ከሰሞኑ መነጋገሪያ ከነበሩ የአገሪቱ ጉዳዮች መካከል ሙስናን የተመለከተው በዓይነቱ ለየት ያለ ነበር። ፀረ ሙስና የወራት የፀረ ሙስና ዘመቻ እጀምራለሁ እያለ የሚሰርቁ ተቆጥበው እንዲጠብቁት ይሁን ተዘጋጅተው እንዲያቋርጡ ባይታወቅም፣ ማስጠንቀቂያ አዘል እቅዱን ለሕዝቡም ለሙሰኞቹም ሲያስተጋባ የነበረበት ወቅት ነው።
በሳምንቱ መጀመሪያ ሰሞን አንድ የክፍለ ከተማ ባለሥልጣን ‹መቶ ሺሕ ብር ጉቦ ሊቀበል ሲል እጅ ከፍንጅ ተያዘ› የሚል ዜና ተሰራጭቶ፣ ግለሰቡ እንደተጠርጣሪ መታየቱ ቀርቶ እንደወንጀለኛ ተደርጎ ምስሉና ገንዘቡ ሲተዋወቅ ቆይቷል። ባለአስር ብር ኖት የታሸገ ገንዘብ ሙስና ለመስጠት ይዞ የሚመጣ ባለጉዳይ ስለመኖሩ ሙሰኞችና ተቀባዮቻቸው ብቻ የሚያውቁት ቢሆንም፣ ተደብቆ ሊሰጥ የታሰበ ነገር ግን አነስ እንዲል መታሰቡ እንደማይቀር ይገመታል።
ተጠርጣሪው ግለሰብ ፊት ያን ያህል በርካታ የታሸገ ብር ዘርግቶ ፎቶ አንስቶ ማሳየቱ ለምን ዓላማ እንደሆነ ብዙዎች ግልፅ ሳይሆንላቸው ነበር ዘገባውን ያስተጋቡት። ከቆይታ በኋላ የነገሩን አካሄድ የታዘቡ ግን አስተያየታቸውን ሠንዝረዋል። ስንት ሙስና በሚሠራበትና ብዙዎች በሚጋለጡበት ሂደት የግለሰቡን ጉዳይ ለምን ማጦዝ ተፈለገ በማለት፣ እንደወንጀለኛ ተደርገው ከፍርድ ቤት ውሳኔ በፊት መቅረባቸውን ተችተዋል።
ስለአቀራረቡ ሂደት ከተቹት በተጨማሪ ግለሰቡን በሥራ የሚያውቁም አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል። በዛም ‹እኚህ ሰው አላግባብ መበልጸግ ቢፈልጉ ኖሮ ከዚህ ቀደም የነበሩበት የሥራ መደብ መቻቸው ነበር። ነገር ግን እንደዛ አላደረጉም። አሁንም በአንድ ክፍል ቤት ሦስት ልጆቻቸውን በችግር እያሳደጉ ነው› ብለው የሚመሰክሩም ተሰምተዋል።
የፍርድ ሂደትን ሊያዛቡ ይችላሉ የሚባሉ ነጥቦች ይቆዩንና፣ በአንጻሩ ከመፈረጅ ሊጠብቅና ለማመዛዘን ሊጠቅም ይችላል የሚባሉ ነጥቦችን እናንሳ። በመጀመሪያ ደረጃ ተጠርጣሪው ከዚህ ቀደም ሙሰኞችን አጋልጠው ያሳሰሩ በመሆናቸው የጉበኞች ቡድን ሲያሴርባቸው የነበሩና አሁንም በተሸረበባቸው ሴራ የተጠለፉ መሆናቸውን የሚናገሩ አሉ። በርካታ የመሥሪያ ቤቱ ሠራተኞችም ታሪካቸውን እያወቁት እንዲህ መሆኑ አሁንም አላሠራ ስላሉዋቸው ነው በማለት፣ የፍትህ ሂደቱ ሁሉን ወገን በመስማት የራሱን የማጣራት ሂደት ይከተላል ብለው እንደሚገምቱ ይናገራሉ።
በሌላ በኩል፣ ተጠርጣሪው የሥራ ድርሻቸው የታሸገ ቤትን የማስከፈት ሥልጣንን ስለማያካትት በማይችሉት ነገር እንዴት ሙስና ይሠራሉ ሲሉ ግራ የገባቸውን ሂደት ያስረዱም ነበሩ። ራሳቸው ባይችሉም ከሌሎች ከሚመለከታቸው ሠራተኞች ጋር ተመሳጥረው ነው ሊባል እንደሚችል ሐሳባቸውን ያነሱ አሉ። ይህ ቢሆንም፣ ሌሎቹ እሳቸውን የሚቀላቅሉበት አንዳችም ምክንያት አይኖርም እያሉ የተሟገቱም አሉ።
ሌላው አሳማኝ ጉዳይ አይደለም የተባለው ነገር የገንዘቡ መጠን ነው። በክፍለ ከተማው፣ የታሸገ ተቋም ለማስከፈት የሚከፈለው የቅጣት መጠን 20 ሺሕ ብር ሆኖ ሳለ፣ ያንን በመክፈል ፋንታ በሙስና 100 ሺሕ ብር ለመክፈል ፈቃደኛ የሚሆን ባለጉዳይ ይኖራል ብሎ ለመገመት አስቸጋሪ ነው የሚሉ አሉ። ሙሰኞች ሲጠይቁ በሕጋዊ መንገድ ከሚከፈለው መጠን አሳንሰው ነው እንጂ አምስት እጥፍ አይደለም በማለት፣ ተጠርጣሪው ይህን ያህል ሊቀበሉ ነበር የተባለበትን ምክንያት ያጣጣሉት አሉ። የፍርድ ሂደቱ ለሁላችንም አስተማሪ ይሆናል ብለን እንጠብቃለን።
ቅጽ 4 ቁጥር 180 ሚያዝያ 8 2014



