ሴቶች ይበረታታሉ!

0
785

“ሲቄ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ‹አለንጋ› የሚል ትርጉም አለው። በገዳ ትውፊታዊ አስተዳደር ውስጥ በባሏ ጥቃት የደረሰባት ሚስት፣ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ባሏ ላይ የካሣ ውሳኔ የምታሳልፍበት ስርዓት ሲቄ ይባላል።

ይህን ሙግት እንዴት ታይዋለሽ? አንዳንድ የሥራ ማስታወቂያዎች በዝርዝራቸው ግርጌ ላይ ‹ሴቶች ይበረታታሉ› ይላሉ። በዚህ ነጥብ የማይስማሙ ሴቶች ጥቂት አይደሉም። እነዚህ ሴቶች ‹ለምን የተለየ ማበረታቻ ይደረግልናል፤ ከፈለግን መጥተን እንወዳደራለን።› የሚልና ተያያዠ ሐሳብ ያነሳሉ።

በሌላ በኩል ‹አዎን! ይበረታታሉ መባል አለበት። ምክንያቱም አንዳንድ ተቋማት ሴቶችን ለመቅጠር ፈቃደኛ አይሆኑም። በተለያየ ምክንያት ቅድሚያ የሚሰጡት ለወንዱ ነው። በዛም ላይ ሴቶች ደፈር ብለው ላይሄዱ ይችላሉ። ስለዚህ መበረታታት ጥሩ ነው።›› ብለው የሚሞግቱም ብዙ ናቸው። ከኹለቱም በተለየ ደግሞ ‹ይበረታታሉ ምን ማለት ነው? ቅድሚያ ይሰጣቸዋል ማለት ነው ወይስ ለውድድር እንዲያመለክቱ ይጠየቃሉ? ብለው ሌላ ጥያቄ የሚያነሱም አሉ።

አንቺስ ምን ትያለሽ? ማበረታቻ ትፈልጊያለሽ ወይስ አያስፈልግም ከሚሉት ወገን ነሽ?

በኹለቱም ወገን እንየው። በእርግጥ ጉዳዩ እንደ ሴቱ ጠባይና አኳኋን ሊለያይ ይችላል። አንዳንዴ የተሰጣቸውን እድል በአንድ አፍ ብለው ተቀብለው የሚሠሩ፣ ከፍ ሲልም አንኳክተው እድል እንዲፈጠር የሚያደርጉ አሉ። በሌላ በኩል እውቀትና አቅም እያላቸውም በየጓዳ ቁጭ ብለው፣ አልችልም በሚል ፍርሃት አዘል ‹ትህትና› ውስጥ ሆነው እድሎችን የማይጠቀሙ ሴቶችም ጥቂት አይደሉም።

ቅድሚያ አሁን ባለንበት የሴቶች የመብት እኩልነት ሁኔታ ጋር በተያያዘ ‹ምን ይሠራል!?› ሊባል ይገባል ብዬ አላምንም። ‹ከዚህ በኋላ ለሴቶች ቅድሚያ መስጠት ይበቃል!› የምንለው በከተማ ብቻ ያለውን እንቅስቃሴ ተከትለን ሳይሆን አገር ዐቀፍ የሆነውን ምስል ተመልክተን ሊሆን ይገባል። በእርግጥ አሁን ላይ በምጣኔ ሀብት ድቀትና በኑሮ ውድነት፣ በሰላም ማጣትና በጦርነት መካከል ሴት ወንድ ሳይል ሁሉም እኩል ተጎጂና ተጠቂ ሆኗል። አዎን! የሴቶች ጫንቃ የተሸከመው ቀላል የማይባለውን እንደሆነ ግልጽ ነው።

ማበረታቻን ያሳንሳል ብለው የሚያስቡ ሰዎች አሉ። ግን እዛ ደረጃ ላይ ደርሰናል ለማለት ትልቅ ድፍረት ይጠይቃል። እንደ ማኅበረሰብም እንዲሠለጥን፣ እንዲያውቅና ከትላንቱ እንዲሻል ማበረታቻ የሚፈልግ ማኅበረሰብ ነው ያለን። በዛም ላይ እንዲያ ያሉ እድሎች ሲገኙ መጠቀም እንጂ መናቅ ተገቢ አይመስለኝም።

ዋናው መታወቅ ያለበት የሚመስለኝ ማበረታቻውን ሰጪው ወንድ አይደለም፣ ከሴቶች መብትን ሲነፍግ የቆየ ስርዓት እንጂ! በማበረታቻዎች ተጠቅሞ ለውጥ በማምጣት ጉዳዩን ከአጀንዳነት ማስነሳትና ማስረሳት እንደውም የተሻለ ውጤት ነው። የዛሬዋ ሴት መጣር ያለባትም የነገ ተከታይዋ ማበረታቻ የሚባል ነገር እንደነበር እስካታውቅ ድረስ የተሻለ አገር እንዲጠብቃት ማድረግን ነው። ያንን ለማድረግ ደግሞ ዛሬ ላይ ያሉ ማንኛውንም የተከፈቱም ሆነ ገርበብ ያሉ በሮችን መክፈት፤ ጥበብ በተሞላ የራስ መተማመን ከፍቶ መዝለቅና መሥራት ነው።
መቅደስ ቹቹ


ቅጽ 4 ቁጥር 180 ሚያዝያ 8 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here