ያልተጣጣመው የኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎትና አቅርቦት

0
1915

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ከኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ በመቀጠል ኹለተኛዋ ግዙፍ ኤሌክትሪክ የማመንጨት አቅም ያላት አገር መሆኗ ይነገራል።

ይሁን እንጂ የምታመነጨው የኤሌክትሪክ ኃይል አምስት ሺሕ ሜጋ ዋት እንደማይደርስና ይህም የአምራች ኢንዱስትሪዎችን ጨምሮ በአገሪቱ ያለውን መሠረታዊ የኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎት ለማሟላት በቂ ነው ለማለት እንደማያስደፍር ይነሳል።

ጥናቶች እንደሚጠቁሙት በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት ጅማሮ በርካታ ዓመታትን ያስቆጠረ ታሪክ ያለው ሲሆን፣ ዘርፉ ከስድስት ዐስርት ዓመታት በላይ ያስቆጠረ እንደመሆኑ ዘመናዊ ሊባል የሚችል የአገልግሎት ተቋም ደረጃ ላይ መድረስ ነበረበት።
በዚህም በተለይ ካለፉት ሦስት ዐስርት ዓመታት በፊት ከዘርፉ ሊገኝ የሚችለውን ጥቅም ማግኘት አዳጋች ሆኖ እንደቆየና በአብዛኞቹ የኢትዮጵያ ከተሞችም የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተደራሽነት ውስን የነበረበት፣ ኅብረተሰቡም ከዘርፉ በሚገኘው ጥቅም ሕይወቱን መለወጥ ያልቻለበት እንደነበር የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

ዘርፉ ወቅቱ የሚጠይቀውን የሰው ኃይልና የቴክኖሎጂ አቅም እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ሳይገነባ ቆይቷል። እንዲሁም አገሪቱ ባለፈችባቸው በተለያዩ መንግሥታት በተለያዩ መዋቅሮች ማለፉና ከዘርፉ የሚገኘውን ትርፍ ብቻ ታሳቢ ያደረገ አሰራር ያለው መሆኑ፣ አልፎም የአገልግሎቱን ጥራት ለማሻሻል የተደረጉ ጥረቶች አለመኖራቸው አሁን ላይ ላለው የኃይል አቅርቦትና ተደራሽነት ችግሮች መባባስ እንደምክንያት ይነሳል።

በዚህ ዘርፍ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት፣ የአገሪቱ የኢኮኖሚ እድገትና የሕዝብ ቁጥር እንዲሁም የኢኮኖሚው እድገት የፈጠረው የዜጎች የዘመናዊ ኑሮ መሻት የኤሌክትሪክ ፍላጎትን በከፍተኛ ደረጃ እያናረው ይገኛል። የአገሪቱ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት የሆነው ግብርናም ለኢንዱስትሪው ክፍለ ኢኮኖሚ ማደግ የራሱን ድርሻ በማበርከት ቦታውን ለማኑፋክቸሪንግና ለኢንዱስትሪ መልቀቅ መጀመሩ የኃይል ፍላጎትን እንዲያሻቅብ ምክንያት እየሆነ ነው።

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አዲስ አበባ ዲስትሪክት ለረዥም ዓመታት በማገልገል ላይ የሚገኙና ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ባለሙያ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያ ከብዙ አገሮች የበለጠ የኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎት ያለባት አገር ናት።

‹‹እንጀራ መጋገር በራሱ ብዙ ኃይል ይፈልጋል።›› ያሉት ባለሙያው፣ ‹‹ሌሎች ብዙ አገሮች የሚኖሩ ዜጎች እሳት ያልነካው ምግብ በስፋት ይጠቀማሉ። ኢትዮጵያ ውስጥ ግን በጣም ዝቀተኛ የሚባል ኑሮ የሚኖር ሰው ቤት ውስጥ የኤሌክትሪክ ምድጃ ማግኘት ይቻላል። ስለዚህም ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎት ያለባት አገር ናት።›› ብለዋል። አያይዘውም፣ የኃይል አቅርቦት ቢኖር እንኳን በስርጭት ችግር የተነሳ ኃይል ሳይቆራረጥ ለተጠቃሚዎች እንደማይደርስ ሐሳባቸውን ይገልጻሉ። የቆጣሪዎችና ማሰራጫ መስመሮች የመሸከም አቅም አናሳ መሆን ያለውን የኤሌክትሪክ ኃይል ምርት በአግባቡ ለመጠቀም አስቸጋሪ እንደሚያደርገውም ነው ያመላከቱት።

ተቋሙ የኃይል አቅርቦቱን ለማስፋት የአምስትና ስድስት ዓመት እቅድ ይዞ ሲነሳም፣ የማኅበረሰቡ የኃይል ፍላጎት በአንዴ በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚጨምር ጠቅሰው፣ ካለው ፍላጎት አንጻር የሚደረገው ማስፋፊያ አናሳ መሆኑን ጠቁመዋል።
በተጨማሪም፣ በኃይል ማስተላለፊያ ቁሳቁሶች ላይ በየጊዜው የሚከሰት ስርቆት የሚፈጸመው ኃይል እንዲቋረጥ በማድረግ ስለሆነ፣ የተሰረቁ ቁሳቁሶች የት እንደሚገቡ ሰፊ ጥናት ማድረግና ስርቆት በሚፈጽሙ አካላት ላይም አስተማሪ የሆነ ጠንካራ እርምጃ መውሰድ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል። የቤት ለቤት የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት ዝርጋታዎችም በባለሙያዎች አለመሠራታቸው ትልቅ ችግር እየሆነ መምጣቱንም አክለዋል።

መብራት በየጊዜው እንዲቆራረጥና ለቀናት ጠፍቶ እንዲቆይ ከሚያደርጉት ምክንያቶች መካከል የኃይል እጥረት ብቻ ዋናው ተጠቃሽ እንዳልሆነ ማሳያዎች አሉ። ሆኖም ከዕቅድና ከምህንድስና ጋር የሚያያዘው የቴክኒክ ሥራ ለኃይል መቆራረጥ ቀዳሚ ምክንያት መሆኑና አሁን ያለው የአገልግሎት አሰጣጥ፣ እንዲሁም የኃይል ስርዓት ቴክኖሎጂው የረቀቀበት ደረጃና ያለው አቅም እየተጣጣመ አለመሆኑ ይነሳል።

ስለሆነም፣ ከኤሌክትሪክ ማምረት፣ ማስተላለፍና ከማሰራጫ አቅም ጋር የተያያዙ ችግሮች የጎሉ ናቸው። በኢትዮጵያ ባለው ሁኔታ የስርጭት መስመሮች አቅም ከማስተላለፍያ መስመሮች አቅም ያነሰ ነው።

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ውስጥ የኤሌክትሪክ መሀንዲስ ሆነው የሚሠሩና ስሜ ባይጠቀስ ያሉ ባለሙያ በበኩላቸው፣ ‹‹ብዙ ዓመት የሠሩ ባለሙያዎች ሲናገሩ እንደምንሰማው›› ብለው እንደጠቀሱት፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ በርከት ያሉ ባለሙያዎች የኃይል መቆራረጥ ሲከሰት በአፋጣኝ ምላሽ በመስጠት ኅብረተሱቡን ከማገልገል ይልቅ ለሚከፈላቸው አበል ቅድሚያ የሚሰጡ ናቸው።

በጥንቃቄ ጉድለት የብዙ ባለሙያዎች ሕይወት አደጋ ላይ እንደሚወድቅ አንስተው፣ ይህም አንድም ቢሆን የሠለጠነ የሰው ኃይል ማጣት ለዘርፉ ትልቅ ኪሳራና ተግዳሮት ነው ብለዋል።

ባለሙያዎች እንደሚሉትም፣ አዳዲስ ኃይል ማመንጫዎች የሚሠሩት የሚፈለገውን የኤሌክትሪክ ኃይል ሊሸከም የሚችል የማስተላለፊያና የማከፋፈያ ኔትወርክ አቅም በሌለበት ሁኔታ ነው። ይህ በሌለበት የማኅበረሰቡ የኃይል ፍላጎትም በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ይገኛል።
ዓለም አቀፍ ተሞክሮ እንደሚያሳየው፤ የስርጭት አቅም ካለው የኃይል ፍላጎት አንጻር ኹለት እጥፍ በልጦ መገኘት አለበት። ይህ ማለት የሚመነጭ የኃይል አቅም አገልግሎት ላይ ሊውልና የስርጭት አቅም ሊሸከመው ከሚችለው የስርጭት ኔትወርክ አቅም ጋር ተመጣጣኝ መሆን ይኖርበታል። የኢትዮጵያ የኃይል ስርጭት ኔትወርክ ግን ከዚህ ጋር የማይጣጣም መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ።

በተለይ ደግሞ የኤሌክትሪክ ኃይል አስተላላፊ መስመሮች ጥገና ወቅቱን የጠበቀ አለመሆን ለኃይል መቆራረጥ ተቀዳሚ ምክንያት እንደሆነ ነው ለአዲስ ማለዳ አስተያየት የሰጡት ባለሞያ የሚናገሩት። ‹‹በሠለጠኑ አገራት የኃይል ማስተላለፊያ ምሰሶዎች የሚያገለግሉበት ዓመት ተጽፎ ይለጠፍባቸዋል፣ የአገልግሎት ዕድሜያቸው ሲያበቃም ይቀየራሉ። እኛ አገር ግን አንድም ምሰሶ ሳይወድቅ በፊት አይቀየርም።›› ነው ያሉት።

የመብራት ማስተላለፊያ ሽቦዎችን የተሸከሙ ብዙ ምሰሶዎችም ያረጁ፣ የተጣመሙና በሌላ እንጨት የተደገፉ መሆናቸውን መመልከት ይቻላል የሚሉት ባለሙያው፣ ከወደቁ በኋላም በሰው ሕይወትና በንብረት ላይ ከሚያደርሱት ኪሳራ ባለፈ ጥናት ተደርጎ እስከሚተኩ ለቀናት የኤሌክትሪክ ኃይል ተቋርጦ እንዲቆይ ይሆናል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮምዩኒኬሽን ዳይሬክተር ሞገስ መኮንን፣ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ካለው የኃይል ፍላጎት አንጻር ምንም ዓይነት ክፍተት የለም ሲሉ ነው ለአዲስ ማለዳ የተናገሩት። አገሪቱ 4 ሺሕ 515 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም ያላቸው ማመንጫ ጣቢያዎች እንዳሏት ጠቅሰውም፣ በአጠቃላይ ያለው ፍላጎት ግን ከ2 ሺሕ 900 ሜጋ ዋት በልጦ አያውቅም ነው ያሉት።

ስለዚህም፣ የተጠቃሚውን ፍላጎት እያሟላን ነው ሲሉ የተናገሩት ዳይሬክተሩ፣ የቀረበው የፍላጎት መጠን በገጠር የሚኖረውንና የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ያልሆነውን የማኅበረሰብ ክፍልም ያካተት ስለመሆኑ በቀረበላቸው ጥያቄ ላይ፣ በገጠር ያለው ማኅበረሰብ ኤሌክትሪክ ኃይል ካልተጠቀመ ፍላጎት እንደሌለው ይቆጠራል ሲሉ በመግለጽ ጠቅሰዋል።

አገልግሎት ሰጭው ከኤሌክትሪክ መስመር ጋር የተገናኘውን ተጠቃሚ ፍላጎት ብቻ ነው የሚገልጸው። በዚያ መሠረት ይህን ያህል አቅርቡ ስንባል እናቀርባለን በማለት አክለዋል።
ተቋሙ ሱዳንና ጅቡቲን ጨምሮ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎትና ሌሎች 11 የሚደርሱ ከፍተኛ ኃይል ተጠቃሚ ደንበኞች እንዳሉትም አስረድተዋል።

ይሁን እንጂ በርካታ ፋብሪካዎች የኃይል እጥረትና መቆራረጥ ለሥራቸው እንቅፋት እንደሆነባቸው ሲገልጹ ይሰማል። ለአብነትም በደብረ ብርሃን የሚገኙ ኢንዱስትሪዎች ከዚህ አንጻር ሰፊ ችግር እንደሚያጋጥማቸው ይገለጻል። ዳይሬክተሩ ይህን አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ፣ ‹‹ደብረ ብርሃን ላይ አዲስ ማከፋፈያ ጣቢያ ሥራ ላይ ከዋለ ገና ኹለት ዓመቱ ነው። እስካሁን ባለን ግንኙነትም እዚያ አካባቢ ያሉ ኢንዱስትሪዎች ችግር አለብን ብለው አላሳወቁንም።›› ብለዋል።

አዲስ ማለዳ በቅርቡ ከታላቁ የህዳሴ ግድብ ኃይል ማመንጨቱን አስመልክቶ የመነጨውን ኃይል ምን ዓይነት ጥቅም ላይ ለማዋል እንደታሰበና በምን ሂደት ላይ እንዳለ ለማወቅ ዳይሬክተሩን ብትጠይቅም፣ ስለጉዳዩ ምላሽ መስጠት እንደማይችሉ ገልጸዋል።

በአጠቃላይ፣ የተሟላ የኃይል አቅርቦት አለመኖርና የኃይል መቋረጥ፣ ለኢኮኖሚው ተጨማሪ እሴት ለመፍጠር አስቸጋሪ ሁኔታን ይፈጥራል። እንዲሁም በኢኮኖሚው የእድገት ጉዞ ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ የላቀ ነው። ዜጎችም ማምረት የሚገባቸውን እና ለኢኮኖሚው ማበርከት የሚጠበቅባቸውን አዎንታዊ ሚና የሚያኮላሽ እንደሆነ ይታመናል።

በተደጋጋሚ ጊዜ በሚከሰተው የኃይል አቅርቦት ማነስ ወይም መቆራረጥ የተለያዩ ኢንዱስትሪዎች ማምረት ከሚገባቸው በታች እንዲያመርቱ በማድረግ፣ የሚያመርቷቸውን ምርቶች ለብልሽት በመዳረግ እንዲጎዱና እንዲከስሩ እንደሚያደርግም ይነገራል።
ባለፈው ዓመት ግንባታቸውን ጨርሰው ወደ ምርት የገቡ የምግብ ዘይት አምራቾች በኃይል አቅርቦች ችግር ማምረት በሚችሉት አቅም እያመረቱ እንዳልሆነ መግለጻቸውም ይታወሳል።

ግንባታቸውን አጠናቀው ወደ ምርት ሥራ የገቡ የምግብ ዘይት አምራች ኢንዱስትሪዎች የኃይል አቅርቦት ማግኘት ባለመቻላቸው አንዳንዶቹ ሙሉ ሰዓት በጀነሬተር እያመረቱ ሲሆን፣ አንዳንዶቹ ደግሞ ከሚያመርቱበት ሰዓት ግማሽ ያክሉን በጀነሬተር እየተጠቀሙ እንደሆነ በወቅቱ ገልጸዋል።

ለአብነትም በአማራ ክልል በቡሬ ከተማ የተገነባው ‹‹ፊቤላ›› እንዲሁም ሌላኛው ‹‹አርት ክራፍት ኢንዱስትሪ›› የተሰኙ የምግብ ዘይት አምራች ፋብሪካዎች የኃይል አቅርቦት ችግር እንዳለባቸው አሳውቀዋል። በዚህ ዓመትም ዘይት አምራች ፋብሪካዎች በሙሉ አቅማቸው እንዳያመርቱ እንቅፋት ከሆነባቸው ችግር አንዱ በቂ የኃይል አቅርቦት አለመኖሩና ያለውም መቆራረጥ እንደሆነ ያነሳሉ።

የአማራ ብሔራዊ ክልል የኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ይኸነው ዓለም፣ ከጉዳዩ ጋር በተገናኘ ከአዲስ ማለዳ ጋር አጭር ቆይታ አድርገዋል። በዚህም እንደገለጹት፣ ለውጥ ከመደረጉ በፊት ለክልሉ ይቀርብ የነበረው የኃይል አቅርቦት ያለውን የሕዝብ ቁጥርና የኢንዱስትሪዎችን ብዛት ያላገናዘበና ፍትኃዊነት የጎደለው ነበር። አሁንም የኃይል አቅርቦት ችግር አገራዊ ቢሆንም፣ እንደ አማራ ክልል ያለውን የፍትሀዊነት ችግር ለማስተካከል የተወሰደው እርምጃ በቂ አይደለም ብለዋል።

በዚህም በአሁኑ ወቅት ማሽን በማስገባት ሂደት ላይ ያሉና ግንባታ የጨረሱ በክልሉ የተለያዩ ቦታዎች የሚገኙ 57 ፋብሪካዎች በኃይል እጦት ምክንያት ሥራ እንዳልጀመሩ ነው የጠቀሱት። ከክልሉ የኃይል ፍላጎት አንጻርም ያለው የኃይል አቅርቦት ተመጣጣኝ እንዳልሆነ አመላክተዋል።

ችግሩን ለመፍታት የተለያዩ የመፍትሄ አምራጮች እንደሚወሰዱ የገለጹት ኃላፊው፣ ኃይል በሚያንስበትና በሚቆራረጥበት ወቅትም ፋብሪካዎች ሥራ እንዳያቆሙ ለማድረግ ጀነሬተር እንዲያስገቡ ምክር ከማቅረብ ጀምሮ ከጉምሩክ ከቀረጥ ነጻ እንዲያስገቡ እገዛ እንዲደረግላቸው የድጋፍ ድብዳቤ እንጽፍላቸዋለን ነው ያሉት።

አብዛኞቹ ፋብሪካዎችም መብራት ሲጠፋ ወዲያው የሚነሳ ጀነሬተር እንዳላቸው ጠቁመው፣ የመብራት መቆራረጡ በበዛ ቁጥር ግን ለነዳጅ የሚያወጡት ወጭ ለኪሳራ እንደሚዳርጋቸው አስገንዝበዋል። አንዳንድ ፋብሪካዎች ደግሞ የሚጠቀሙት ኃይል ከፍተኛ በመሆኑ በጄነሬተር የማይንቀሳቀሱ መኖራቸውንም ጠቁመዋል።

በክልሉ ከጊዜ ወደ ጊዜ አዳዲስ ፋብሪካዎች እየተገነቡ ቢሆንም የኃይል አቅርቦት መጠኑ ግን ቀድሞ በነበረበት ነው የሚሉ መኖራቸውን ተከትሎ ኃላፊው ማብራሪያ ሲሰጡ፣ ካለው ፍላጎት አንጻር የሚደረገው ማስፋፊያ በቂ ነው አይባልም እንጂ የማስፋፊያ ሥራዎች ይሠራሉ ነው ያሉት።

ለአብነትም ተከታዩን አንስተዋል፤ ‹‹ደብረ ብርሃን ከተማ ላይ በቅርብ ንዑስ ማከፋፊያ ጣቢያ (Substation) ገንብተናል። ወልዲያ ላይ አቅሙን አሳድገናል። ደብረ ታቦር ላይ አዲስ ተንቀሳቃሽ ንዑስ የማከፋፈያ ጣቢያ (Mobile substation) ገንብተናል።›› አያይዘውም፣ ጎንደር (አዘዞ) እና ሻውራ እንዲሁ የንዑስ ማከፋፈያ ጣቢያዎችን አቅም ማሳደግ እንደተቻለ ገልጸዋል። ቡሬ ላይም ንዑስ ማከፋፈያ ጣቢያ ለማስገንባት መሬት ተለይቶና ጨረታ ወጥቶ አሸናፊው የግንባታ ዕቃዎችን እያስገባ መሆኑንም ነው ያስረዱት።

ከፌዴራል መንግሥቱ ጋር በመነጋገር በቀጣይ 22 ንዑስ ማከፋፈያ ጣቢያዎችን ለማስገንባት እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመውም፣ ክልሉ ከነፋስ፣ ፀሐይና የምድር እንፋሎት (Geothermal) ኃይል የማመንጨት አቅም ስላለው በዘርፉ ባለሀብቶች ገብተው እንዲሳተፉ የቅስቀሳ ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል። ይህንን ተከትሎም ደብረ ብርሃን አካባቢ በንፋስ ኃይል ለማመንጨት ፍላጎት ያላቸው ባለሀብቶች መኖራቸውን አብራርተዋል።

በአጠቃላይም እንደ አገር ችግሩ የሰፋ ነው የሚሉት ኃላፊው፣ በክልሉም የኃይል ማነስና መቆራረጥ የትኛውም አካባቢ ያለ ነው። በተለይ የኃይል መቆራረጥ ደግሞ በኃይል ማነስ፣ ስርቆትና ሌሎች ተያያዥ ችግሮች ሊከሰት ይችላል ብለዋል።
በፋብሪካዎች የሚከሰተውን የኃይል አቅርቦት ችግር በጊዜያዊነት ለማቃለልም ከአንዱ አካባቢ ወደ ሌላው አካባቢ ኃይል የማዘዋወር ሥራ እንደ አንድ የመፍትሔ አማራጭ እንደሚወሰድም ነው የተናገሩት።

በተጨማሪም፣ የኃይል አቅርቦት ችግሩ ከፋብሪካዎች ጋር ብቻ የተያያዘ ሳይሆን፣ ሕይወታቸውን ከኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ጋር ያስተሳሰሩ የኅብረተሰብ ክፍሎችም ክፉኛ እንደሚጎዱ ይነገራል።

ኢትዮጵያ 95 በመቶ የኤሌክትሪክ ኃይል የምታመነጨው ከውሃ ሲሆን፣ 3 ነጥብ 4 በመቶ የሚሆን ደግሞ ከንፋስ ታመነጫለች። ከዚህ ሌላም ዝቅተኛ መጠን ያለው ኃይል ከምድር እንፋሎት ኃይል ማመንጫና ከረጲ ደረቅ ቆሻሻ ኃይል ማመንጫ ኤሌክትሪክ ኃይል ይገኛል ነው የተባለው። ወደፊት ከፀሐይ ኃይል ኤሌክትሪክ ለማመንጨት ዕቅድ ከመያዙ ውጭ ከሶላር እና ከኑክሌር ኃይል የመነጨ ኃይል እስከ አሁን እንደሌላትም ተመላክቷል።

የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት በዜጎች የኑሮ ዘይቤና መሻሻል ላይ የሚያመጣው አዎንታዊ ለውጥ እንዳለ ሆኖ፣ የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት ዋና አንቀሳቃሽ ሞተር የሆነውን የኃይል አቅርቦት ለማሳደግም በትኩረት መሥራት እንደሚገባ ባለሙያዎች ይመክራሉ።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከተጠናቀቀ በኋላ የአገሪቱ ኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም አሁን ካለበት 4 ሺሕ 515 ሜጋ ዋት ወደ 10 ሺሕ ሜጋ ዋት ገደማ ከፍ እንደሚል ይጠበቃል።


ቅጽ 4 ቁጥር 180 ሚያዝያ 8 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here