ማክሰኞ ሚያዝያ 4 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) ሰሞኑን በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ አንዳንድ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሃይማኖታዊ እንቅስቃሴዎችን በተመለከተ ጉዳዩን በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በማገናኘት ሲሰራጭ መቆየቱ የሚታወስ ሲሆን፤ የትምህርት ሚኒስቴር በአበባ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የተነሱ ቅሬታዎች በህገ መንግስቱ መሰረት የሚስተናገዱ ሆነው፤ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከተው ግን የአዲስ አበባ ት/ቢሮን እንጂ የትምህርት ሚኒስቴር አለመሆኑን አስታውቋል።
እንደዚህ ያሉ ቅሬታዎች የአገሪቱን የፌደራል ሥርዓት አሰራር በውል ካለመረዳት የመጣ ሊሆን እንደሚችል በመገመት፤ በፌደራል የትምህርት ሚኒስቴርና በክልሎች በሚተዳደሩ የአንደኛና ኹለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች አሰራር የግንኙነት ማዕቀፍ መረዳት ለሚፈልጉ ወገኖቻችን በአጭሩ ገለፃ ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ ማግኘቱን ሚኒስቴሩ ገልጿል።
የአስፈፃሚ አካላት ስልጣንና ተግባራት ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር 1263/2014 አንቀፅ 34 ለትምህርት ሚኒስቴር የተሰጡ ስልጣንና ተግባራትን ያከናውናል እንጂ የስልጣን ተዋረዱን ጠብቆ ላልመጣና ከክልሉ ትምህርት ቢሮ አቅም በላይ ባልሆነ ጉዳይ ትምህርት ሚኒስቴር ጣልቃ የሚገባበት ምንም አይነት አሰራር የለም ሲልም ትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል።
ስለሆነም ከሰሞኑ ከሀይማኖታዊ ጉዳይ ጋር በተያያዘ በአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የተነሱ ቅሬታዎች በህገ መንግስቱ መሰረት የሚስተናገዱ ሆነው፤ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከተው ግን የአዲስ አበባ ት/ቢሮን እንጂ የትምህርት ሚኒስቴር አለመሆኑን የገለፀው የትምህርት ሚኒስቴር፤ የሚኒስቴሩን ስልጣንና ተግባራት እንደሚከተለው አስቀምጧል፡-
ሀ/ የአጠቃላይና የከፍተኛ ትምህርት፣ ፖሊሲዎችን፣ ስትራቴጂዎች፣ ህጎችና እና ፕሮግራሞች ይቀርጻል፣ ለአፈጻጸሙ ከአገራዊ የልማት አቅጣጫ ጋር የተጣጣመ ዝርዝር መርኃ ግብር ያዘጋጃል፤ በሚመለከተው አካል ሲፀድቅም ተግባራዊ ያደርጋል፤
ለ/ የአጠቃላይና የከፍተኛ ትምህርት የሥርዓተ-ትምህርት ማዕቀፍ ያዘጋጃል፣ የትምህርት እና የትምህርት ተቋማትን ስታንዳርድ ያወጣል፣ አገራዊ የብቃት ማዕቀፍ ያዘጋጃል፣ በሥራ ላይ መዋሉንም ያረጋግጣል፤
ሐ/ የአጠቃላይና ከፍተኛ ትምህርት ፖሊሲና ሥርዓተ-ትምህርት መሠረት ያደረጉ አገር አቀፍ ፈተናዎች ዝግጅት፣ ሪከርድ መያዝና የምስክር ወረቀት የመስጠት ሂደቶችን በበላይነት ያስተባብራል፤
መ/ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በጥናትና ምርምር የጎለበቱ እንዲሆኑ የሚያስችል ስልት ይነድፋል፣ ይተገብራል፤ የጥናትና ምርምር ውጤቶች በሥራ ላይ የሚውሉበትን መንገድ ያመቻቻል፤
ሠ/ ከኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በከፍተኛ ትምህርትና የምርምር ተቋማት እና በኢንዱስትሪው ዘርፍ መካከል ለምርምርና ቴክኖሎጂ ልማት እንቅስቃሴ የሚያግዝ ምቹ የእርስበርስ ትስስርና ቅንጅታዊ አሠራር እንዲፈጠር ሁኔታዎችን ያመቻቻል፤
ረ/ የመንግሥት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን አፈጻጸም ይከታተላል፤
ሰ/ የመንግሥት ከፍተኛ ትምህርት ተማሪዎች ቅበላና ምደባ አፈጻጸም ፍትሃዊ መሆኑን ያረጋግጣል፤
ሸ/ የአጠቃላይ እና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሊያሟሉ የሚገባቸውን ደረጃ መውጣቱን ያረጋግጣል፤ በተቋማቱ ጥራትና አግባብነት ያለው ትምህርትመሠጠቱን ይከታተላል፤
ቀ/ ጥራቱን የጠበቀ የከፍተኛ ትምህርት እንዲስፋፋ ያደርጋል፣ በበላይነት ይመራል፤
በ/ ትምህርትን በተመለከተ አገራዊ የአህዝቦት ተግባራትን ያከናውናል፡፡
ከህገ መንግስቱ አንፃር፡-
የብሄራዊ ፖሊሲ መርሆችና አላማዎች አንቀፅ 90 ንዑስ አንቀፅ 2 መሰረት ትምህርት በማንኛውም ረገድ ከሃይማኖት፣ ከፖለቲካ አመለካከትና ከባህላዊ ተፅዕኖዎች ነፃ በሆነ መንገድ መካሄድ አለበት የሚል የህገ-መንግስቱ አስገዳጅ ድንጋጌዎች ውስጥ ተካትቶ እንደሚገኝ መረዳት እንደሚያስፈልግም የትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል።
_____________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n



