ባለፈው ዘጠኝ ወራት ለውጭ ገበያ ከቀረበ ቡና ከ819 ሚሊዮን በላይ ዶላር ገቢ መገኘቱን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን የገበያ ልማትና ቁጥጥር ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክትር ሻፊ ዑመር ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ በዘጠኝ ወራት 188 ሺሕ 250.3 ቶን ቡና ወደ ተለያዩ አገራት ለመላክ ታቅዶ 210 ሺሕ 819.81 ቶን ቡና ወደ ውጭ ገበያ ቀርቦ 894.3 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቷል ብለዋል።
በ2014 በጀት ዓመት በዘጠኝ ወራት የተላከው ቡና ካለፈው ዓመት ተመሳሰይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር፣ 146 ሺሕ 746.6 ቶን ቡና የተላከ ሲሆን፣ 64 ሺሕ ቶን ብልጫ የተመዘገበበት እንደሆነ ኃላፊው ጠቁመዋል።
ባለፈው ዓመት በተመሳሳይ ወር ኢትዮጵያ 146 ሺሕ 746 ቶን ቡና ወደ ውጭ ልካ 512 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገቢ እንዳገኘች ያስታወሱት ሻፊ፣ ዘንድሮ በዘጠኝ ወር የተገኘው ገቢ 381.9 ሚሊዮን ዶላር ብልጫ እንደታየበት አስታውቀዋል።
በዘጠኝ ወራት ውስጥ የተገኘው ገቢ ጥሩ መሆኑን አመላካች ነው ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፣ በቀሪዎቹ ሶስት ወራት የሚገኘው ገቢ በዕቅዱ ልክ ቢሄድ እንኳን ከተቀመጠው አኃዝ በላይ አፈጻጸም እንደሚመዘገብ ለመገመት ይቻላል ብለዋል።
ባለሥልጣኑ ኹለት ስትራቴጂዎችን ነድፎ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ ያስታወቁት ሻፊ የመጀመርያው ነባሩ የኢትዮጵያ ቡና መዳረሻ ገበያዎች ላይ በተወዳዳሪነት መቆየት ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ አዳዲስ የቡና ገበያ መዳረሻ አገሮችን ማፈላለግ ላይ ያተኮረ እንደሆነ ተናግረዋል።
አዳዲስ የቡና መዳረሻ አገሮች ከሆኑት ውስጥ፣ ቻይናና ታይዋን ተጠቃሾቹ እንደሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ ከእነዚህ ከፍተኛ የኢትዮጵያ የቡና ገዥ አገሮች ምድብ ውስጥ እየገቡ ካሉ አገሮች ጋር ያለውን ገበያ ይበልጥ ለማጠናከር በርካታ ሥራዎች እንደሚከናወኑ ጠቁመዋል።
የኢትዮጽያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን በተያዘው ዓመት ከቡና ኤክስፖርት ለማግኘት ካቀደው አንጻር ሲፈተሽ የአንድ ቢሊዮን ዶላር አጠቃላይ ገቢ ዕቅድ ለማሳካት የሚያስችል እቅድ እንዳለው ተገልጿል።
ባለስልጣኑ አክሎም፣ በቀሪዎቹ ሶስት ወራት ውስጥ ከኤክስፖርት የሚገኘውን ገቢ በዕቅዱ ልክ ለማሳካት እየሰራ ሲሆን፣ ባለስልጣኑ አፈጻጸሙ እንደሚመዘገብ ለመገመት እንደማይቸገርም ኃላፊው ገልጸዋል።
ባለሥልጣኑ ሁለት ስትራቴጂዎችን ነድፎ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ እና የመጀመርያው ነባሩ የኢትዮጵያ ቡና መዳረሻ ገበያዎች ላይ በተወዳዳሪነት መቆየት ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ አዳዲስ የቡና ገበያ መዳረሻ አገሮችን ማፈላለግ ላይ ያተኮረ እንደሆነ ተናግረዋል።
አዳዲስ የቡና መዳረሻ አገሮች ከሆኑት ውስጥ ሩሲያ፣ ቻይናና ታይዋን ተጠቃሾቹ እንደሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ ከእነዚህ ከፍተኛ የኢትዮጵያ የቡና ገዥ አገሮች ምድብ ውስጥ እየገቡ ካሉ አገሮች ጋር ያለውን ገበያ ይበልጥ ለማጠናከር በርካታ ሥራዎች እንደሚሰሩም ሀላፊው ተናግረዋል።
የቡና ዋጋ በዓለም አቀፍ ገበያ እየጨመረ መምጣቱ በዘርፉ እየተገኘ የሚገኘው ገቢ ለመጨመሩ የራሱ የሆነ አስተጽዖ እንዳለው የተገለጸ ሲሆን፣ ከዚህ በሻገር በተለያዩ አገሮች በሚደረጉ ዓለም አቀፍ ኤግዚቢሽኖች ላይ ምርቱን በማስተዋወቅ የሚደረጉት ጥረቶች ሚና እንዳላቸው ተናግረዋል።
የኢትዮጵያን ቡና ከገዙት አገራቶች መካከል ጀርመን፣ ሳዑድ ዓረቢያና ጃፓን ይገኙበታል።
ቅጽ 4 ቁጥር 180 ሚያዝያ 8 2014



