ 4 ቁጥር 179 ሚያዝያ 1 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here