በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት የ17 መሥሪያ ቤቶችን 38 ተሽከርካሪዎች እና የተለያዩ ያገለገሉ ንብረቶችን በሽያጭ በማስወገድ ከ31 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ማግኘቱን የመንግሥት ግዥ አገልግሎት ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።
ከሐምሌ 1/2013 እስከ መጋቢት 30/2014 ባሉት ዘጠኝ ወራት ከተሽከርካሪዎች እና የተለያዩ ያገለገሉ ንብረቶች በሽያጭ በማስወገድ ከ19 ሚሊዮን ያላነሰ ብር ለማግኘት ታቅዶ፣ ከ31 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መገኘቱን የመንግሥት ግዥ አገልግሎት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ጎጃም ታደለ ለአዲስ ማለዳ ጠቁመዋል።
የ17 መሥሪያ ቤቶችን 38 ያገለገሉ ተሽከርካሪዎችን በሽያጭ በማስወገድ 17 ሚሊዮን 195 ሺሕ 366 ብር የተገኘ ሲሆን፣ 13 ሚሊዮን 916 ሺሕ 154 ብር እንዲሁ የ21 መሥሪያ ቤቶችን 90 ሎት ያገለገሉ ንብረቶች እና አልሙኒየም፣ ስቲል ቁርጥራጭ ብረታ ብረቶችን በሽያጭ በማስወገድ የተገኘ ነው። በአጠቃላይ በዘጠኝ ወራት ከሽያጭ ከተወገዱ ተሽከርካሪዎች እና ንብረቶች 31 ሚሊዮን 111 ሺሕ 521 ብር ገቢ መገኘቱን ነው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዋ የተናገሩት።
ኃላፊዋ አክለውም የመንግሥት ግዥ አገልግሎት በዘጠኝ ወር ለማግኘት ካቀደው እቅድ አንፃር 140 በመቶ ማሳካት ችሏል ብለዋል። የፌዴራል መንግሥት ግዥ አገልግሎት በ2013 በጀት ዓመት በዘጠኝ ወራት ከሽያጭ ከተወገዱ ተሽከርካሪዎች እና ከተለያዩ ንብረቶች 34 ሚሊዮን ብር ሰብስቦ ነበር።
የዘንድሮው ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከኹለት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ብር በላይ ቅናሽ ያሳየ ሲሆን፣ ለዚህም በተያዘው ዓመት በሽያጭ የሚወገዱ የተለያዩ ተሽከርካሪዎችና ንብረቶች በብዛት ባለመላካቸው እና የመሸጫ ዋጋ መጨመሩን ተከትሎ ሽያጩ በተጠበቀው ልክ መካሄድ ባለመቻሉ ነው ተብሏል።
የኢትዩጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት አራት፣ የብሔራዊ የእንስሳት ዝርያ ማሻሻያ ኢንስቲትዩት አራት፣ የፌዴራል አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ማስፋፊያ ባለሥልጣን ኹለት፣ የሕዝብ ተወካዩች ምክር ቤት አንድ፣ የብሔራዊ ሜትሪዎሎጂ ኤጀንሲ አንድ፣ የመንግሥት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ አንድ፣ የአለርት ሆስፒታል አንድ እና የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዘጠኝ፣ በድምሩ 23 ተሽከርካሪዎችን ለአገልግሎቱ አስረክበው ገቢውን ያስገኙ ተቋማት መሆናቸውን ኃላፊዋ ገልፀዋል።
ኃላፊዋ ከዚህ በተጨማሪ የፌዴራል ፖሊስ የተለያዩ ጎማዎችና የተሽከርካሪ መለዋወጫዎች ስድስት ሎት እና የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን የተለያዩ መጠን ያላቸው ጎማዎች 10 ሎት የጨረታ መነሻ ዋጋ በማፅደቅ ለማስወገድ ጨረታ ማቅረብ ተችሏል። የፌዴራል ፖሊስም አንድ ሎት የተለያዩ ጎማዎች እና የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን አንድ ሎት ጎማዎች በመሸጥ 295 ሺሕ 908 ብር እና ከሰነድ ሽያጭ ሦስት ሺሕ ብር ገቢ ተገኝቷል ብለዋል።
ተቋሙ በቀጣይ አራት ወራት የተሻለ ገቢ ለማስገባት ጥረት እንደሚያደርግ እና ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ለማስገባት እንደሚሠራ ኃላፊዋ ጠቅሰዋል።
የመንግሥት ግዥ አገልግሎት በተያዘው በጀት ዓመት በአስራ ኹለት ወራት ቆመው አገልግሎት የማይሰጡ ተሽከርካሪዎችን እንዲሁም አገልግሎት የማይሰጡ የተለያዩ ያገለገሉ ንብረቶችን ለሽያጭ በማቅረብ ከ32 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ለማግኘት ማቀዱ ተጠቅሷል።
ቅጽ 4 ቁጥር 180 ሚያዝያ 8 2014


