የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ዴቪድ ሳተርፊልድ እና ምክትላቸው ዛሬ አዲስ አበባ እንደሚገቡ ተገለጸ

0
1012

ዕረቡ ሚያዝያ 5 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ዴቪድ ሳተርፊልድ እና ምክትል ልዩ መልዕክተኛ የሆኑት ፔይቶን ኖፕፍ ዛሬ ሚያዝያ 5 ቀን 2014 አዲስ አበባ፤ ኢትዮጵያ እንደሚገቡ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።

ልዩ መልዕክተኛው የአምባሳደር ዴቪድ ሳተርፊልድ እና የምክትላቸው ፓይተን ኖፍ በጉብኝታቸው ከኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት፣ የሰብአዊ ድርጅቶች ተወካዮች እና የዲፕሎማቲክ አጋሮች ጋር በመገናኘት ይወያያሉ ተብሏል።

በተጨማሪም በዚህ ጉብኝት ጦርነትን ለማስቆም፣ ያልተገደበ የሰብአዊ አገልግሎት አቅርቦት እንዲኖር፣ የሰብአዊ መብት ረገጣ እና የኹሉም ተዋናዮች ጥሰቶች ላይ ግልፅ ምርመራ እንዲደረግ እና በኢትዮጵያ ያለውን ግጭት በድርድር ለመፍታት አሜሪካ የምታደርገውን ጥረት ያስቀጥላሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።

የቀድሞውን የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ጄፍሪ ፌልትማንን በቅርቡ የተኩት ሳተርፊልድ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ይህ የመጀመሪያቸው አይደለም።

አምባሳደሩ መጋቢት 12 እና 13/2014 አዲስ አበባ ገብተው ለኹለት ቀናት ባደረጉት ቆይታ ከአፍሪካ ኅብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ኦሉሴጉን ኦባሳንጆን፣ ከኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ውይይት አድርገው እንደነበር ይታወሳል።

በተያያዘም የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛው ዴቪድ ሳተርፊልድ ከክረምት በፊት ስልጣናቸውን እንደሚለቁ ጉዳዩን በቅርብ ከሚያውቁ ምንጮች ሰምቻለሁ ሲል ሮይተርስ ዘግቧል።

ዛሬ አብረዋቸው አዲስ አበባ እንደሚገቡ የሚጠበቁት ምክትላቸው ፔይቶን ኖፕፍ ቦታውን እንደሚረከቡ እንደሚጠበቅም በዘገባው ተመላክቷል።
_____
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here