የቃፍታ ሽራሮ ብሔራዊ ፓርክ ደን በከፍተኛ ሁኔታ እየተመነጠረ መሆኑ ተገለጸ

0
522

ከ56 ጥበቃዎች መካከል ያሉት ስምንት ብቻ ናቸው

በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ የሚገኘው ቃፍታ ሽራሮ ብሔራዊ ፓርክ ከአምናው በከፋ መልኩ በከፍተኛ ደረጃ አርሶ አደሮች ተከፋፍለው እየመነጠሩት መሆኑን የፓርኩ ሠራተኞች ለአዲስ ማለዳ ተናገሩ።

አርሶ አደሮች ፖርኩን ከአምናው በከፋ ሁኔታ በዘንድሮው ዓመት መሬቱን በመከፋፈል እየመነጠሩት ስለመሆኑ መረጃ እንደደረሳቸው የቃፍታ ሽራሮ ብሔራዊ ፓርክ ጽሕፈት ቤት ተወካይ ኃላፊ ታጠቅ ሻዎል ተናግረዋል።
የፓርኩ ክልል የሆነው የአዲ ጎሹ ቀጠና ጥበቃ ሠራተኛ አያልነህ አለምንህ በበኩላቸው፤ ‹‹እያየን እየተጠረገ ነው›› ሲሉ ደኑ እየተመነጠረ መሆኑን ገልጸዋል።

ባሳለፍነው ዓመት የፓርኩ ደን ተመንጥሮ ለእርሻ መሬት መዋሉን ያስታወሱት ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈቀዱ ሌላኛው የፓርኩ ሠራተኛ በበኩላቸው፤ አሁንም ቢሆን ዝናብ ሲዘንብ ለማረስ በቅድሚያ አርሶ አደሩ ፓርኩን ተከፋፍሎ ደኑን እየመነጠረ ነው ብለዋል።
አክለውም፤ በዚህ ከቀጠለ በቀጣይ ዓመት ፓርኩ ጭራሽ ይጠፋና ባድማ የመሆን ዕድል ይገጥመዋል ሲሉ ነው ፓርኩ አሁን ያለበት ሁኔታ ሊያስከትለው የሚችለውን ጉዳት የጠቆሙት።

የፓርኩ ሠራተኛ አካባቢው በርሃማ መሆኑን ገልጸው፤ የደን ምንጠራው ከቀጠለ ይበልጥ በርሃማነት እየተስፋፋ እንደሚመጣ አያጠራጥርም ነው ያሉት።

ሌላኛው ደበሳይ አዳናው የተባሉ ግለሰብ ለአዲስ ማለዳ በሰጡት አስተያየት፣ ሰሞኑን ደኑ እየተጨፈጨፈ መሆኑን የተናገሩ ሲሆን፤ የሚቆረጡትን ዛፎችም አርሶ አደሮቹ እያከሰሏቸው ነው ብለዋል።
ደበሳይ በተያያዘም በፓርኩ ውስጥ ያሉ እንስሳት አልፎ አልፎ ቢታዩም አብዛኛዎቹ እየተሰደዱ መሆናቸውን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

አርሶ አደሮች ፓርኩን የሚመነጥሩት፤ የእርሻ መሬት ዕጥረት ገጥሟቸው ሳይሆን በተለያዩ ምክንያቶች መሆኑንም የፓርኩ ጽሕፈት ቤት ተወካይ ታጠቅ አብራርተዋል።

አርሶ አደሮቹ ደኑን ለመመንጠር ያነሳሳቸው የመጀመሪያው ምክንያት ድሮ በወያኔ ወቅት የወያኔ አባል የሆኑ ሰዎች በፓርኩ ሥራ እንዲሳተፉ እየተደረጉ ሌላው የአካባቢው ነዋሪ ግን ከሥራ ይባረር እንደነበር በማሰብና ቂም በመያዝ ነው ተብሏል። ኹለተኛው አነሳሽ ምክንያት ‹‹ፓርኩ ባለቤት የለውም፤ የወያኔ ነው›› በሚል ግንዛቤ የጎደለው አመለካከት እንደሆነም ተብራርቷል።

ሌላኛውና ሦስተኛው ምክንያት አካባቢው ‹ቀይ መስመር ላይ በመሆኑ› ማለትም የጦርነት ቀጠና ስለሆነ፤ አርሶ አደሮቹ የቀን ሠራተኛ አናገኝም የሚል ስጋት ስላደረባቸው፤ በተደጋጋሚ ሲታረስ ከኖረው ማሳ ይልቅ አዲስ መሬት አረም እንደማይበቅልና ከፍተኛ ምርት እንደሚያስገኝ በማሰብ ነው ብለዋል።

በሌላ በኩል በቃፍታ ሽራሮ ብሔራዊ ፓርክ የጽሕፈት ቤት ሠራተኞች ብዛት በአጠቃላይ 72 እንደነበሩና ከእነዚህም መካከል 56 የጥበቃ ሠራተኞች ሲሆኑ፤ በአሁኑ ወቅት አገልግሎት እየሰጡ ያሉት ግን ስምንት ሠራተኞች ብቻ መሆናቸውን ታጠቅ አብራርተዋል።
አራቱ ሠራተኞች አዲ ጉቱ ይገኛሉ የተባለ ሲሆን፤ አንዱ ሰሞኑን ጡረታ ስለወጣ ሦስት ብቻ እንደቀሩም ታጠቅ ተናግረዋል። ከዚህም በተጨማሪ ዘሩባቢት በተሰኘ ጣቢያ አንዲት ሴት ጥበቃ እንዳለች እንዲሁም ሌሎች ሦስት ጥበቃዎች ደግሞ አደባይ ቀበሌ እንዳሉ ታጠቅ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ኃላፊው ፓርኩን ለመታደግ፤ ባሳለፍነው ሚያዚያ 1/2014 ጉዳዩን በተመለከተ ከወረዳ፤ ከዞን እንዲሁም ከፌዴራል ከመጡ አመራሮች ጋር ውይይት እንዳደረጉ ጠቅሰዋል።
ታጠቅ ለአዲስ ማለዳ የገለጹት፤ በፓርኩ የሚደርሰውን ጥቃት እንዲቆም ለማድርግ ዞንና ወረዳ ጥበቃ ለማድረግና ጥፋት የሚያደርሱትን አካላት ለማስወጣት ኃላፊነት ወስደዋል።

አዲስ ማለዳ ከዚህ ቀደም ለንባብ ባበቃችው እትሟ ከ300 በላይ ዝሆኖች ወደ ኤርትራ እንደተሰደዱ መዘገቧ ይታወሳል።

ቃፍታ ሽራሮ ብሔራዊ ፓርክ የተመሠረተው በ1999 ሲሆን፤ ከ42 በላይ የዱር እንስሳት፤ 200 የወፍ፤ አምስት የአይጥ ዝርያዎች፤ ዘጠኝ ተሳቢ እንስሳትንና ሌሎችንም አስጠልሎ የኖረ 2174 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ስፋት ያለው ፓርክ ነው።


ቅጽ 4 ቁጥር 180 ሚያዝያ 8 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here