ኹለት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ብቻ ሕጉን የጣሱ 22 የተቋሙ ሠራተኞች ላይ ከሥራ እስከማሰናበት የደረሰ እርምጃ መውሰዱን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወሳኝ ኹነትና ምዝገባ ኤጀንሲ ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።
የኤጀንሲውን ሕግ በመጣስ ወንጀል የሚፈጸሙ አካላትን በሕግ ተጠያቂ ለማድረግ ከ11 ክፍለ ከተማ እና ከሁሉም ወረዳዎች ባለሙያዎችን በማዋቀር የቁጥጥር ሥራ የተሠራ እንደሚገኝ እና ከአገራዊ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በኋላ ብቻ 22 የተቋሙ ሠራተኞችን በሕግ ተጠያቂ በማድረግ አስተዳደራዊ እርምጃ መውሰዱን የኤጀንሲው ከፍተኛ አማካሪ መላክ መኮንን ለአዲስ ማለዳ ጠቁመዋል።
አማካሪው አክለውም፣ እነዚህ ወንጀሎች የተፈጸሙት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ባስቀመጠው የሥራ አቅጣጫ መሠረት፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ሁሉም የግል ባንኮች በአዲስ አበባ ከተማ የሚኖሩ ደንበኞች መረጃቸውን በአዲስ መልክ እንዲያስመዘግቡ መጠየቁን ተከትሎ መታወቂያ ለማውጣት እና ለማሳደስ በተቋሙ በሁሉም ቅርንጫፎች አገልግሎት ለማግኘት የሚመጡ ሰዎች ቁጥር በጨመረበት ወቅት ነው ብለዋል።
በተያዘው በጀት ዓመት ኤጀንሲው ለአዲስ ማለዳ መረጃ እስከሰጠበት እለት ድረስ የተቋሙን ሕግ የጣሱ 60 የሚሆኑ ሠራተኞች ላይ ከደመወዝ ቅጣት ጀምሮ ከሥራ እስከማሰናበት የደረሰ ተገቢው አስተዳደራዊ እርምጃዎች መውሰዳቸውንም አማካሪው ጠቁመዋል።
አማካሪው አክለውም፣ ኤጀንሲው በከተማዋ ያለውን ከፍተኛ የተገልጋይ ቁጥር እና የተቋም የማስተናገድ አቅም ከግምት በማስገባት የተቋረጡ አገልግሎቶችን ቀድሞ በተዘጋጀው አሠራር መሠረት የነዋሪውን የመኖሪያ አድራሻን መሠረት ያደረገ በተለምዶ የቀጠና ወይም የብሎክ አደረጃጀት መርሃ-ግብር አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል ብለዋል።
የሲስተም መቆራረጥ የፈጠረውን ከፍተኛ ችግር ለመቅረፍ የማንዋል አገልግሎት በከፍተኛ ቁጥጥር አገልግሎት እየተሰጠበት ነው የተባለ ሲሆን፣ የተገልጋዩን ቁጥር ካለው የህትመት አቅም ጋር ለማጣጣም ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝም ተነግሯል።
ይሁን እንጂ በአንዳንድ በርካታ የሕዝብ ቁጥር ባላቸው ወረዳዎች ላይ ጉዳያችሁን በቶሎ እናስጨርሳለን፣ ቀጠሮ እንዳይኖር እናደርጋለን የሚሉና ሰልፍ እንይዛለን በማለት ገንዘብ የሚጠይቁ መኖራቸውን ኤጀንሲው በማወቅ እየተከታተለ ነው ተብሏል።
ተቋሙ ሕጉን የሚጥሱ አካላትን በሕግ እርምጃ እንዲወሰድ እያደረገ ነው የተባለ ሲሆን፣ ተገልጋዩ ኅብረተሰብ እንዲህ አይነት ሁኔታዎች ሲገጥሙት በአቅራቢያ ላለ የጸጥታ መዋቅር ወይም በተቋሙ ነፃ የስልክ መስመር 7533 እንዲጠቁም አማካሪው ጠቁመዋል።
አማካሪው አክለውም በክፍያ ማለዳ ሰልፍ እንይዛለን ለሚሉ ገንዘብ በመስጠት ተግባር ላይ የሚሳተፉ ነዋሪዎችም ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስበዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የወሳኝ ኩነት ምዝገባ እና መረጃ ኤጀንሲ አገር አቀፍ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የጣላቸው የአገልግሎት ክልከላዎች ከተነሱ በኋላ የተጀመሩ የመታወቂያ አገልግሎቶችን ጨምሮ ከወረዳ ጽሕፈት ቤቶች እስከ ዋና መሥሪያ ቤት በቀን በአማካይ ከ12 ሺሕ በላይ ተገልጋዮችን ማስተናገዱ ተገልጿል።
ተቋሙ በክልከላው ወቅት በማዕከል ታትመው የነበሩ ከ69 ሺሕ በላይ የነዋሪነት ዲጂታል መታወቂያዎችን በኹለት ዙር ለኹለት ሳምንታት አስፈላጊውን ማጣራት በማድረግ ለተገልጋዩ አድርሷልም ተብሎ ከወር በፊት ይፋ ተደርጎ ነበር።
ቅጽ 4 ቁጥር 180 ሚያዝያ 8 2014



