ዕረቡ ሚያዝያ 5 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) ጣራ የነካው የሲሚንቶ ዋጋ ለማረጋጋት መንግስት የቅዳሜና እሁድ ገበያ (”ሰንዴይ ማርኬት“) ሊጀመር መሆኑን የንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታውቋል።
የንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ ሀሰን መሀመድ ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንደተናገሩት፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በውል ባልታወቀ ምክንያት የሲሚንቶ ዋጋ በእጥፍ መጨመሩን ገልፀው፤ ይህንን ለመቆጣጠር መንግስት የተለያዩ የቁጥጥር ሥራዎች እየሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡
ለሲሚንቶ ዋጋ መናር እንደ ምክንያትም የግብአት እጥረት፣ ህገወጥ ደላሎች፣ የጥቅም ትስስት የፈጠሩ ነጋዴዎች የሚፈጥሩት አሻጥር እና በተለያዩ አካባቢዎች ያለው የጸጥታ ሁኔታዎች መሆናቸውን ሚኒስትር ዴኤታው ገልፀዋል፡፡
መሰረታዊ የፍጆታ ምርቶችን ለተጠቃሚው በቀጥታ ለማድረስ የተጀመረው የቅዳሜ እና እሁድ ገበያ በርካታ ስኬቶች ታይተውበታል ያሉት ሀሰን፤ የሲሚንቶ ገበያም ለመጀመር ዝግጅት እያደረግን እንገኛለን ሲሉ ለኢትዮ ኤፍ ኤም ተናግረዋል፡፡
ህገወጥ ደላሎችን ለመቆጣጠር እና ተጠቃሚው በቀጥታ የሲሚንቶ ምርት ከአምራች ድርጅቶች የሚያገኙበትን ሁኔታ ለማመቻቸት የዝግጅት ሥራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ ነው የተባለው፡፡
በአገሪቱ ከ18 በላይ የሲሚንቶ አምራቾች ቢኖሩም፤ በሙሉ አቅማቸው እያመረቱ የሚገኙ ከአራት ወይም ከአምስት አይበልጡም ሲሉም ነው ሚኒስትር ዴኤታው ያስረዱት፡፡
_____________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n




